1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሐረሪ ክልል ኮሌራን ለመከላከል የውኃ ጉድጓዶች የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ተገለጸ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 8 2016

በኢትዮጵያ 85 ወረዳዎች እስከ ጥቅምት የመጀመሪያ ሣምንት 24,700 ሰዎች በኮሌራ እንደተያዙ የተ.መ. የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ መረጃ ይጠቁማል። ወረርሽኙ ሐረሪን ጨምሮ በስምንት ክልሎች ተከስቷል። በሐረሪ ክልል የውኃ ጉድጓዶችን በማጽዳት ወረርሽኙን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የክልሉ የጤና ቢሮ አስታውቋል

https://p.dw.com/p/4Z8EZ
የሐረሪ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሒ
በሐረሪ ክልል በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ አንድ ሰው ሕይወቱ እንዳለፈ የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሒ ተናግረዋል።ምስል Mesay Teklu/DW

ኮሌራ በሐረሪ ክልል

በሀረሪ ክልል በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ ከተያዙ ሃምሳ ሰዎች አርባ ስምንቱ ታክመው መዳናቸውን፣ አንድ ሰው መሞቱን እና ሌላ አንድ ሰው በህክምና ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል ።

ለወረርሽኙ ምላሽ ለመስጠት የተለያየ የቅድመ ዝግጅት ስራ ሰርቼያለሁ ያለው የክልሉ ጤና ቢሮ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎችን ለማከም የሚያስችሉ አራት ጊዜያዊ የህክምና ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ጠቁሟል።

የወረርሽኙ መጠን ጋብ ብሎበታል በተባለው በዚህ ጊዜ ህብረተሰቡን የማስተማር እና ሌሎች የወረርሽኙን መስፋፋት መከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል ።

የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ ለሚዲያ በሰጡት መግለጫ በክልሉ በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ ከተያዙ ሃምሳ ሰዎች አርባ ስምንት ያህሉ ከበሽታው ድነው ወደ ቤት መመልሳቸውን ፣ አንድ ታማሚ ሲሞት አንዱ በህክምና ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎችን ለማከም  የሚያስችሉ ጊዜያዊ አራት የህክምና ማዕከላት መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል ።

በየአካባቢው ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውን የመፈለግ እና የማከም ስራን ጨምሮ  ህበረተሰቡ የሚገለገልባቸው የውሃ ጉድጓዶች ለወረርሽኙ መስፋፋት አስተዋፅኦ ያላቸው በመሆኑ የውሃ ጉድጓዶችን የማከም ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።

በድሬዳዋ ኮሌራ 3 ሰዎች ገደለ

በጅኔይላ ወረዳ የጅኔይላ ጤና ጣቢያ በክልሉ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የመጀመሪያው ታማሚ የተገኘበት ተቋም እንደነበር ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት የጤና ጣቢያው ኃላፊ አቶ መሀመድ ኢብራሂም በተቀመጠ የህክምና ፕሮቶኮል መሰረት ለታማሚው እና ሌሎች የበሽታው ተጠርጣሪዎች ተገቢው ህክምና መሰጠቱን ጠቅሰው በአሁን ሰዓት በወረዳው ተመሳሳይ ችግር አለመኖሩን አብራርተዋል።

ሕሙማን በጤና ተቋም
በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላከል የውኃ ጉድጓዶች የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ ነውምስል Mesay Teklu/DW

በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡን ቤት ለቤት የማስተማር ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ የገለፀችው እና በጤና ጣቢያው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዋ ሲስተር አልምፀሀይ ብርሀኑ ህብረተሰቡም እየተቀበለ እና ተግባራዊም እያደረገ ነው ብላለች። በሀረሪ ክልል የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን የሚጠቁመው ታማሚ የተገኘው ከወራት በፊት መሆኑን ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

ኮሌራ በሀረሪ ክልል

ወረርሽኙ በጀመረበት ወቅት ባይገለፅም በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው ባሳለፍነው አመት ሐምሌ ወር ላይ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ጠቁማል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ እንዳሉት ወረርሽኙ ለመጀመርያ ጊዜ ከተከሰተበት ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን  በበሽታው የተያዙት አጠቃላይ ታማሚዎች ብዛት ሃምሳ ነው። ለታማሚዎቹ በተደረገ ህክምና "አርባ ሰምንቱ የህክምና አገልግሎት አግኝተው ድነው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል ፤ አንድ ሰው አሁንም ህክምና እያገኘ ነው ያለው ። አንድ ምት ተመዝግቧል" ብለዋል።

በኮሌራ ወረርሺኝ ቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ሰዎች ሞቱ

ቢሮው የወረርሽኙን ጉዳት ለመከላከል ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ማዋቀርን ጨምሮ ግብዓት የማፈላለግ እና ሌሎች የዝግጅት ስራዎችን መስራቱን ያነሱት ኃላፊው አራት ያህል ጊዜያዊ የኮሌራ ህክምና መስጫ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

"በሽታው አጣዳፊ ከመሆኑ አንፃር በተለይ አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ በኃላ አንድና ሁለት ቀን ቤቱ ቆይቶ ወደ ህክምና የሚመጣ ከሆነ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ እና የማይድንበት ሁኔታ ሊፈጠር  ስለሚችል ህብረተሰባችን ጥንቃቄ ያድርግ" ሲሉ አቶ ያሲን መልእክት አስተላልፈዋል ።

በክልሉ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ የመጀመሪያ ታካሚ ያስተናገደው የጅኔይላ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ መሀመድ ኢብራሂም ለመጀመሪያው ታማሚም ሆነ በዚያው ዙርያ በበሽታው መያዛቸው የተጠረጠሩ ሰዎችን በማከም ድነው እንዲሄዱ ማድረጋቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ሐረር ከተማ
በሐረሪ ክልል ለተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ዋናው ምክንያት የውኃ ብክለት ነውምስል Reuters/T.Negeri

በክልሉ አንድ ወረዳ በሆነው ጅኔይላ በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት የኮሌራ ታማሚ የለም ያሉት አቶ መሀመድ እርሳቸው የሚመሩት ጤና ጣቢያ እና ባለሞያዎች ህብረተሰቡን የማስተማር ስራዎችን ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን እየሰሩ ነው ብለዋል።

የኮሌራ ወረርሽኝ በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ

ሀረሪን ጨምሮ በአጎራባች ክልሎች ወረርሽኙ መኖሩን ያነሱት አቶ መሀመድ መፍትሄ የሚሆነው  በማህበረሰቡ ዘንድ መፈጠር ያለበትን ከፍተኛ ግንዛቤ መፍጠር መሆኑን አፅንኦት ሰተዋል። "ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሽታ መኖሩን አውቆ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግ አለበት" ብለዋል።

ህብረተሰቡን ቤት ለቤት እያስተማሩ ካሉ የክልሉ  የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች አንዷ ሆና በጅኔይላ ጤና ጣቢያ እየሰራች ያለችው ሲስተር አለምፀሀይ ብርሀኑ "ህብረተሰቡ አካባቢውን በማፅዳት ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሀን በመጠቀም ፣ ምግቦችን አብስሎ በመመገብ እና ፍራፍሬዎችን አጥቦ በመጠቀም " ለበሽታው የሚጋልጡ ነገሮችን እንዲከላከል የማስገንዘብ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግራለች።

ከተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች በሚዋሰነው የሀረሪ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ጉዳት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ከጤና ባለሞያዎች የሚሰጠውን ምክር በመተግበር የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ