1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮቪድ 19 ወረርሽኝነቱ አበቃ ማለት ይቻላል?

ማክሰኞ፣ መስከረም 17 2015

ከሁለት ዓመታት በላይ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የከረመው የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ስጋት የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጋረደው ሰነባበተ። ምንም እንኳን በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የቀነሰ መሆኑ ቢነገርም ከሰው ወደሰው በመዛመት ባህሪውን ለውጦ ተባብሶ እንዳያገረሽ የሚሰጉ ግን ጥቂት አይደሉም።

https://p.dw.com/p/4HPuX
Corona Virus Welle Symbolbild
ምስል Michael Bihlmayer/CHROMORANGE/picture alliance

ጤና እና አካባቢ

በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም መነጋገሪያ የሆኑ ከህልውና ጋር የተገናኙ በርካታ ጉዳዮች ጋርደውት ስለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ብዙም ሲነገር አይሰማም። ተሐዋሲው ወረርሽኝነቱ አበቃ ማለት ይቻል ይሆን? በሚልም የሚጠይቁ ጥቂት አይደሉም። የዓለም የጤና ድርጅት ግን ባለፈው ሳምንት ይህን ለማለት ጊዜ ገና መሆኑን በይፋ አሳውቋል። 

ከሁለት ዓመታት በላይ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የከረመው የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ስጋት የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጋረደው ሰነባበተ። ምንም እንኳን በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የቀነሰ መሆኑ ቢነገርም ከሰው ወደሰው በመዛመት ባህሪውን ለውጦ ተባብሶ እንዳያገረሽ የሚሰጉ ግን ጥቂት አይደሉም። ኮቪድ 19 ከፍተኛ ስጋት መሆኑን በማሳሰብ ወረርሽኝነቱን ለዓለም ያወጀው የዓለም የጤና ድርጅት ከሰሞኑ ወረርሽኙ አብቅቷል ብሎ የሚያሳውቅበት ጊዜ ገና መሆኑን አሳውቋል። «እዚህ ኒውዮርክ በሚካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የተገኙ ሁሉ አሁን ከምን ደረጃ ላይ ደርሰናል? ወረርሽኙ አበቃ? የሚል ጥያቄ ነው የሚጠይቁት።  ባለፉት ሁለት ሳምንታት ለመገናኛ ብዙሃን ባደረግነው ገለጻ፤ ወረርሽኙ ገና አላበቃም ፤ ነገር ግን ማለቂያው እየተቃረበ መሆኑ ይታያል ብያለሁ።»

ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ባለፈው ሳምንት ከብዙዎች ለቀረበላቸው «ኮቪድ 19 ወረርሽኝነቱ አላበቃም?» ለሚለው ጥያቄ በይፋ የሰጡት ምላሽ ነው። ይኽንኑ በማንሳት ከአዲስ አበባ ያነጋገርኳቸው የውስጥ ደዌ የሳንባ እና ጽኑ ህክምና ባለሙያ ዶክተር አስቻለው ወርቁም ምንም እንኳን ተመርምረው በተሐዋሲው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ቢነገርም አሁንም ግን ወረርሽኝነቱ አበቃ ለማለት እንደማይቻል ይናገራሉ። 

Schweiz, Genf I Hauptsitz der Weltgesundheitsorganisation I WHO I Gebäude
የዓለም የጤና ድርጅትምስል Reuters/D. Balibouse

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሳምንት በፊት ነው በሀገራቸው ወረርሽኙ ማብቃቱን ለመገናኛ ብዙሃን የተናገሩት። በዩናይትድ ስቴትሷ ቨርጂኒያ ግዛት የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩን ግን የሚሉት ከእሳቸው ይለያል። «እርግጥ ነው በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ይታያል፤ ሀኪም ቤት የሚገቡትም ቁጥር ቀንሷል ግን እንደህክምና ባለሙያ ተሐዋሲው ዳግም እንዳይዛመት ስጋት አለን» ነው ያሉት። 

ባለፉት ዓመታት እንደታየው የኮሮና ተሐዋሲ ቅዝቃዜን ተከትሎ የሚስፋፋ እና የሚጠናከር አይነት ነው። በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ በአሁኑ ወቅት የመኸር ዝናብና ቅዝቃዜ እየታየ ሲሆን ከወራት በኋላ ክረምቱ እየተጠናከረ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ላይ ደግሞ የክረምቱ ወቅት ቢያበቃም ጥቅምትን ይዞ ቅዝቃዜው እንደሚበረታ ይታወቃል፤ ለዚህም «በጥቅምት አንድ አጥንት» ይላሉ አበው። ብርዱን ቅባት በመመገብ ስለመቋቋም ሲመክሩ። ዳርዳር የሚል የመሰለው የኮሮና ተሐዋሲ በዚህ ወቅት እንደከዚህ ቀደሙ ይጠናከራል የሚል ስጋት መኖሩን የህክምና ባለሙያዎቹ አጽንኦት ይሰጣሉ። እንደውም ዶክተር አስቻለው ኮቪድ የወቅት ፍርርቅ አልገታውም ነው የሚሉት።

ምንም እንኳን እንዲህ ቢሉም ከሌላው በተለየ ስጋት የሚፈጥር እንዳልሆነ ዶክተር አስቻለው አመልክተዋል። ዋናው ነገር ተገቢው ጥንቃቄ ላይ ትኩረት ማድረግ መሆኑንም ይመክራሉ። ፕሮፌሰር ያሬድም እንዲሁ ካለፉት ሁለት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት በቀጣይ ወራት የሰሜኑን ንፍቀ ክበብ የቅዝቃዜ ወራት በምታስተናግደው ዩናይትድ ስቴትስ የተሐዋሲው ስርጭት ከፍ ሊል እንደሚችል የባለሙያዎች ግምት እንዳለ ገልጸዋል።

Symbolbild Coronavirus Forschung Maske
ምስል Cheng Min/Xinhua/picture alliance

የኮሮና ተሐዋሲ መከሰትንም ሆነ የስርጭቱን ጉዳይ ከህክምና ባለሙያዎቹ በበለጠ ፖለቲከኞች በየመድረኩ ሃሳብ የሚሰነዝሩበት ሆኖ መክረሙ አወዛጋቢ ምልከታዎች እንዲመጡ ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። አሁንም ወርሽኝነቱ አበቃ በማለት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አስቀድመው በድፍረት የተናገሩት ፖለቲከኞች መሆናቸውን ልብ ይሏል። የኮሮና ታማሚዎችን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩት ፕሮፌሰር ያሬድ ግን ተሐዋሲው አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ያመለክታሉ።

በአሁኑ ጊዜ ዶክተር አስቻለው እንዳስተዋሉትም ሆነ ብዙዎች እንደሚገልጹት ለኮሮና ተሐዋሲን ለመከላከል በህዝቡ ይደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ቀርቷል። የመዘናጋቱ አካሄድ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እዚህ ጀርመንም ሆነ በሌሎች ሃገራት ይታያል። አሁንም ግን በተሐዋሲው የሚያዙም ሆነ ህመሙ የሚጠናባቸው ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። የዓለም የጤና ድርጅት ከዚህ ቀደም በተሐዋሲው በተያዙት ላይ ይደረግ የነበረው ጥብቅ እገዳም ሆነ በሀኪም ቤት ውስጥ ነጥሎ የህክምና እርዳታ የመስጠቱ አካሄድ ቀስ በቀስ እየቀረ እንዲሄድ፤ የወትሮውም የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴም ወደ ቦታው እንዲመለስ የማድረጉ ሙከራ እየታ መሆኑንም አንስተዋል ዶክተር አስቻለው።

Symbolbild Covid-19 Medizinische Makse
አፍና አፍንጫን መሸፈን ምስል Maridav/Colourbox

እዚህ ጀርመን በህዝብ መጓጓዣዎች በባቡርም ሆነ በአውቶቡስ ለመንቀሳቀስ የግድ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ያስፈልጋል። ሰዎች በሚሰበሰቡበት ስፍራም ሆነ በገበያ ቦታዎች ደግሞ በተቃራኒው የፈለጉ ሰዎች ብቻ ናቸው አፍና አንፍጫቸውን የሚሸፍኑት። እንዲህ ያለው መዘናጋት የመጣው ደግሞ አንድም ተደንግገው የነበሩ ደንቦች በመላላታቸው አንድም መገናኛ ብዙሃን ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸውን በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት እና እሱን ተከትሎ በመጣው የፍጆታ አቅርቦት እጥረት፤ የኤኮኖሚ ድቀት ላይ በማድረጋቸው መሆኑን የሚገልጹ አሉ። መዘናጋቱ በየቦታው እንደሚታይ ነው ፕሮፌሰር ያሬድ የሚናገሩት፤ ግን መዘዙ ብዙ መሆኑን ያሳስባሉ። በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ሆነ የህክምና ባለሙያዎቹ እንደገለጹት ቁጥራቸው ቢቀንስም ዛሬም በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዙና ሀኪም ቤት የሚገቡ ሰዎች አሉ። በሽታው ስጋትነቱ እስኪያበቃ ጥንቃቄ ማድረጉ ጠቃሚ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። ማብራሪያ ለመስጠት የተባበሩንን የህክምና ባለሙያዎች እናመሰግናለን። 

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ