1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ሰሚ ያጡ የወሲባዊ ትንኮሳ ሰለባዎች በሊባኖስ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26 2015

በሊባኖስ ከሚኖሩ የውጭ ሃገራት ሴት የቤት ሠራተኞች 68 በመቶው ወሲባዊ ትንኮሳ እንደሚያጋጥማቸው ሁለት ተቋማት በሠሩት ጥናት ይፋ አድርገዋል። ሊባኖስ ወንጀሉን የሚፈጽሙ ግለሰቦችን እስከ አራት ዓመታት በሚደርስ እስራት የሚቀጣ ሕግ ቢኖራትም የውጭ ሃገራት ዜጋ የሆኑ የቤት ሠራተኞችን ያገለለ ነው።

https://p.dw.com/p/4IyuX
Libanon Beirut | entlassene Haushaltshilfen aus Äthiopien
ምስል Mekdes Ylima

ሰሚ ያጡ የወሲባዊ ትንኮሳ ሰለባዎች በሊባኖስ

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሊባኖስ የሚገኙ ሴት የቤት ሠራተኞች አስገድዶ መደፈርን ጨምሮ የተለያዩ ወሲባዊ ትንኮሳዎች እንደሚፈጸሙባቸው «እኛ ለእኛ በስደት» የተባለው ለቤት ሠራተኞች መብት የሚሟገት ድርጅት እና በሊባኖስ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በጥምረት ያከናወኑት ጥናት ይፋ አድርጓል። ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው የቤት ሠራተኞች 86 በመቶው የኢትዮጵያ እና የፊሊፒንስ ዜጎች ናቸው። በሊባኖስ ከሚገኙ ሴት የቤት ሠራተኞች 76 ከመቶ ገደማ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ የእኛ ለእኛ በስደት መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር ባንቺ ይመር ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።

የጥናቱ ውጤት ምን ይላል?

ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው የቤት ሠራተኞች 68 በመቶው በሥራ ላይ ቢያንስ አንድ ጊዜ ወሲባዊ ትንኮሳ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል። በጥናቱ መሠረት በቤት ሠራተኞቹ ላይ የሚፈጸሙት ወሲባዊ ትንኮሳዎች እስከ አስገድዶ መድፈር የዘለቁ ናቸው። ከትንኮሳዎቹ መካከል ወሲባዊ አስተያየቶች እና ቀልዶች መሰንዘር፣ ስለ የቤት ሠራተኞቹ ወሲባዊ ህይወት እና አካላዊ ገጽታ አጸያፊ ጥያቄዎች ማቅረብ፣ የመራቢያ አካላትን፣ ራቁት ገላን በግላጭ ማሳየት እንደሚገኙበት ጥናቱ ይፋ አድርጓል። ያለ ፈቃድ የቤት ሠራተኞችን ሰውነት መንካት፣ ማቀፍ፣ መሳም፣ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው የስልክ ጥሪዎች ማድረግ እና መልዕክቶች፣ ፎቶግራፎች እና ምስሎች መላክ፣ ፎቶ ማንሳት፣ ቪዲዮ መቅረጽ የመሳሰሉ ትንኮሳዎች የጥናቱ ተሳታፊዎች እንደገጠማቸው ገልጸዋል። ወሲብ ለመፈጸም ጥያቄ ወይም ጫና የገጠማቸውም ይገኙበታል።

ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው በሊባኖስ የሚገኙ ሴት የቤት ሠራተኞች መካከል 56 በመቶ ገደማው ከላይ ከተጠቀሱት ወሲባዊ ትንኮሳዎች ቢያንስ አንዱ እንደገጠማቸው ተናግረዋል። ወደ 12 በመቶ ገደማው ደግሞ ወሲባዊ ትንኮሳ እንደገጠማቸው ጥናቱን ላከናወኑ ባለሙያዎች ቢያረጋግጡም የደረሰባቸውን በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

ተንኳሾቹ እነማን ናቸው?

የእኛ ለእኛ በስደት እና በሊባኖስ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የጋራ ጥናት ወሲባዊ ትንኮሳዎቹ በአብዛኛው የሚፈጸሙት በአሰሪዎች መሆኑን ይገልጻል። ጥናቱ እንደሚያሳየው 70 በመቶ ወሲባዊ ትንኮሳዎች የሚፈጸሙት በተለይ በወንድ ቀጣሪዎች ነው። ጥናቱን ካከናወኑ ባለሙያዎች አንዷ የሆኑት የእኛ ለእኛ በስደት መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ባንቺ ይመር "በአሰሪዎች፣ በታክሲ ሾፌሮች፣ በፖሊሶች ወሲባዊ ትንኮሳ ይደርሳል። በዘመድ፣ ቤት በሚገኙ [የቀጣሪዎች] ያላገቡ ልጆች ወይንም አግብተው ከቤት ወጥተው እናታቸውን ለመጠየቅ በሚመጡ ወሲባዊ ትንኮሳው ይፈጸማል" ስትል ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።

"በቤት ውስጥ የተለያየ ችግር ደርሶባቸው፤ ተደብድበው፤ ተደፍረው፤ ገንዘብ ሳይሰጣቸው ቀርቶ፤ [ወደ አገራቸው] አላሳፍርም ብለዋቸው ወይም ከቤት አባረዋቸው ጠፍተው የሚወጡ ልጆች አሉ። እነዚህ ልጆች ደግሞ ያለ ወረቀት ነው የሚሠሩት" የምትለው ባንቺ እነዚህ የቤት ሠራተኞች በእንቅስቃሴያቸው ለወሲባዊ ጥቃት እንደሚጋለጡ አስረድታለች። "ታክሲ ውስጥ መነካት አለ፤ አላስፈላጊ ንግግሮች አሉ። የታክሲ ሹፌሮች በጣም በጣም አስቸጋሪዎች ናቸው። ወይ ራሳቸውን ይነካሉ፤ ወይ ብር ልስጥሽ እና እንተኛ አለ። ሥራ ቦታ ደግሞ ሲሔዱ በጣም አስቸጋሪዎች፤ ቢሮ ውስጥ የተለያዩ ትንኮሳዎች የሚያደርጉ ሥራ የማያሰሩ አለቆቻቸው አሉ" ብላለች ባንቺ።

ኢትዮጵያውያኑ ዶላር፣ ሥራ እና መመለሻ በጠፋባት ሊባኖስ

ወሲባዊ ትንኮሳ ከገጠማቸው 75 በመቶው በሊባኖስ በተመላላሽነት የሚሠሩ ሲሆኑ 25 በመቶው አሁንም በወሰዷቸው አሠሪዎቻቸው ዘንድ በቋሚነት የሚያገለግሉ ናቸው። በሊባኖስ በሕጋዊ መንገድ እና ያለመኖሪያ ፈቃድ በሠራችባቸው ዓመታት «ችግሩንም መከራውንም ቀምሺያለሁ» የምትለው ባንቺ "በከፋላ ሥርዓት አንዲት የሰው ቤት ሠራተኛ ወደ ሊባኖስ ከመጣች ያለ አሠሪዋ ፈቃድ ሥራ መቀየር፤ ከአገር መልቀቅ የአሠሪዋን ሥም መቀየር አትችልም። በዚህ ምክንያት መፍትሔ አግኝታ ወይም ጥላ እስክትጠፋ ወይ ደግሞ ኤጀንሲዋ ጋር ሔዳ ቤት እስኪቀይርላት ድረስ ወይ ውሏን ጨርሳ እስክትወጣ ድረስ የሚፈጸምባት ጾታዊ ትንኮሳ በየዕለቱ ነው የሚሆነው ማለት ነው" ስትል ታስረዳለች።

ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው የቤት ሠራተኞች 95 በመቶው ወሲባዊ ትንኮሳ ሲገጥማቸው ፈጻሚው እንዲያቆም ግፊት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ወሲባዊ ትንኮሳ በፈጸሙባቸው ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ወይም ሌላ እርምጃ የወሰዱ የቤት ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው። ሊባኖስ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጻሚዎችን እስከ አራት ዓመት በሚደርስ እስራት የሚቀጣ ሕግ ቢኖራትም ለውጭ አገራት ዜጎች ከለላ የሚሰጥ አይደለም።

"በሊባኖስ ሕግ መሠረት የሌላን አገር ዜጋ ወይንም የቤት ሠራተኛን መንካት ወይንም ጾታዊ ትንኮሳ ማድረግ ሕገ ወጥ አይደለም። ሕጉ ላይ ስላልተካተትን የትም ሔደን ማመልከት አንችልም" ስትል ባንቺ ሕጉ ለቤት ሠራተኞች ከለላ ባለመስጠቱ የተፈጠረውን ዳፋ አስረድታለች። ወሲባዊ ትንኮሳ የተፈጸመባቸው የቤት ሠራተኞች ለቀጣሪዎቻቸው ቢናገሩም መፍትሔ አያገኙም።

"ለሚስቶቻቸው፣ ለእናቶቻቸው ወይ ለአባቶቻቸው በሚነግሩበት 'ሰዓት ዝም በሉ' የሚል ምላሽ የተሰጣቸው፤ "ፊት ሰጥተሽው ነው፤ ባሌ ይኸን አያደርግም። ስሙን አታጥፊ" የሚል ውንጀላ የገጠማቸው መኖራቸውን በጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው የቤት ሠራተኞች መረዳታቸውን ባንቺ ገልጻለች።  "ባሎቻቸውን ወይም ልጆቻቸውን እንደመቆጣት ´የቤተሰቤን ስም አጠፋሽ፤ የባሌን ስም አጠፋሽ` ብለው ይናደዳሉ" የምትለው ባንቺ "አዝነው ´እኔም ሴት ነኝ` ብለው ባሎቻቸውን የሚቆጡ፤ በባሎቻቸው ላይ እርምጃ የሚወስዱ እኛ ባደረግንው ጥናት አልገጠመንም" በማለት አስረድታለች።

ለኢትዮጵያውያኑም ሆነ ከሌሎች አገሮች ወደ ሊባኖስ ላመሩ የቤት ሠራተኞች በጥናቱ ይፋ ከሆነው ወሲባዊ ትንኮሳ ባሻገር የአገሪቱ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ሌላ ብርቱ ፈተና ሆኖባቸዋል። በፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ የምትናጠው አገር ካለፈው እሑድ ወዲህ ያለ ፕሬዝደንት ቀርታለች። የስድስት ዓመታት የሥራ ዘመናቸው ተጠናቆ ከፕሬዝደንትነታቸው የተሰናበቱት ሚሼል ኦውን ሊባኖስ እና ብሔራዊ ባንኳ ተዘርፈው የአገሪቱ መጻኢ ጊዜ አሳሳቢ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።

የሊባኖስ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ምን ያህል ብርቱ ነው?

የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው የሊባኖስ አመታዊ የምርት መጠን በጎርጎሮሳዊው 2018 ከነበረበት 55 ቢሊዮን ዶላር በሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ 20.5 ቢሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል። የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ 90 በመቶ የመግዛት አቅሙን አጥቷል። በዚህ ሳቢያ ሊባኖስ ከዓለም ገበያ የምትሸምታቸው ሸቀጦች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምዕራብ እስያ የኤኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽን (ESCWA) መረጃ መሠረት 6.5 ሚሊዮን ሊባኖሳውያን ወይም 80 በመቶ የአገሬው ዜጎች ደሐ ናቸው። የዚህ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ በትር በቀጥታ የተሻለ የሥራ ዕድል እና ገቢ ፈልገው ወደ ሊባኖስ ያመሩ የቤት ሠራተኞች ላይ የሚያርፍ ነው።

ከሁለት ዓመታት በፊት ሊባኖስ በገጠማት የኤኮኖሚ ቀውስ "ቤሩት ውስጥ ያለ ወረቀት የሚኖሩ ልጆች ሥራ ፈተው" እስከ መቀመጥ መገደዳቸውን ባንቺ ትናገራለች። ኢትዮጵያውያኑ ሥራ ቢሰሩ እንኳ በአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ መዳከም ምክንያት ኑሯቸው "ከእጅ ወደ አፍ" ሆኖ የምግብ፣ የቤት ኪራይ እና የሕክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን እስከ መቸገር ደርሰዋል።

በሊባኖስ ኤኮኖሚያዊው ቀውስ በበረታበት ወቅት የአገሬው ሰዎች የቤት ሠራተኞቻቸውን አውጥቶ እስከ መጣል ደርሰዋል። እኛ ለእኛ በስደት ላለፉት ሁለት ዓመታት ከ15 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የቤት ሠራተኞች የምግብ እና የሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉን ዋና ዳይሬክተሯ ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች። ባንቺ እኛ ለእኛ በስደት የተባለውን የመብት ተሟጋች ተቋም የመሠረተችው የቤት ስደተኞቹ ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ ነው። ማኅበሩ በሰው ቤት ሰተራተኛ ሴቶች የሚመራ ሲሆን ተቋሙ በካናዳ ለትርፍ ያልተቋቋመ ሆኖ ተመዝግቧል። ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ የቤት ሠራተኞች እንደ ትምህርት ያሉ ዕገዛዎች ለማቅረብ የሲቪክ ድርጅት ሆኖ ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያውያኑ የቤት ሠራተኞች ፈተና ግን በዚያው በሊባኖስ ብቻ አይደለም። "ልጅ ያላቸው፤ ደካማ ቤተሰብ ያላቸው እና አቅመ ደካሞች የሚደግፉ አሉ። ኢትዮጵያ ያለ ቤተሰብ ደግሞ አይረዳም። ቤይሩት ናቸው እንጂ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን አይረዱም" ስትል የእኛ ለእኛ በስደት ዋና ዳይሬክተር ትናገራለች።

"ቤተሰብ መርዳት አለመቻላቸው፣ ቤተሰብ ችግራቸውን አለመረዳቱ፣ የሥራ መጥፋት፣ የምንዛሪው መውደቅ እና የኑሮ ውድነቱ" በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚታተኑ ችግሮች ናቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ሊባኖስ ያመሩ የቤት ሠራተኞች ለሚገጥሟቸው ፈተናዎች መፍትሔው እንዲህ ቀላል አይደለም። «የእኛ ለእኛ በስደት» ዋና ዳይሬክተር ባንቺ ይመር እንደምትለው በተለይ በወሲባዊ ትንኮሳ የሚያርፍባቸው ጠባሳ ለዓመታት አብሯቸው የሚዘልቅ ነው። የቤት ሠራተኞቹ በዚያው በሊባኖስ መፍትሔ ማግኘት የሚቸግራቸው ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም ሕመማቸው አብሯቸው ይዘልቃል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ