1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ብሔራዊ ባንክ ወለድ ያለበትን ብድር በተመለከተ የጻፈው ደብዳቤ የሕጋዊነት ጥያቄ ተነሳበት

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2016

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት “የወለድ ክፍያ ያለበትን ብድር” ውል እንዳያዋውል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ባለሙያዎች ከ12% ያልበለጠ ወለድ የሚከፈልበት ብድር ከሚፈቅደው የፍትሐ ብሔር አንቀጽ እንደሚጋጭ ይሞግታሉ። ብድር ፈላጊዎች ሕጋዊ አማራጭ ሲዘጋባቸው ወደ አራጣ ሊገፋቸው እንደሚችል ባለሙያዎች ሥጋት አላቸው

https://p.dw.com/p/4YIDK
የኢትዮጵያ ብር እና ሣንቲም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “የወለድ ክፍያ ያለበትን ብድር” በተመለከተ ለሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት የጻፈው ደብዳቤ የሕጋዊነት ጥያቄ ተነስቶበታል። ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የሕጋዊነት ጥያቄ የተነሳበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “የወለድ ክፍያ ያለበትን ብድር” ውል እንዳያዋውል ለፌድራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት የጻፈው ደብዳቤ በባለሙያዎች የሕጋዊነት ጥያቄ ተነስቶበታል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ከፍትሐ ብሔር እና ከሀገሪቱ ንግድ ሕግ የሚቃረን እንደሆነ ይሞግታሉ።

ደብዳቤው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እና ዋና ኤኮኖሚስት ፈቃዱ ደግፌ ፊርማ መስከረም 26 ቀን 2016 የተጻፈ ነው። ደብዳቤው “ግለሰቦች እና ወይም ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ ያሉ የንግድ ድርጅቶች በመካከላቸው የሚያደርጉትን የወለድ ክፍያ ያለበትን ብድር” የፌድራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ማዋዋል እንደሚችል እና እንደማይችል ለብሔራዊ ባንክ ላቀረበው ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ ነው። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፌድራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት “ማንኛውም የወለድ ክፍያ ያለበትን የብድር ውል ማዋዋል እንደሌለበት በአጽንዖት” አሳስቧል።

“በብድር መልክ ገንዘብ መሰብሰብ እና የብድር ተመን አውጥቶ በወለድ ማበደር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው የፋይናስን ተቋማት” ብቻ ሥራ እንደሆነ ይኸው ደብዳቤ ያትታል። የሕግ ባለሙያው አቶ ጸጋአምላክ ሰለሞን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “ሰርኩላር ብድር የሚለውን ሐሳብ ሳይሆን የከለከለው፤ እነዚህ ብድሮች ያለ ምንም ወለድ በነጻ ድርጅት ለሌላ ድርጅት ወይም ባለ አክሲዮን ለድርጅት እንዲያበድር ግምት ይወስዳል” ሲሉ ይናገራሉ።

ደብዳቤው አበዳሪ “ማንኛውም አይነት ኤኮኖሚያዊ ጥቅም” ሳይኖረው ያበድራል የሚል ግምት እንደሚወስድ የገለጹት ጸጋአምላክ ሰለሞን እና ጓደኞቻቸው የተባለው የሕግ ቢሮ መሥራች የሆኑት የሕግ ባለሙያ “ለእኔ የተለያዩ ሰዎች በእንደዚህ አይነት መልኩ ሊበዳደሩ አይችሉም። ወይ ይኸን ብድር እያበደረ ያለው ቤተሰብ ለቤተሰብ ነው፤ ወይም ደግሞ የራስ ድርጅት ለራስ ድርጅት ያለ ምንም ኤኮኖሚያዊ ጥቅም እየተበዳደሩ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ ባንኮች ይታያሉ
“በብድር መልክ ገንዘብ መሰብሰብ እና የብድር ተመን አውጥቶ በወለድ ማበደር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው የፋይናስን ተቋማት” ብቻ ሥራ እንደሆነ ለሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት የተጻፈው ደብዳቤ ያትታል።ምስል Eshete Bekele/DW

 

ደብዳቤው “አንድ ግለሰብ ለሌላ ግለሰብ ወለድ ያለው ብድር ቢያበድር ክልክል ነው፤ ድርጅት ለድርጅት ወለድ ያለው ብድር ቢያበድር ክልክል ነው የሚል ይዘት” እንዳለው የገለጹት የሕግ ባለሙያው አቶ ሐዋዝ መራዊ በበኩላቸው “የሕግ ውጤት ሊኖረው የማይገባ” እንደሆነ ይሞግታሉ።

አንድ ኩባንያ የፋይናንስ ችግር ወይም የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲገጥመው ከእህት ኩባንያ በወለድ እንደሚበደር የገለጹት አቶ ሐዋዝ “ባለ አክሲዮኖች ለድርጅቶቻቸው ብድር ያበድራሉ፤ ግለሰቦች ለግለሰቦች፤ ቢዝነሶች ለቢዝነሶች ብድር ያበድራሉ። ሲያበድሩ የተወሰነ ወለድ ያስቀምጡበታል” ሲሉ እስካሁን ያለውን አሠራር አስረድተዋል።

በውሳኔው ላይ የሚነሱት የሕጋዊነት ጥያቄዎች ምንድናቸው?

“ከ12 በመቶ አይብለጥ እንጂ ወለድ ማስቀመጣቸው በፍትሐ ብሔር ሕጉ ሕጋዊ የሆነ ተግባር ነው” የሚሉት አቶ ሐዋዝ “እንደዚህ አይነት ወለድ ደግሞ አበዳሪ ድርጅት ወለዱን ሲከፍል በወጪነት ወይም በተቀናሽነት የሚያዝለት ወጪ ነው” በማለት በታክስ ሕግ ጭምር የተፈቀደ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፌድራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት የጻፈው ደብዳቤ አቶ ጸጋአምላክ እንደሚሉት “አንድ ሰው ለሌላ ሰው ብድር በወለድ አበደረ ማለት የባንክ አገልግሎትን ያለ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እየሰጠ ነው” ከሚል ድምዳሜ የደረሰ ነው። የሕግ ባለሙያው “ይኸ አተረጓጎም ግን ልክ አይደለም” የሚል አቋም አላቸው።

በኢትዮጵያ ሕግ የባንክ አገልግሎት ብዙ ነገሮችን ያካተተ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ጸጋአምላክ “ከዚያ ውስጥ አንደኛው ብድር ሰጥቶ ወለድ እየሰበሰበ ሥራውን መስራት የባንክ ሥራ ዋና መሠረት ነው። ባንኮች ያንን ገንዘብ ከየት ያመጡታል ሲባል ተቀማጭ መሰብሰብ የሚለው ሌላኛውን የባንክ ሥራ ትርጉም ሕጉ ላይ አለ። እዚህ ላይ ስንመጣ ግን ግለሰቦች ብድር የሚያበድሩት የራሳቸውን ገንዘብ ተጠቅመው ነው እንጂ አንደኛ ከግለሰቦች ሰብስበው አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ብር ባለ ሁለት መቶ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጻፈው ደብዳቤ “አንድ ግለሰብ ለሌላ ግለሰብ ወለድ ያለው ብድር ቢያበድር ክልክል ነው፤ ድርጅት ለድርጅት ወለድ ያለው ብድር ቢያበድር ክልክል ነው የሚል ይዘት” እንዳለው የሕግ ባለሙያው አቶ ሐዋዝ መራዊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ “አንድ ሥራ ፈቃድ ሊያገኝ የሚገባው እና ልክ እንደ ቢዝነስ ሊቆጠር የሚችለው አንድ ሰው ሙያዬ ብሎ ሥራውን ሲሰራው ነው” የሚሉት አቶ ሐዋዝ በበኩላቸው ብድር መስጠት ብቻውን የባንክ ሥራ ላይ እንደመሰማራት ሊቆጠር እንደማይገባ ተናግረዋል። “አንድ ሰው ገቢ ለማግኘት ብሎ ቀጣይነት ባለው መልኩ የማበደር ሥራ ላይ ሲሰማራ ነው የባንክን ሥራ ሰራ ሊባል የሚችለው እንጂ ወለዱ ከ12 በመቶ እስካልበለጠ ድረስ በፍትሐ ብሔር ሕጋችን የማበደር ተግባር የተፈቀደ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የወለድ መጠኑ “ከ12 በመቶ የበለጠ እንደሆነ የአራጣ ሥራ ስለሚሆን የወንጀል ኃላፊነትን የሚያስከትል ተግባር ነው። በተደጋጋሚም ካበደረ አንድ ሰው ወይም ሙያዬ ብሎ የሚሰራው ሥራ ከሆነ ያለ ፈቃድ የባንክን ሥራ መስራት ስለሚሆን የወንጀል ኃላፊነትን የሚያስከትል ተግባር ነው” የሚሉት አቶ ሐዋዝ “አልፎ አልፎ በአንድ በመቶም ሊሆን ይችላል፤ አስራ አንድ በመቶም ሊሆን ይችላል፤ አስራ ሁለት በመቶም ሊሆን ይችላል ማበደር ግን የተከለከለ ተግባር አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።የፓን አፍሪካ ክፍያ ሥርዓት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የኢትዮጵያን አባልነት ይጠባበቃሉ

ደብዳቤው ከፍትሐ ብሔር እና የንግድ ሕግ እንደሚቃረን የጠቀሱት አቶ ሐዋዝ “ብሔራዊ ባንክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣውን በደብዳቤ ሊሽረው አይችልም፤ ከሻረውም ደግሞ ይኸ ደብዳቤ ዋጋ ቢስ ሊሆን ይገባል” የሚል ክርክር በሕግ ባለሙያዎች እና የቢዝነስ ማኅበረሰቡ ዘንድ እንዳለ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የፌድራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ወለድ የሚከፈልባቸው ብድሮች እንዳያዋውል የብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ ያሳስባል። ይኸ ማሳሰቢያ በኢትዮጵያ ፍትሐ ብሔር በተፈቀደው መሠረት ከ12 በመቶ ያልበለጠ ወለድ የሚከፈልበት ብድር ስለማበደር የሚለው ነገር የለም። አቶ ሐዋዝ ግን  “በፍትሐ ብሔር ሕጋችን ግለሰቦችም ሆኑ ሌሎች ተቋማት ማበደር እንደሚችሉ ተደንግጓል። በሕጉ ላይ የተቀመጠው ገደብ የወለዱ መጠን ከ12 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚል ነው” ሲሉ የብሔራዊ ባንክን ውሳኔ ያጠይቃሉ።

በኢትዮጵያ ካልሲ የሚያመርት ጀማሪ ኩባንያ
ውሳኔው መያዣ ከሚጠይቁ ባንኮች ብድር ማግኘት የማይችሉ ጀማሪ ኩባንያዎችን አማራጭ ሊያሳጣ እንደሚችል የሕግ ባለሙያዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይኸ በአንጻሩ ሕጋዊ አማራጭ የተዘጋባቸውን ኩባንያዎች አራጣን ወደ መሰሉ ሕገ ወጥ መንገዶች ሊገፋ እንደሚችል ሥጋት አለምስል Addis Alemayehou

አቶ ጸጋአምላክ በፍትሐ ብሔር ሕግ “ማንኛውም ግለሰብ ከ12 በመቶ በላይ የወለድ ምጣኔ ማስቀመጥ አይችልም እንጂ፤ ከ12 በመቶ እና ከዚያ በታች በሆነ ወለድ ማበደር እንደሚችል የፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ተቀምጧል” ሲሉ ከአቶ ሐዋዝ የተስማማ አስተያየት ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ በፍትሐ ብሔር የተፈቀደው ከ12 በመቶ ባልበለጠ ወለድ የማበደር አሰራር “በባንክ ሥራ አዋጅ ሙሉ በሙሉ ተሽሯል የሚል አይነት ግምት ነው የተወሰደው” የሚሉት አቶ ጸጋአምላክ “ትልቅ ስህተት ነው” የሚል አቋም አላቸው።

የፍትሐ ብሔር ሕግ “ማንኛውም ሰው የራሱን ገንዘብ ለግለሰብ ሲያበድር ያለን ግንኙነት የሚገዛ” እንደሆነ የገለጹት የጸጋአምላክ ሰለሞን እና ጓደኞቻቸው የሕግ ቢሮ መሥራች የባንክ ሥራ ሕግ በአንጻሩ ባንክ “በማንኛውም መልኩ ከሰዎች የሰበሰበውን የሕዝብ ገንዘብ ሲበድር የሚገዛበት የራሱ የሆነ ሕግ እንዳለው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ “ይኸንን ልዩነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና ግለሰቦች ወይም ማንኛም ሰው የራሱን ገንዘብ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ያለውን መብት የሚሽር ይመስለኛል” ሲሉ አቶ ጸጋአምላክ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ የግል ብድር ለሚሹ ምን ያጎድላል?

ይኸ ውሳኔ የሕግ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከተሰጣቸው የፋይናንስ ተቋማት ብድር ማግኘት የሚቸግራቸው ጀማሪ እንዲሁም አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት ገንዘብ የሚያገኙበትን ዕድል የሚያሳጣ ነው። ቀድሞም የኢትዮጵያ ባንኮች መያዣ ወዳላቸው ተበዳሪዎች በማዘንበላቸው የፋይናንስ ተደራሽነት የተገደበ እንደሆነ የሚያስታውሱት አቶ ጸጋአምላክ “ውሳኔው ለጀማሪ ቢዝነሶች ብድርን እንደ አንድ የገንዘብ ምንጭ የመጠቀም አማራጭን ያሳጣቸዋል” ሲሉ ተጽዕኖውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀድሞ እና አዲስ ዋና መሥሪያ ቤቶች
የኢትዮጵያ ባንኮች መያዣ ወዳላቸው ተበዳሪዎች በማዘንበላቸው የፋይናንስ ተደራሽነት የተገደበ እንደሆነ የሚያስታውሱት አቶ ጸጋአምላክ “ውሳኔው ለጀማሪ ቢዝነሶች ብድርን እንደ አንድ የገንዘብ ምንጭ የመጠቀም አማራጭን ያሳጣቸዋል” ሲሉ ተጽዕኖውን አስረድተዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

ከፍተኛ መዋቅራዊ የዋጋ ንረትን ለማቃለል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የሀገር ውስጥ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ” እንደሚገደብ አስታውቋል። “ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲያስተካክሉ” እንደሚደረግ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። “ኢትዮጵያ ውስጥ ብድር ማግኘት ከባድ ሆኗል” የሚሉት አቶ ሐዋዝ ይኸ በነሐሴ 2015 ይፋ የተደረገ ውሳኔ ባንኮች ካለባቸው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ጋር ተደማምሮ ለብድር አቅርቦት እክል እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የትይዩ ገበያውን ሁለተኛ ፈርጅ መቆጣጠር ይችላል?

“የውጭ ብድር ለማግኘት ብሔራዊ ባንክ መፍቀድ እና ማጽደቅ ይጠበቅበታል። አንድ ድርጅት የውጭ ብድር አግኝቶ የብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ለማግኘት በጣም ጥብቅ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለበት። ስለዚህ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ብድር ለማግኘት እጅግ ፈታኝ የሆነ ጊዜ ላይ ሆነን ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ወለድ ያለው ብድር ማበደር አይቻልም የሚባለው ነገር ጀማሪ ለሆኑ ለአነስተኛ እና መካከለኛ የቢዝነስ ተቋማት፣ ለውጭ ኢንቨስተሮች” ፈተና እንደሚሆን አስረድተዋል።

ብድር ፈላጊዎች ሕጋዊው አማራጭ ሲዘጋባቸው አራጣን ወደ መሰሉ ሕገ ወጥ መንገዶች ሊገፋቸው እንደሚችል አቶ ጸጋአምላክ ሥጋት አላቸው። “ብድርን ከወለድ ነጻ ማድረግ ተጽዕኖው ሰዎችን በሕጋዊ መንገድ ብድር ከመበዳደር ይልቅ ከመጋረጃ ጀርባ እንዲበዳደሩ ታደርጋለህ ማለት ነው። ይኸ ደግሞ ከሕግ ማዕቀፍ ውጪ ስለሆነ ብድርን ውድ ያደርገዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዘለግ ያለውን ዘገባ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ