1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና በሰሜን ሽዋ ዞኖች ግጭት አለ መባሉ

ማክሰኞ፣ ጥር 16 2015

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች በየጊዜው በሚነሱ ግጭቶች የሰው ሕይወት ሲጠፋ ቆይቷል በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረትም ወድሟል፣ በሁለቱ አስተዳደሮች አመራሮችና በህዝቡ ጥረት ችግሮች ተወግደው ባለፉት ጥቂት ወራት እፎይታ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ሰሞኑን ደግሞ ችግሩ አገርሽቶ በርካቶች ተገድለዋል።

https://p.dw.com/p/4Me2M
Äthiopien Stadt Debre Sina
ምስል Eshete Bekele/DW

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሕረሰብ አስተዳደርና በሰሜን ሽዋ በግጭት ወደ 30 ገደማ ሰዎች መገደላቸውን

ምክንያቱ በውል ባልታወቀ መነሻ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጂሌ ጥሙጋ ወረዳና በዚሁ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወትና ኤፍራታና ግድም ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌዎች በታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ገልፀዋል፣ ከሁለቱም በኩል 30 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል  ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች በየጊዜው በተለያዩ ምክንያቶች በሚነሱ ግጭቶች የሰው ሕይወት ሲጠፋ ቆይቷል በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረትም ወድሟል፣ በሁለቱ አስተዳደሮች አመራሮችና በህዝቡ ጥረት ችግሮች ተወግደው ባለፉት ጥቂት ወራት እፎይታ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ሰሞኑን ደግሞ ችግሩ አገርሽቶ በርካቶች መገደላቸውን ከስፋራው የደረሱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ የችግሩን መነሻ ከኦሮሞ ብሔረሰብ የተሸገሩ ታጣቂዎች በአማራ ልዩ ኃይል ላይ ጥቃት መክፈታቸው ነው ይላሉ፡፡ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የከሚሴ ከተማ ነዋሪ ደግሞ ምክንያቱን አንድ ለመፈተሸ ያልፈለገ ሰው እንዲፈተሸ ሲጠየቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በተተኮሰ ጥይት የአንድ ኦሮሞ ነዋሪ ቤት ጉዳት በመድረሱ መነሻው ይህ ነው ይላሉ፣ በነበረው  ውጊያ ቁጥሩ ያልታወቀ ብዙ ሰው መገደሉንም ከደረሳቸው መረጃ ተነስተው ተናግረዋል፡፡

ውጊያ ባለበት የሰሜን ሸዋ ዞን ጀጀባ ከሚባል ቦታ በኬላ ጥበቃ ላይ ያሉ እማኝ አሁንም ሁኔታው እጅግ አስፈሪ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን በሰሜን ሸዋ በኩል 18 ሰዎች መመገደላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ቀኑ 7 ሰዓት ተኩል ድረስ የሁለቱን ዞኖች ወረዳዎች በሚያዋስኑ ጆበሀ፣ ጀጋኖ፣ ጀጀበ፣ ኩሪ ብሪ፣ አለና፣አጣዬ፣ ጃዋ፣ በጤ ውጊያ መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት በአካባቢዎቹ የነበረው ግጭት ተወግዶና ሰላም ሰፍኖ ሁለቱም ብሔረሰቦች (የአማራና ኦሮሞ) በጋራ ሲገበያዩ እንደነበር የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ይህን የማይፈልጉ አካላት ችግሩን እንደገና እንዲቀሰቀስ አድርገዋል ሲሉ ከስሰዋል፡፡ 

ይህ ዘገባ እየተጠናቀረ ባለበት ሰዓት የሰሜን ሸዋ ከተማ የሆነችው አጣዬ በከባድ መሳሪያ እየተደበደበች እንደሆነ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንድ የሰንበቴ ከተማ ነዋሪ በኦሮሞ ብሔረሰብ በኩል ህፃናትን ጨምሮ የ11 ሰዎች ቀብር መፈፀሙንና በሶስት ቀበሌዎች በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለጉዳዩ ከክልልና ከሁለቱ የዞን የስራ ኃላፊዎች ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት ስልክ በመዘጋቱ አሊያም መነሳት ባለመቻሉ አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር 

ታምራት ዲንሳ