1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን የሚገኙ የታንዛንያ ቅርሶች ጉዳይ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 3 2015

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴታ ካትያ ኮይል የሰው ልጆች አጽሞችን ለታንዛንያ ለመመለስ መንግሥታቸው እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና ትኩረቱ ቅርሶችን መመለስ ላይ ብቻ መሆኑ መተቸቱ አልቀረም። በተለይ ስልታዊው ዘረኝነት እና ኢፍትሀዊነት ወደ ጎን መገፋቱ በታሪክ ምሁራን ተነቅፏል።

https://p.dw.com/p/4SPUn
Blick in die Saurierhalle mit Skelett eines Brachiosaurus brancai, dem weltweit größten ausgestellten Saurierskelett, Museum für Naturkunde, Berlin, Deutschland, Europa
ምስል Ingo Schulz/imageBROKER/picture alliance

ጀርመን የሚገኙ የታንዛንያ ቅርሶች ጉዳይ

ጀርመን ታንዛንያን ቅኝ የገዛችበትን ዘመን የሚያስታውስ እጅግ የሚመስጥ ቅርስ በበርሊኑ የተፈጥሮ ታሪክ ቤተ መዘክር ውስጥ ይገኛል። ይህም  13 ሜትር ርዝመት ያለው ከዓለም ትልቁ የተገጣጠመ የዳይኖሰረስ ቅሪተ አጽም ነው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከያኔው የጀርመን የምሥራቅ አፍሪቃ ቅኝ ግዛቶች አንዷበሆነችው ታንዛንያ  የጀርመን ቅሪተ አካል ተመራማሪዎች በቁፋሮ አውጥተው የዘረፉት ይህ  በበርሊኑ ቤተ መዘክር የሚገኘው ቅርስ ለዘመናት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና የጎብኚዎች መስህብ ሆኖ ዘልቋል። ከቦን ዩኒቨርስቲ የታሪክ የዶክትሬት ትምህርቱን በቅርቡ ያጠናቀቀው ፊልሞን ሞቶ ሊጎበኝ ካሰባቸው መካከል አንዱ ይህ ቅሪተ አጽም ነው። ታንዛኒያዊው  የታሪክ ምሁር  ቅሪተ አጽሙ ጀርመን የመጣበትን የቅኝ ግዛት ዐውድ ያውቃል። በርሱ አመለካከት ቅሪተ አጽሙ ወደ ጀርመን የመጣው በሕገ ወጥ መንገድ ነው። ከልጅነቱ አንስቶ ይህን የመሳሰሉት ቅርሶችና ሌሎችም ጀርመን የዘረፈቻቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ አጥንቶች ወደ ሀገራቸው ታንዛኒያ እንዲመለሱ የሚጠይቁ ውይይቶች  በሀገሩ ይካሄዱ እንደነበር ያውቃል።

«እንደምረዳው በጣም ጠቃሚ ውይይቶች ናቸው።ሰዎች እርስ በርሳችን ስንነጋገር ንግግር ካለ በአዎንታዊ መንገድ መፍትሄ የሚያስገኝ ውይይት ለማካሄድ እድል ይሰጣል። ሰዎችን ካልተነጋገሩ ግን በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ድባብ ጥላቻ የተሞላበት ይሆናል።»

ስለ ጀርመን የቀድሞ የቅኝ ግዛት ዘመን  በሚካሄዱ ፖለቲካዊ ክርክሮች ላይ የሚነሱት ጉዳዮች ከማያስደስታቸው አንዷ የተቃዋሚው የጀርመን የግራዎቹ ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሴቪም ዳግዴለን አንዷ ናቸው። የጀርመን ፌደራል መንግሥት ለጀርመንን የቅኝ ግዛት እዳዎች ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰe ጥሪ ያቀርባሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ቅርሶቹን የመመለሱ ሕጋዊ ሂደት ሊጀመር ይገባል።

«ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር ግንኙነቶችን እንደገና ስለመጀመር እንደሚናገር  እንደ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልትስ ያለ ማንኛውም ፖለቲከኛ በቅኝ ግዛት ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎችን ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ ሂደት ወደ ጎን ሊተው አይገባም ።»

Sevim Dagdelen Mitlgied des Deutschen Bundestages
ምስል Savim Dagdelen

የምክር ቤት አባልዋ ዳግዴለንና በምክር ቤቱ የፓርቲያቸው ተወካይ ቡድን ላቀረቡት ለዚህ ጥያቄ ያገኙት መልስ አላስደሰታቸውም።የጀርመን ፌደራል መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አንድሪያስ ሚሻኤሊስ

የምክር ቤት አባልዋ ዳግዴለንና በምክር ቤቱ የግራዎቹ ፓርቲ ቡድን ተወካይ  ላቀረቡት ለዚህ ጥያቄ ያገኙት መልስ አላስደሰታቸውም። የጀርመን ፌደራል መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አንድሪያስ ሚሻኤሊስ ፣የሰው ልጆች ቅሪተ አካላትንና ሌሎች ባህላዊ ንብረቶችን መመለስን በሚመለከት ድርድር እንዲካሄድ ሀሳብ መቅረቡን የጀርመን ፌደራል መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ከታንዛንያ መንግሥት ጋር ንግግር ማካሄድን እንደሚደግፍ አስታውቀዋል። ይሁንና ከዳግደሌን ቁልፍ ጥያቄዎች አንዱ አሁንም መልስ አላገኘም። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ እይታ ያኔ የሆነው የጦር ወንጀል ወይስ የዘር ማጥፋት ለሚለው ጥያቄ  የጀርመን ፌደራል መንግሥት የሰጠው መልስ  አመጹን የማክሸፍ እርምጃ ነው የተወሰደው የሚል ነው። ጀርመን ቀድሞ በቅኝ በያዘችው አሁን ታንዛንያ ተብሎ በሚጠራው ሀገር ደቡባዊ ክፍል የገጠሩ ህዝብ ላይ ጭናው የነበረውን በግዳጅ ጥጥ ለውጭ ገበያ ማምረትን በመቃወም የአገሬው ሰዎች  ካመጹ በኋላ ማጂ ማጂ በመባል የሚጠራው ጦርነት ተነሳ።ከጎርጎሮሳዊው 1905 እስከ 1908 ዓም ድረስ በዘለቀው በዚሁ ጦርነት ቁጥራቸው እስከ 300,000  የሚደርስ ሰዎች በአመዛኙ በረሀብ ሕይወታቸው አልፏል።በወቅቱ እርሻዎች በእሳት የጋዩ ሲሆን ብዙዎች ሰዎችም በረሀብ አለንጋ ተገርፈዋል። የጀርመን መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ከታንዛንያ መንግሥት ጋር መተማመን የሞላበት ንግግር ማካሄድን ጠቁሟል። ሆኖም የልዩ ልዑካን ጉዳይ አልታቀደም ። እዚህ ላይ የግራ ክንፍ ፖለቲከኛዋ ዳግደሊን ከናሚቢያው የሄሬሮና የናማ ጎሳዎች የዘር ማጥፋት ወንጀል ትምሕርት ሊወሰድ ይገባል ይላሉ።በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለቱም መንግሥታት የጋራ መግለጫ ለማውጣት በቅተዋል። ይሁንና ናሚብያ ግን አላጸደቀችውም። የዚህ ምክንያቱም በተለይ በጋራ መግለጫው ላይ ከድርጊቱ ሰለባዎች ቤተሰቦች በኩል ጠንካራ ተቃውሞ መነሳቱ ነው።  እዚህ ላይ የግራ ክንፍ ፖለቲከኛዋ ዳግደሊን ከናሚቢያው የሄሬሮና የናማ ጎሳዎች የዘር ማጥፋት ወንጀል ትምሕርት ሊወሰድ ይገባል ይላሉ።

Reopening Of Natural History Museum In Berlin
ምስል Alexander Hassenstein/Getty Images

«ከናሚብያው ጉዳይ በተለየ የፌደራል ጀርመን መንግሥት ከታንዛኒያ መንግሥት ጋር በመተባበር በተለይ በዘር ማጥፋት ወንጀሉ ሰለባ የሆኑ ማኅበረሰቦችን ማወያየትንም ከልብ ሊያስብበት ይገባል።»

የሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁሩ ዩርገን ዚመረር መንግሥት ጉዳዩን ወደ ጎን ማለቱ አንድ ነገር ያሳያል ይላሉ።

« አንድ አካል በይፋ በቅኝ ግዛት ዘመን ለተፈጸሙ ጥቃቶች እውቅና ሲሰጥ ከካሳ  ወይም ከይቅርታ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅድመ ሁኔታዎች ያስፈራዋል። ምክንያቱም የዚህን መሰለን ክርክር በቅጡ ስናጤን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለተፈጸሙ ወንጀሎች የካሳ ጥያቄም ይነሳል።ይሁንና የናሚብያን ጉዳይ እየሸፋፈኑና እየደበቁ ማለፍ አይሰራም።»

በሌላ በኩል የጀርመን መንግሥት በቀድሞ የሀገሪቱ የቅኝ ግዛት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመንቀሳቀስ እየሞከረ ነው። ባለፈው ታህሳስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ከከባህል ሚኒስትር ዴታ ክላውዲያ ሮት ጋር በቅኝ ግዛት ዘመን ጀርመን የተዘረፉትን የቤኒን ነሐሶችን ለማስረከብ ናይጀሪያ ነበሩ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴታ ካትያ ኮይል ደግሞ የሰው ልጆች አጽሞችን ለታንዛንያ ለመመለስ መንግሥታቸው እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና ትኩረቱ ቅርሶችን መመለስ ላይ ብቻ መሆኑ መተቸቱ አልቀረም። በተለይ ስልታዊው ዘረኝነት እና ኢፍትሀዊነት ወደ ጎን መገፋቱ በታሪክ ምሁሩ ዚመረር ተነቅፏል።  የጀርመንም ሆነ የአውሮጳ ብልጽግና ከየት መጣ የሚለውን ጥያቄ የሚያነሱት ምሁራን ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚሽን እንዲቋቋም ጥሪ አቅርበዋል።   

 

ኂሩት መለሰ