1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ መታሰቢያ በቨርጂኒያ

ዓርብ፣ መስከረም 20 2015

ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ ለኢትዮጵያ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዘክር መርሐ ግብር በአሜሪካ ቨርጂኒያ ተካሄደ። የምኒልክ ሶሳይቲ ሰብሳቢ አቶ ዮም አብይ ፍሰሐ በተለይ ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት መርሐ ግብሩን ማካሄድ ያስፈለገው አዲሱ ትውልድ የአጼ ምኒልክን አበርክቶ በሚገባ እንዲያውቀው ለማስቻል ነው።

https://p.dw.com/p/4HbLe
አዲስ አበባ የሚገኘው የዳግማዊ ዐጤ ምንሊክ ሐውልት
ምስል Solomon Muchie/DW

ምኒልክ ሶሳይቲ የተባለ ማኀበርም ተመስርቷል

ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ ለኢትዮጵያ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዘክር መርሐ ግብር በአሜሪካ ቨርጂኒያ ተካሄደ። የምኒልክ ሶሳይቲ ሰብሳቢ አቶ ዮም አብይ ፍሰሐ በተለይ ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት መርሐ ግብሩን ማካሄድ ያስፈለገው አዲሱ ትውልድ የአጼ ምኒልክን አበርክቶ በሚገባ እንዲያውቀው ለማስቻል ነው። የማኀበሩ ጸሐፊና የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ በበኩላቸው ማኀበሩ በአጼ ምኒልክ ስም የቴክኖሎጂና የሳይንስ ኢንስቲትዩት ለመመስረት በዝግጅት ላይ መሆኑን ዐስታውቀዋል። 

በዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራችነታቸው የሚታወቁት አፄ ምኒልክን ለመዘከር በተሰናዳው መርሐ ግብር ላይ፣ የቀድሞው ንጉስ ለኢትዮጵያ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በታሪክ ምሁራን ቀርቦበታል። ዘመን ተሻጋሪ ንግግሮቻቸውም ለታዳምያኑ ቀርቧል። 

የምኒልክ ሶሳይቲ ማኀበር ሰብሳቢ አቶ ዮም አብይ፣ «ዝክረ ምኒልክ» በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን መርሐ ግብር ዓላማ እስመልክተው የሚከተለውን ተናግረዋል። የአድዋ ድል በዓልና የምንሊክ አደባባይ

«በመጀመሪያ ዋናው ነገር ምንድን ነው፣ታሪክን ለሚቀጥለወሰ ትውልድ አፄ ምኒልክ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በጣም ከፍ ያለ ነው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝብ በሙሉ ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚቀጥለው ትውልድ እንዲያውቀው ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲያውቅ ነው የምንፈልገው። የኢትዮጵያ ታሪክ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በደንብ ወጣቶች አልተማሩትም።እና ጣዕሙ እንዳይለወጥ ትልቅ ታሪክ ያላት ሃገር ናት። ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ለዓለም ሕዝብ ትልቅ ያበረከተች ሃገር ስለሆነች እነዚህን ደግሞ ወጣቶቹ መጪው ትውልድ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ እንዲያውቅ ለማድረግ ነው። ትልቁ ዓላማችን እሱ ነው።»

የማኀበሩ ጸሐፊና የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ በበኩላቸው፦ «የሃገራችንን አንድነት፣ ወጣቱ ለሃገሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ፣ በፍቅርና በአንድነት  መኖር እንዲችል፣የአባታቻችንን ታላላቅ ጠድልና ታሪክ በማስተማር አባቶቻችንን ሆነን እንድንገኝ ወይም በልጠን እንድንገኝ እንጂ ያነሰ ትውልድ እንዳንሆን፣ለሃገራችን ችግር እንዳንሆን የሚያስተምር ዕቅድና ዓላማ ያለው ነው።»

አቶ ሙሉጌታ፣ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አገልግሎት የሚኖረውና፣በአፄ ምኒልክ ስም የተሰየመ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ኢንስቲትዩት፣ ለመመስረት ሶሳይቲው በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዕለቱ ለኢትዮጵያ መልካም ያደረጉ ግለሰቦች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ሁለት አባት አርበኞች በዳግማዊ ዐጤ ምንሊክ አደባባይ ፊት ግራና ቀኝ ቆመው
ምስል Getachew T. Haile-Giorgis

ከተሸላሚዎቹ መኻከል፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሰሜን ወሎ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ አቶ ተካልኝ ገዳሙ፣ አርቲስት አለም ፀሐይ ወዳጆና አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን(ቴዲ አፍሮ)ይገኙበታል።

ታላቊ የአድዋ ድል የአንድነት ተምሳሌት

አቶ ዮም እንዳሉት፣ሽልማቱ ወጣቶች ተሸላሚዎችን እንደ ተምሳሌት እንዲመለከታቸው ታስቦ የተካሄደ ነው።

«ትላልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች ናቸው። እነዚህን ሰዎች ደግሞ ለእነሱ እውቅና በመስጠት ወጣቱ ትውልድ እነዚህን ሰዎች እያየ እንደ ተምሳሌት እንዲወስዳቸው እና ጥሩ ጥሩ ነገርን ለሃገሩ እንዲያደርግየማለት ነው፤ እና ኢትዮጵያ የሚለውን ነገር ነው ለማጠናከር የምንፈልገው የኢትዮጵያን አንድነት ነው፣አብሮነትን ነው እና መጪው ትውልድ ይህን ወስዶ ደግሞ እንደዚህ መቼም ኃላፊነት አለብን በሚል ነው።የኛ ትውልድ አባቶቻችን እናቶቻችን አያቶቻችን ኢትዮጵያን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ትልቅ መስዋእትነት ከፍለው በአንድነት እዚህ አድርሰውልናል እና አሁን ደግሞ እኛ ደግሞ ኃላፊነት ስላለብን ይህንን ለመወጣት የተደረገ ነገር ነው።»

የሚኒልክ ሶሳይቲ ማኀበር፣አፄ ምኒልክን ለመዘከር ፣ምኒልክ ቴሌቪዥንን መስርቶ የተለያዪ ዝግጅቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል። የምኒልክ ቴሌቪዥን ግብን በተመለከተ የጣቢያው መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ የሚከተለውን ይናገራሉ።

«እኛ እንግዲህ ምኒልክ ቴሌቪዥን ብለን የመሠረትነው በምንሊክ ስም ለሃገርና ለወገን የሚጠቅሙ ነገሮችን ማስተማርና ወጣቱን ማንቃት በሃገራችን ላይ ሠላምና አንድነት ፍቅር መፍጠር እንዲችል፣ጥላቻና መለያየትን የሚሰብኩት ሰዎች እንዳሉ ሆኖ እነሱን በመጣላት ወይ በመሳደብ ሳይሆን ማስተካከል የሚቻለው እነሱ ትውልድ ላይ ደሰሩትን ወይም የዘሩትን መጥፎ ነገር መስበርም ሆነ ማጥፋት የሚቻለው በበጎ ነገር ስለሆነ፣በጎ ነገር ለመስራት ብለን ምኒልክ ቴሌቪዥንን መስርተናል። በምኒልክ ስምም ያደረግነው በቀጥታ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ እንዲሆን እና ሕዝቡም ይህን አውቆት በእዛ ላይ ትኩረት ተደርጎ፣ ለታሪካችን ቦታ እንዲሰጥ፣ ትክክለኛው ታሪካችን እንዲነገር እንዲሰበክ እንዲማር ወጣቱ የተዛባውን ደግሞ ቻሌንጅ ማድረግ እንድንችል፣ በፍቅርና በሰላም ጥሩ ነገር ማስተማር እንድንችል በመዝናኛ ተአማኒ የሆነ ታላቁ አፄ ምኒልክ በእርሳቸው ስም ነውና እዛ ደረጃ ስብዕና ያለው ተቋም ለመመስረት ሞክረናል። ቴሌቪዥኑ የተቋቋመው በዚያ ደረጃ  ነው።የቴሌቪዥኑ እንቅስቃሴ በቂ አይደለም ብለን በማሰባችን ምኒልክ ሶሳይቲ የተባለ ማኀበር መስርተናል።ሁለቱም የተያያዘና የሚደጋገፍ፣ አብሮ የሚሄድ ተቋም ነው» ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ