1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ127ኛው የአድዋ ድል አከባበር በአዲስ አበባ

ሐሙስ፣ የካቲት 23 2015

127 ኛው የአድዋ ድል ክብረ በዓል በብሔራዊ ደረጃ «አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት» በሚሉ መሪ ሀሳቦች ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል። ሆኖም በበዓሉ አክባሪዎች እና በሥነ ሥርዓት አስከባሪ ፖሊሶች መካከል ፍጥጫ መፈጠሩ ተሰምቷል። ፖሊሶችም የበዓሉን ታዳሚ ለመበተን አስለቃሽ ጢስ ሲተኩሱና ድብደባ ሲፈጽሙ ታይተዋል።

https://p.dw.com/p/4OAnG
Äthiopien Addis Abeba Adwa Sieg
ምስል Solomon Muche/DW

የ127ኛው የአድዋ ድል በአል

 

127 ኛው የአድዋ ድል ክብረ በዓል በብሔራዊ ደረጃ «አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት» በሚሉ መሪ ሀሳቦች  ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል። ፕሬዝደንት ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ ንጋት ላይ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አደባባይ በመገኘት የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። ሆኖም ይህ ከሆነ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን በበዓሉ አክባሪዎች እና በሥነ ሥርዓት አስከባሪ ፖሊሶች መካከል ፍጥጫ መፈጠሩ ተሰምቷል። ፖሊሶችም የበዓሉን ታዳሚ ለመበተን አስለቃሽ ጢስ ሲተኩሱና ድብደባ ሲፈጽሙ ታይተዋል።

የመስቀል አደባባዩ አከባበር በጀት እና ሄሊኮፕተሮች ጭምር የታገዘ ላቅ ያለ ወታደራዊ ትዕይንት ቀርቧል። በዚህም  የተለያዩ ተቋማት መሪዎች ንግግሮች የተደረጉ ሲሆን ፕሬዝደንቷም «የአድዋ ድል ለነፃነት ፣ ለሉዓላዊነት፣ ከጭቆና ለመላቀቅ ለሚታገሉ ሁሉ የአንድነት ፣ የመተባበር እና የማሸነፍ ተምሳሌት ነው» ብለዋል።

ዛሬ ከንጋቱ ጀምሮ በፖሊስ ማርሽ ቡድን ታጅቦ በምኒልክ አደባባይ የተከበረው 127ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ ኢትዮጵያዊያን የጣልያን ወራሪዎችን አድዋ ላይ ድል ሲመቱ የበረውን ሁኔታ ለማስታወስ ታዳሚዎች በልዩ ልዩ አልባሳት ተውበው፣ በኅብር ዝማሬዎች ደምቀው፣ በፉከራና በመወድስ ልዩ ልዩ ትርኢቶችን አሳይተዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ከዚህ በፊት በነበሩ የአድዋ ድል መታሰቢያ ክብረ በዓላት ላይ ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ ወይም እስከ አራት ሰዓት ገደማ ዝግ ሆኖ ይቆይ የነበረው አደባባዩ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከመሆኑ በፊት ለተሽከርካሪ ክፍት ተደርጓል። ይህም ብዙዎችን አስከፍቷል። ይህንን ተከትሎ በበዓሉ አክባሪዎች እና በሥነ ሥርዓት አስከባሪ ፖሊሶች መካከል ፍጥጫ ተፈጥሮ ታይቷል።
ቆይቶም ፖሊሶች የበዓሉን ታዳሚ ለመበተን ኃይል በመጠቀም በተለይ ወደ ሰሜን ማዘጋጃ መውጫ ባለው መንገድ ላይ የነበሩ ሰዎችን ደብድበዋል፤ አስለቃሽ ጭስም ተኩሰዋል። በዚህም የተጎዱ እና ራሳቸውን ስተው የወደቁ ሰዎችንም ተመልክተናል።

Äthiopien Addis Abeba Adwa Sieg
ለ127ኛው የአድዋ ድል ክብረ በአል በምኒሊክ አደባባይ የተገኙ ወጣቶች በከፊልምስል Solomon Muche/DW

ክብረ በዓሉ በአድዋ ድልድይ እና በመስቀል አደባባይም ተከብሯል። አንድነትን የሚሰብኩ ድምጾች እና ሀሳቦች ለቃለ መጠይቅ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ዘንድ ሁሉ የተነሱ ናቸው።
መስቀል አደባባይ ላይ በነበረው አከባበር ላይ በጀት እና ሄሊኮፕተሮች ጭምር የታገዙ ላቅ ያሉ ወታደራዊ ትዕይንቶች ቀርበዋል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝደንት ፣ የመከላከያ ሠራዊት ፊልድ ማርሻል እና የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ንግግር አድርገዋል። ፕሬዝዳንት ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ «ዓለም ያከበረውን ፣ ያደነቀውን እኛም ከዚያም በላይ ልናከብረው ይገባል» ብለዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ