1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ

ሰኞ፣ ሰኔ 6 2014

የባህር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስማማው ሞገስ የግንዛቤ ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው ዘመቻው በባህርዳር እንዳልተጀመረ ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት 2 ቀናት የክትባት ዘመቻው ይጀመራል ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል ክትባት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮቪድ መከላከያ ክትባት ፡መውሰዳቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4CdE4
Südafrika Kapstadt | Impfung
ምስል Themba Hadebe/AP Photo/picture alliance

የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ በአማራ ክልል

በአማራ ክልል ከሰኔ 2/2014 ዓ ም ጀምሮ 6 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት መጀመሩን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፣ ያነጋገርናቸው ተከታቢዎች ክትባቱ ችግር እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ግን ቀሪ የቅድመ ዝግጅት ስላሉ ዘመቻው እስካሁን እንዳልተጀመረ ጤና ተቋማቱ አመልክተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ የመቀነስ አዝማሚያ ታይቶበት የነበረ ቢሆንም ህብረተሰቡ በዚህ በመዘናጋት የጥንቃቄ መንገዶችን መከተል ባለመቻሉ ወረርሽኙ አሁን እየጨመረ መምጣቱን በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ ለዶቼቬለ ተናግረዋል፡፡ወረርሽኙን ለመከላከል ካለፈው ሳምንት ሐሙስ  ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ መከላከያ ክትባት መጀመሩንና በአማራ ክልል ከ6 ሚሊዮን በላይ እድሜያቸው 12ና በላይ ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች ይከተባሉ ብለዋል፡፡

በዚህ ዘመቻ የማጠናከሪያ ክትባት ያልወሰዱ፣ ሁለት ጊዜ ይወሰድ የነበረን የመከላከያ ክትባት አንዴ ብቻ የወሰዱ ክትባቱን የሚያገኙ ሲሆን በዋናነት ግን ከዚህ በፊት ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች ከተዘጋጁ 4 ዓይነት ክትባቶች መካከል አንዱን እንደሚወስዱ አመልክተዋል፡፡በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዝቋላ የተፈናቃዮች የህክምና ባለሙያ ደርቤ ውዱ በመጠለያ ጣቢያው ከዘመቻው አንድ ቀን ቀድመው ክትባቱን እየሰጡ እንደሆነ ለዶቼ ቬሌ በስልክ ገልጠዋል፡፡የምስራቅ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጋሻዬ ጌታሁን አስፈላጊው ቅስቀሳ ከተደረገ በኋላ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች የክትባት ዘመቻው መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ክትባቱን ከወሰዱ የዝቋላ ተፈናቃዮች መካከል አንዳንዶቹ ክትባቱ የፈጠረባቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሌለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በባሕር ዳር ከተማ በየትኛውም የጤና ተቋም የዘመቻ ክትባቱ እንዳልተጀመረ ማረጋገጥ ችለናል፡፡የባህር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስማማው ሞገስ ቀሪ በተለይም ከተማሪዎችና መምህራን ጋር መሰራት ያለባቸው የግንዛቤ ሥራዎች በመኖራቸው ዘመቻው እንዳልተጀመረ ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት 2 ቀናት የመከላከያ ክትባት ዘመቻው ይጀመራል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ክትባት ከተጀመረበት ከመጋቢት 2013 ዓም ጀምሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮቪድ መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ ተናግረዋል፡፡እስከ ትናንት ሰኔ 5/2014 ዓ ም በአማራ ክልል 311ሺህ ሰዎች የኮቪድ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን 16ሺህ 475 ከህመሙ ሲያገግሙ 496 ህይወታቸው ማለፉን የክልሉ ቢሮ በእየለቱ የሚያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡


ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ