1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀኝ ጽንፈኞች ተቃውሞና የጀርመን መሪዎች ቁጣ 

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 26 2012

በበጀርመን የኮሮና ተህዋሲ ሥርጭትን ለመከላከል የተጣሉ ገደቦችን በመቃወም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ቀኝ ጽንፈኞች የወሰዱት እርምጃ አስደንግጧል ።እነዚሁ ሰልፈኞች የጀርመንን መጥፎ ታሪክ የሚያስታውሱ ባንዲራዎችንና ዓርማዎችን ይዘው አደባባይ መውጣታቸውና የሃገሪቱ ዴሞክራሲ ተምሳሌት የሆነውን የጀርመን ምክር ቤት ጥሰው ለመግባት መሞከራቸው ተወግዟል።

https://p.dw.com/p/3hsPu
Berlin | Demonstration gegen Corona Maßnahmen am Reichstagsgebäude
ምስል Getty Images/O. Messinger

የቀኝ ጽንፈኞች ተቃውሞና የጀርመን መሪዎች ቁጣ 

ባለፈው ቅዳሜ በጀርመን ዋና ከተማ በበርሊን፣በሃገሪቱ የኮሮና ተህዋሲ ሥርጭትን ለመከላከል የተጣሉ ገደቦችን በመቃወም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ቀኝ ጽንፈኞች የወሰዱት እርምጃ አስደንግጧል ።እነዚሁ ሰልፈኞች የጀርመንን መጥፎ ታሪክ የሚያስታውሱ ባንዲራዎችንና ዓርማዎችን ይዘው አደባባይ ከመውጣታቸውም በላይ የሃገሪቱ ዴሞክራሲ ተምሳሌት የሆነውን የጀርመን ምክር ቤት ጥሰው ለመግባት መሞከራቸው ተወግዟል።የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን በዚህ ላይ ያተኩራል። ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።
በጀርመን የኮሮና ተህዋሲን ሥርጭት ለመግታት የተጣሉ ክልከላዎችን በመቃወም ቅዳሜ ነሐሴ 23፣2012 ዓም በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ነሐሴ 29፣2020  በተካሄደው ሰልፍ ላይ ቁጥራቸው እስከ 30 ሺህ እንደሚደርስ  የተገመተ ሰዎች መካፈላቸው ተገልጿል።የበርሊን ከተማ ሹማምንት ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ሰልፉ እንዳይካሄድ ማገዳቸውን አስታውቀው ነበር። ሆኖም ፍርድ ቤት እገዳውን ካነሳ በኋላ ነበር ሰልፉ የተካሄደው።እናም«ኮሮና የለም መንግሥትም በሽታውን ለመቆጣጠር በሚል ምክንያት የጣለብን አስገዳጅ ገደቦች አያስፈልጉም  ይነሱ»የሚሉ የሚገኙባቸው እነዚሁ ሰልፈኞች፣የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንዳለው  በጀርመን ራስንና ሌላውንም ከኮሮና ለመጠበቅ የተደነገጉ ደንቦችን ጥሰው ነበር አደባባይ የወጡት። ድርጊታቸውም በበርሊን ከተማ አስተዳደር ተኮንኗል።

Deutschland Berlin Protest gegen Corona-Maßnahmen
ምስል DW/D. Vachedin

በዚህ ግርግር ደግሞ ቁጥራቸው እስከ አራት መቶ የተገመተ ሰልፈኞች ከሌሎቹ ተነጥለው የጀርመን ምክር ቤትን ጥሰው ለመግባት ሙከራ አድርገዋል።ይህም  ብዙዎችን አስቆጥቷል። ሰልፈኞቹ ከ1871 እስከ 1918 ጥቅም ላይ የዋሉትን የጀርመን የታሪክ ጉድፍ መታወሻ የተከለከሉ ባንዲራዎችንና ዓርማዎችን ይዘው ነበር። 
ከተለያዩ የጀርመንና የአውሮጳ ከተሞች የመጡት እነዚህ ሰልፈኞቹ የጀርመን ታሪክ ጥላሸት የሚባሉትን እነዚህን  ባንዲራዎችና ዓርማዎችን  በምክር ቤቱ ህንጻ ደረጃዎች ላይ ወጥተው ማውለብለባቸው በጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ክፉኛ ተወግዟል።
«ክቡራትና ክቡራን የዘውዳዊው አገዛዝ ባንዲራዎች፣ የዘውዳዊው አገዛዝ የጦርነትእና ፖለቲከኞች እንዲሁም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች   ባንዲራዎች የዴሞክራሲያችን ማዕከል በሆነው በነጻ  በተመረጠው በጀርመን ፓርላማ ደረጃዎች ላይ  መታየቱ ከዚህ ስፍራ ታሪክ አንጻር አስከፊ ብቻ ሳይሆን በፍጹም ልንታገሰው የምንችል አይደለም።ማንኛውንም ፀረ ዴሞክራሲያዊ የስም ማጥፋት ዘመቻም ሆነ የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክን በጀርመን ምክር ቤት ፊት ማውገዝን አንታገስም።»
ሽታይንማየር በዚህ የውግዘት መልዕክታቸው ቅዳሜ በጀርመን ምክር ቤት ፊት ለፊት የሆነው ብዙዎችን ማስደንገጡን አልሸሸጉም።ድርጊቱን ከፈጸሙት ጋር አብሮ የሚታይም ሆነ የሚተባበር ከነርሱ ተለይቶ የሚታይ እንደማይሆን ነው ያሳሰቡት።  
«ባለፈው ቅዳሜው የበርሊኑ ሰልፍ ቀኝ ጽንፈኞች የፈጸሙት የደቦ ጥቃትና ኹከት ብዙ ሰዎችን አስፈርቷል፤አስቆጥቷል።እንደዚህ ዓይነቶቹን ኹከቶች ወደፊትም አንታገስም።በኮሮና ምክንያት በወሰድናቸው እርምጃዎች የሚበሳጭ ወይም አስፈላጊነታቸውን የሚጠራጠር ሊቃወም ይችላል። ሆኖም ተቃዋሚ ሰልፈኞች የዴሞክራሲ ጠላቶችና የፖለቲካ ቀስቃሾች ጋሪ ሲጠለፉ ይህን ልረዳ አልችልም።በየጎዳናው ከቀኝ ክንፍ ጽንፈኞች ጋር የሚተባበር ፣ከአፍቃሪ ናዚዎች ፣ የውጭ ዜጎችን ከሚጠሉ እና ከፀረ ሴማውያን ራሱን በግልጽና በንቃት የማያገል ከነርሱ የሚለይ አይደለም።»

Bundespräsident Frank-Walter Steinmeier
ምስል Getty Images/M. Hitij

ናዚዎች በጎርጎሮሳዊው 1933 ሥልጣን ሲይዙ አሁን የጀርመን ፓርላማ የሆነው ይኽው ህንጻ ተቃጥሎ ነበር።ብዙዎች ህንጻውን ያቃጠሉት ናዚዎች ናቸው ብለው ያማናሉ። ከአደጋው በኋላ እንደገና ተሰርቶ የጀርመን ምክር ቤት ለመሆን በበቃው በዚህ ስፍራ ቅዳሜ የተፈጸመውን  የጀርመን ምክትል መራሄ መንግሥት እና የገንዘብ ሚኒስትር ኦላፍ ሾልዝ ተቀባይነት የሌለው ሲሉ በእጅጉ ኮንነውታል።«ተቀባይነት የለውም።አንዳንዶቹ አሁን የዴሞክራሲያችን ዋነኛው ምልክት በሆነው በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡንደስታግ ህንጻ ፊት ለፊት ከዘመናዊው ዴሞክራሲያችን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን ያለፈውን መጥፎ የጭለማ ዘመን ባንዲራዎች ሰቅሏል።እነዚህ ሰዎች ለህንጻው የሚገባውን  ክብር ለመስጠት እምቢተኛ  ብቻ አይደሉም፤ይልቁንም በጀርመን ታሪክ ውስጥ ያሉ መጥፎ ጊዜዎችን እያስታወሱንም ነው።» 
በኮቪድ 19 ምክንያት በጀርመን የተጣሉ ክለከላዎችን በመቃወም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ከተፈጸመው  ከዚህ ድርጊት በስተጀርባ ቀኝ ጽንፈኛ አቋም ያላቸው ፓርቲዎችና ግለሰቦች እንዳሉበት ተደርሶበታል ይላል ይልማ ቀኝ ጽንፈኞች ከበስተጀርባ እንደሚገኙባቸው የተነገሩት የቅዳሜ ዓይነቶቹ ሰልፎች አሁን ተደጋግመው የሚካሄዱበት ምክንያት በኮሮና ምክንያት የጣለው ክልከላ ሳይሆን ሰበቡ ሌላ ነው ይላል ይልማ።
በጀርመን ሆኖ የማያውቀው  የጀርመን ምክርቤትን ጥሶ ለመግባት መሞከር ልዩ ትኩረት ስቧል።ይልማ እንደሚለው በኮሮና ክልከላ ሰበብ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ኃይል የተቀላቀለበት ሰልፍ ቢያካሂዱም በጥናት እንደተረጋገጠው አብዛኛው ህዝብ የጀርመን መንግሥት በሽታውን ለመቆጣጠር የወሰደው እርምጃ ደጋፊ ነው። 

Deutschland Berlin | Coronavirus | Protest gegen Maßnahmen, Flaggen
ምስል picture-alliance/Sulupress.de

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ