1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራዩ ጦርነት እና የነዋሪዎች የሰላም ጥሪ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 2 2015

አንድ የሽረ ከተማ ነዋሪ ከከተማዋ ወደ ምዕራብና ሰሜን አቅጣጫ ባሉ የደደቢት እና የአድያቦ አካባቢዎች "ከባድ» ያሉት ጦርነት" መቀጠሉን ተናግረዋል። ካለፈው ሐሙስ ወዲህ ባሉ ተከታታይ ቀናት ብዙሀንን ለጉዳት የዳረጉ የአየር ላይ ጥቃቶች በሽረ ከተማ እና አካባቢ መፈፀማቸውንም ገልፀውልናል።

https://p.dw.com/p/4I5QH
ትግራይን የሚያሳየው የኢትዮጵያ ካርታ
የኢትዮጵያ ካርታ

የትግራዩ ጦርነት እና የነዋሪዎች የሰላም ጥሪ

በነሐሴ አጋማሽ ዳግም በተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጲያው ጦርነት ምክንያት፣የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውና መፈናቀላቸው ቀጥሏል። ጦርነቱ በተለይም ትግራይን ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑ የሰሜን ምዕራብ እና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ከአካባቢዎቹ ሸሽተው መቀሌ ደርሰዋል የተባሉ ነዋሪዎችና የተለያዩ ምንጮች ያስረዳሉ። በሌላ በኩል ጦርነቱ በሰላማዊ ንመንገድ እንዲቆም የሚጠይቁም አሉ ። የሽረ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና በቪሳት ኢንተርኔት እንደሚያገኙ የገለፁልን ግለሰብ ከከተማዋ ወደ ምዕራብና ሰሜን አቅጣጫ ባሉ  የደደቢት እና የአድያቦ አካባቢዎች "ከባድ» ያሉት ጦርነት" እየቀጠለ ስለመሆኑ የተናገሩ ሲሆን፣ ካለፈው ሳምንት ዕለተ ሐሙስ ወዲህ ባሉ ተከታታይ ቀናት ደግሞ ብዙሀንን ለጉዳት የዳረጉ የአየር ላይ ጥቃቶች በሽረ ከተማ እና አካባቢ መፈፀማቸው ገልፀውልናል። በመቐለ የአየር ጥቃቶችን በመስጋት በገበያዎች፣ ቤተእምነቶች እና ሌሎች ሁነቶች የህዝብ መሰባሰብ ቀንሷል፣ ዛሬ ጨምሮ በየቀኑ የፀረ አውሮፕላን ተኩስ በከተማዋ ይሰማል፣ ከጦርነቱ መፋፋም ጋር ተያይዞ በተለይም ወጣቶች ወደ ትግራይ ሐይሎች እንዲቀላቀሉ በየቀበሌው ቅስቀሳ ይደረጋል። በሌላው የትግራይ ክፍል ያለው ሁኔታ ለማወቅ የስልክ ይሁን ሌላ የግንኙነት መስመር በመላው ትግራይ ባለመኖሩ ዝርዝር መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል። 

ባለፈው እሁድ ከዓዲግራት ተነስተው መቐለ መምጣታቸው የነገሩን ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የዓይንእማኝ፣ ዓዲግራት በለቀቁበት እሁድ ዕለት ከተማዋ ከሰሜን አቅጣጫ በሚተኮስ ከባድ መሣርያ ስትደበደብ ውላለች ብለዋል። እንደ የዓይንእማኙ ገለፃ በእሁዱ የከባድ መሣርያ ድብደባ በርካታ ሰላማዊ የዓዲግራት ከተማ ነዋሪዎች መጎዳታቸውንና እንዲሁም መኖርያ ቤቶች መውደማቸውን የሚናገሩ ሲሆን፣ ከዓዲግራት ቅርብ ርቀት በሚገኘው ኢሮብ ወረዳም እንዲሁ ከኤርትራ በኩል የከባድ መሳርያ ድብደባ ሲፈፀም መሰንበቱ ይገልፃሉ።
«በአዲግራትበድብደባው በርካታ ሰው ተጎድቷል።ፍንጣሪ የመታው ብዙ አለ።ኅብረተሰቡ በጣም ተጎሳቁሏል ። ደንግጦ አካባቢውን ለቆ የሚወጣ ሰውም አይቻለሁ።በኢሮብ አካባቢ ደግሞ ከመስቀል በዓል ዋዜማ አንስቶ ተከታታይ ድደባ አለ።ከአይጋ ተራራ አካባቢ ነው የሚተኩሱት።በዱሀን ከባድ ጉዳት ደርሷል።የሚደበድቡት የኤርትራ ሠራዊት ናቸው።ወደ ሶብያ አካባቢ ለመግባት ይሞክራሉ።ግን እስካሁን የሉም።»
እንደ ትግራይ መንግስት ገለፃ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስት ጦሮች ከነበሩት ግንባሮች በተጨማሪ በዛላንበሳ፣ ራማ እና ፆሮና በኩል ተጨማሪ የጦር ግንባሮች ስለመከፈታቸው አረጋግጧል። ጦርነቱ ተባብሶ በቀጠለበት፥ በተለይም ከኤርትራ ጋር ከሚዋሰኑ የትግራይ አካባቢዎች 500 ሺህ ገደማ የሚሆን ህዝብ እንደአዲስ  መፈናቀሉ በትግራይ ክልል በኩል ይገልፃል። የክልሉ አስተዳደር እና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት እንደሚሉት ወደ ትግራይ የሚገባ ሰብአዊ እርዳታ በመደናቀፉ 6 ሚልዮን የሚጠጋ በክልሉ የሚኖር ህዝብ በመድሃኒት በምግብ አቅርቦት እጥረት  ግር ተጋልጧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጦርነቱ ቆሞ ግጭቱ በሰላማዊ ንግግር እንዲፈታ ዜጎች ጥሪ ያቀርባሉ።በመቀሌ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ጥሪያቸው ሰላም ነው።የትግራይ ማሕበራት ጥያቄ

ታሞ መቀሌ ሆስፒታል የሚገኝ ህጻን ከእናቱ ጋር
ታሞ መቀሌ ሆስፒታል የሚገኝ ህጻን ከእናቱ ጋር ምስል Million H. Silase/DW


«ዮሐንስ ገብረ ሚካኤል እባላለሁ አሁን እንደምናየው በቃ ህዝቡ በከባድ መሣሪያ በድሮንም በሚግ እየጠፋ ነው።ህዝብ እየተጎዳ ብቻ ነው።እና እያገኘነው ያለነው በቃ መጥፎ ነገር እንጂ ጥሩ ነገር እያገኘን አይደለም።በጣም እየተጎዳን ነው ህዝብ በጣም እየተጎዳ ነው።ለህዝብ ብለው ጦርነቱን በድርድር ቢፈቱት ጥሩ ነው።»
«ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጦርነቱ እንዲቆም ግፊት ማድረግ አለበት።ጦርነት እጅግ በጣም አስከፊ ነገር ነው።የትግራይ ህዝብ ከባድ ችግር ላይ ነው ያለው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መድኃኒት ክትባት ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ አለበት።»
«መጋቤ ሀዲስ መምህር አምሀ ማርቆስ እባላለሁ ፤ነገሩ እጅግ በጣም መመለስ የማይችልበት ደረጃ እየሄደ ይመስላል ሁለት ሦስት ዓመት አይተነዋል።ትክክል አልሆነም ስለዚህ አሁን በተለይ የሃይማኖት መሪው ሰላም ቢሰብክ መስቀል ይዞ ሰላም ቢያውጅ፤ህዝብን አስፈጅተዋል።ጠቅላላው ኤኮኖሚም ደቋል።ይህን አይቶ የማይማር ፖለቲካ መኖር የለበትም፤ከመንግሥትም ጭምር ይሄ ከሆነ ትርፉ በቃ ሁሉም ነገር ያለፈው አልፏል፤አሁን ግን ሰላምን ነው የምንሻው።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ 
ኂሩት መለሰ