1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአደአ በርጋ ጥቃት የኢንጪኒ ከተማ ባለሥልጣን እና የጸጥታ አስከባሪዎችን ጨምሮ ሰዎች ተገደሉ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 29 2016

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አደኣ በርጋ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት የኢንጪኒ ከተማ ባለሥልጣን እና የጸጥታ አስከባሪዎችን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። የሰባት ሰዎች አስከሬን ዛሬ ጠዋት መገኘቱን የተናገሩት የከተማው ነዋሪ ማረሚያ ቤት ተሰብሮ እስረኞች መለቀቃቸውን ገልጸዋል

https://p.dw.com/p/4ZyGj
ኦሮሚያ ክልል
በኦሮሚያ ክልል በበረታው ግጭት በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰዎች ለአሰቃቂ ጥቃት ተጋልጠዋል። ምስል Seyoum Getu/DW

በአደአ በርጋ ጥቃት የኢንጪኒ ከተማ ባለሥልጣን እና የጸጥታ አስከባሪዎችን ጨምሮ ሰዎች ተገደሉ

ለደህንነታቸው በመስጋት ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በአደአ በርጋ የእንጭኒ ከተማ ነዋሪ ህዳር 28 ቀን ለ29 ቀን 2016 ዓ.ም. አጥቢያ ከሌሊቱ ስድስት ሰኣት ጀምሮ በተፈጸመ ጥቃት የወረዳው ማረሚያ ቤት ተሰብሮ እስረኞች መለቀቃቸውን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በታጣቂዎቹ ጥቃት የከተማዋ አስተዳዳሪን ጨምሮ የሰዎች ህይወት ማለፉንም አመልክተዋል። “በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንዳለ ተለቀዋል። ብርሃኑ ሃብትዬ የተባሉ የከተማዋ አስተዳዳሪም ተገድለዋል፡፡ በተለያዩ ጥበቃ ስራ የሚሰሩ እንዲሁም በማረሚያ ቤት ጥበቃ ላይ ነበሩ የተባሉ ፖሊሶችም መገደላቸውን ሰምተናል” ሲሉ ተናግረዋል። 

ቅዳሜ ጠዋት በከተማው “ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ወጥተው አስከረን እየሰበሰቡ ነው፡፡ ቢያንስ ወደ ሰባት አስከሬን ተገኝተዋል፡፡ የተጎዱትም ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ በግምት ከእኩለ ሌሊት ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስ ሰባት ሰዓት ሰምተን የማናውቅ አይነት የተኩስ እሩምታ ስንሰማ ነው ያደርነው” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

የሰላማዊ ሰዎች ግድያ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ

አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላኛውም ነዋሪ በወረዳው የፖሊስ ጣቢያ ላይም ጥቃት መድረሱን አመልክተዋል፡፡ “ታውቃለህ በቃ የወረዳው መሳሪያ ግምጃ ቤትም ተሰብሯል መባሉን ጠዋት ሰምተናል፡፡ ሲንቄ ባክ ላይም ከፍተኛ የመሰባበር ጉዳት ደርሷል፡፡ ሌሎች ባንኮች ግን ምንም አልሆኑም፡፡ ታጣቂዎቹ በያቅጣጫው ወደ ከተማው መግባታቸው ነው የተሰማው፡፡ እኛ ወጥተን ማየት ፈጽሞ የማይታሰብ ብሆንም ጠዋት እንደሰማነው ቁጥራቸውም በሺዎች የሚቆጠሩ ነው ተብሏል፡፡ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ አንድ ከታጣቂዎች የሞተ ሰው ግን አስከረኑ እስከ ከሰኣት አልተነሳም፡፡ እኛ ጠዋት እንደተመለከትነው እስካሁን ሰባት አስከሬን ቆጥረናል” ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ
በአደአ በርጋ በተፈጸመው ጥቃት ላይ ዶይቼ ቬለ ከኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ምስል Seyoum Getu/DW

ሌላኛዋ ለደህንነታቸው የሰጉና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አስተያየት ሰጪም ሃሳባቸውን ቀጠሉ፡ “ታጣቂዎቹ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንደመሆኑ በከተማው ውስጥ በነበሩ የመንግስት ጸጥታ ሃይል ሚመለሱ አይመስልም፡፡ አሁን ከቤት ለመውጣትም ሰግተናል፡፡ ወንድ ወንዱ ብቻ እየወጣ የሞቱትን ማንሳት ለቅሶ መድረስ ነው ያለው፡፡ ከተማዋ ጸጥ ብላለች፡፡ ሱቆችን ጨምሮ ምንም የተከፈተ ነገርም የለም” ይላሉ፡፡

በወረዳው አጋጥሟል የተባለውን የጸጥታ ችግር በተመለከተ ዶይቼ ቬለ ለወረዳው ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ፋና ረጋሳ ብደውልም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ትረቱ አልሰመረም፡፡ ለኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛም ደውለን ስልካቸው አይነሳም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ ለኦሮሚያው ተፋላሚ ኃሎች ግልጽ ደብዳቤ መጻፋቸውን የገለጹት መቀመጫቸውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረጉ 23 የኦሮሞ ማህበረሰብ ድርጅቶች በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ሶስተኛ ዙር የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

በኦሮሚያ ያላቧራው ግጭት ላለፉት አምስት ዓመታት የሚታይ ቀውስ አስከትሎ በርካታ ውድመቶችን ፈጥሯል ያለው የማህበረሰብ ድርጅቶቹ ጥሪ፤ ተፋላሚ ኃይሎቹ ሰላምን ቀዳሚው አማራጭ አድርገው ዳግም ወደዚያው እንዲመለሱ በአጽእኖት ጠይቋል፡፡ የኦሮሞ ሌጋሲ ሊዴርሺፕ እና አድቮኬሲ ማህበር፣ የኦሮሞ ሙያተኞች ቡድንእና የኦሮሞ ድጋፍ ቡድን ጨምሮ 23 የኦሮሞ ማህበረሰብ ማህበራት የሰላም ንግግር ዳግም በአስቸኳይ እንዲጀምር እና እውነተኛ ድርድር ተደርጎ የአምስት ዓመታቱ ጦርነት እንዲያበቃ ተጠይቋል፡፡

ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የኦነሰ ድርድር ክሽፈት

ሴና ጅንጅሞ ደብዳቤውን ከጻፉት የኦሮሞ ሌጋሲ ሊዴርሺፕ እና አድቮኬሲ ማህበር (OLLA) ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ድርጅታቸው ላለፉት ሶስት ዓመታት የኦሮሚያው ቀውስ እልባት እንዲያገኝ በርካታ በሮችን ስንቆሰቁስ ነበር የሚሉት ሴና፤ በተለይም ከዚህ አንጻር ከአሜሪካ መንግስት ጋር ላለፉት 1 ዓመት ተኩል ገደማ ጥሩ ግንኙነት መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡ የድርጅታቸው እና ሰሞኑን በጋራ ሆነው የሰላም ጥያቄ ደብዳቤ የጻፉት የማህበረሰብ ድርጅቶቹ ዋና ዓለማ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) በአነስቸኳይ ለሶስተኛ ዙር የሰላም ስምምነት ተቀምጠው ቢያንስ የተውክስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካርታ
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የበረታው ግጭት እስካሁን መፍትሔ አላገኘም።

“ቢያስ ሌላ እንኳን ባይሆን ጦርነት አቁመን ውይይት መቀጠል አለብን የሚል መግባባት ላይ እንዲደርሱ ነው የጠየቅነው፡፡ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ለኦሮሞ  ነው የምሰራው የምሟገቱ ይላሉ፡፡ ግን ከማንም በላይ የኦሮሞ ህዝብ የዓለም ጆሮ ተነፍጎ መከራ እያሳለፈ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ነው ሰፊ ውይይቱ ስለ 100 እና 50 ዓመታት የፖለቲካ ችግር ላይ የሚያውጠነጥን ሳይሆን ቀዳሚ ተግባሩ ጦርነት ማቆም ላይ መስማማት አለባቸው የሚል ነው የደብዳቤው መልእክት፡፡ ለዚህ ደግሞ እርቁ እውን እንዲሆን የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ በሮችን እየቆሰቆስን ነው፡፡”

የደብዳቤው ዝርዝር ጉዳይ ለህዝብ ሙሉ በሙሉ ክፍት ባይሆንም በደብዳቤው ለሁለቱ አካላት ሰፊ ጉዳዮች መጠቀሳቸውን ያነሱት ሴና፤ ውይይቱ በሂደት ሌሎች ተዋናዮችን ማካተት እንዳለበትና ለጊዜው ግን አንገብጋቢ በሆነው የተውክስ አቁም ላይ መተኮር እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

“በኦሮሞ ትግል ውስጥ የተሳተፈው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብቻ አይደለም፡፡ ትግሉ ለዓመታት እንደመደረጉ ውይይቱም መስፋት አለበት፡፡ ግን አሁን ሰው እያለቀ ስለሆነ ጦርነት እንዴት እናቁም በሚለው ጉዳይ ብቻ ተወያዩ ነው ያልነው፡፡ ድርድሩም በሚካሄድበት ለአሜሪካ እና ስዊድን መንግስታት እንዲሁም ለኢጋድ በጻፍነው ደብዳቤ ሌሎች ተዋናዮችም በውይይቱ ብሳተፉ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣ ይሆናል ብለን ጠይቀናል” ብለዋል። 

የጻፋችሁት ደብዳቤ ተሰሚነት ኖረዋል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ሴና ጅንጅሞ “እንደዛ ብየ ነው የማስበው፡፡ አሁን ጥሪውን ያቀረቡ የማህበረሰብ አባላት እኮ ላለፉት ዓመታት ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም ጭምር ድምጽ ሲሆኑ የቆዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ የህዝቡን ድምጽ ካልሰማ ለማነው የሚታገለው፤ አገር ውስጥ ያለው ሰው እኮ በግራም በቀኝም ባለበት ስጋት ድምጹን ማሰማት አይችልም፡፡ ስለዚህ ሁለቱም አካላት የግድ ለዚህ ደብዳቤ መልስ መስጠት አለባቸው ብለን እናስባለን” ሲሉ መልሰዋል። 

ይሁንና እስካሁን ለደብዳቤው የተሰጠ ምላሽ በሁለቱም ተፋላሚዎች አለመሰማቱን አስረድተው መገናኛ ብዙሃን ለሁለቱም ወገኖች ትያቄ ብያቀርብ ብለዋል፡፡ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብም በደብዳቤው የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ተጠቅሶ ወደ ውይይቱ መመለስ አስፈላጊነቱ የጎላ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በሙያቸው ሳይንትስት የሆኑና በማህበረሰብ ማህበራቱ ውስጥ ተሳትፎ እነደሚያደርጉ የገለጹት ዶ/ር ናርዶስ ጣሰው በበኩላቸው ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት ሁሉም ሰው ተስፋ የጣለበት የተፋላሚዎቹ ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር ያለ አውንታዊ ደምዳሜ ማለቁ አሳዛኝ ነበር ነው ያሉት፡፡ “በጦርነቱ ሂደት ሰው በጣም ተጎድቷል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በየቦታው ወጥቶ ማረስና ልጁን ማስተማር አልቻለም፡፡ በመሆኑም የችግሩን ስፋት አይተው ወደ ሶስተኛ ዙር ድርድር እንዲገቡ ነው እኛ ተጽእኖ ለማድረግ የሞከርነው” ብለዋል፡፡

የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሰላም ንግግር ያለውጤት መቋረጥ አስግቷቸዋል

ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ስለደብዳቤው እና የሶስተኛ ዙር ሰላም ስምምነት መጀመር አለመጀመር ላይ ያሉት ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እና መንግስት ሸነ በሚል በሽብርተኝነት የፈረጀው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በቅርቡ በታንዛንያ ያደረጉት የሰላም ስምምነት ጥረት መክሸፉን ተከትሎ ግን በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች ግጭቶቹ እንደ ቀጠሉ ናቸው፡፡

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ