1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን፤ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን የግሎባል ኢኮኖሚ ሽልማትን አሸነፉ

ረቡዕ፣ ሰኔ 14 2015

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥስራቿ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ጀርመን የኪል ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋም የሚያዘጋጀውን ግሎባል ኢኮኖሚ ሽልማትን አሸነፉ። ዶ/ር እሌኒ በጀርመን ኪል ከተማ የ18ኛዉን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሽልማትን በቢዝነስ ዘርፍ ሲወስዱ፤ ሽልማቱ ኢትዮጵያ ወስጥ ላከናወኗቸው ስራዎች እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ መደሰታቸዉን ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4Su1B
Wirtschaftspreis an Eleni Zaude Gabre-Madhin
ምስል Zega Ras-Work

ይህን ሽልማት በመቀበሌ በጣም ተደስቻለሁ፤ ይህ ለኢትዮጵያም ትልቅ ኩራት እንደሆነ ይሰማኛል

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥስራቿ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ጀርመን የኪል ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋም የሚያዘጋጀውን ግሎባል ኢኮኖሚ ሽልማትን አሸናፊ ሆኑ። ሰኔ 12 ቀን 20215 ዓ.ም  በጀርመንዋ ኪል ከተማ በተዘጋጀዉ 18ኛ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ በቢዝነስ ዘርፍ ሽልማታቸውን የተቀበሉት ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን፤ ሽልማቱ ኢትዮጵያ ወስጥ ላከናወኗቸው ተግባራት እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ መደሰታቸዉን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያዊትዋ የኢኮኖሚ ምሁር ሌላ፤ በፖለቲካዉ ዘርፍ የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ንጎዝ ኦኮንጆ አሸናፊ ሲሆኑ ፤ በምጣኔ ኃብት ዘርፍ  ደግሞ የአፍሪቃ ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሌዎናርድ ዋንታቼኮ ሽልማታቸዉን ወስደዋል።

ጀርመን ኪል ከተማ የሚገኘዉ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋም አሸናፊዎችን የሚወስኑ ዳኞችን ጠቅሶ በድረ-ገፁ እንዳስነበበዉ፤ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ለሽልማቱ ብቁ ካደረጋቸዉ ሥራዎቻቸዉ መካከል የበርካታ አርሶ አደሮች እና ወጣቶች  ህይወት ማሻሻላቸው የታየበት ሥራ፤ በተለይ በአፍሪቃ ጭምር ቀዳሚ ነው በተባለዉ  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አማካኝነት ለ15 ሚሊዮን አርሶ አደሮች መተዳደሪያን ማስገኘታቸዉን ጠቅሷል።  

Wirtschaftspreis an Eleni Zaude Gabre-Madhin
ጀርመን፤ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን የግሎባል ኢኮኖሚ ሽልማትን አሸነፉ ምስል Zega Ras-Work

ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን“ብሉሙን” የተሰኘዉን የወጣቶች የሃሳብ ማፍለቂያ ተቋምን ማቋቋማቸዉ እና ወጣቱ ከግብርና ጋር ለተያያዙ የሥራ ፈጠራዎች  እና የሃሳብ ማፍለቂያ የሚሆን ማዕከል ለወጣቶች እንደፈጠሩም ጠቅሷል።

ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ፤ ለሽልማቱ ሦስት ነገሮች ተጠቅሰዋል።

“በአንድ  በኩል በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ነዉ የተጠቀሰዉ፤ ለከፍተኛ ሃገር ልማት አገልግሎት ተጽዕኖ እንዲሁም በቀጥታ የበርካታ ሚሊዮን ወዛደሮችን ህይወት በመጥቀም ትራንስፎርም በማድረግ በሚባለዉ ላይ ነዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተቋቋመዉ «ብሉሙን» በተሰኘዉ ተቋም ከወጣቶች ስራ ፈጠራ ጋር ፤ ወጣቱን ለማልማት ስለተሰራዉ ስራ ነዉ።  ሦስተኛዉ፤  በአፍሪቃ አቀፍ የተለያዩ ሥራዎች በአንድ በኩል፤ «ኢሌኒ ልልሲ» የሚባለዉ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በርካታ ሃገሮች ላይ እንደዚሁ አይነት የምርት ገበያ አሰራር ለመዘርጋት ፍላጎት ስለነበር፤ እነሱን በማገልገል፤ እና ያንን ሥራ በመዘርጋት ፤ የተለያዩ ስድስት ሰባት ሃገሮች ላይ እንዲሁም ደግሞ አሁን በምሰራበት በኒዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም «ዩ ኤን ዲ ፒ» አፍሪቃ ቢሮ   በሚገኘዉ ፤ አፍሪቃ አቀፍ የሆነ የስራ ፈጠራ ድጋፍ ፕሮጀክትን በመምራት እና  በርካታ ሚሊየን ለሚሆኑ የወጣቶች የፈጠራ ስራ የፋይናንስ ድጋፍ የሚሰጥ ፕሮግራም በመምራት የሚለዉ ሁሉ ለሽልማቱ መገኘት ተጠቅሷል።”  

ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ጀርመን ኪል ላይ የነበረዉ የሽልማት መንፈስ በጣም በጣም ደስ ይል ነበር ሲሉ ተናግረዋል። በተለይ ከአንዷ ተሸላሚ አንደበት እንደተሰማዉ፤ ስለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ፕሮግራም ብዙ ትልቅ ስሜት ማሳደሩን ተናግረዋል።   

እንደዚህ አይነት ሽልማት መገኘቱ በጣም የሚያኮራ፤ እና ጥሩ ስሜት የሚሰጥ ነበር ያሉት ዶ/ር እሌኒ በሽልማቱ ተደስቻለሁ፤ ትልቅ ክብር ነዉ የተሰማኝ ብለዋል። ሽልማቱን ያገኘሁት በቢዝነስ ዘርፍ ፤ ያሉት ዶ/ር እሌኒ በፖለቲካዉ ዘርፍ ሽልማት ካገኙት ከዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ከዶ/ር ንጎዝ ኦኮንጆ እና ፤ በምጣኔ ኃብት ዘርፍ  ከአፍሪቃ ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፕሬዝዳንት ከፕሮፌሰር ሌዎናርድ ዋንታቼኮ ጋር ይህን ሽልማት በመቀበሌ ተደስቻለሁ፤ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ኩራት እንደሆነ ይሰማኛል ሲሉ አክለዋል።

Wirtschaftspreis an Eleni Zaude Gabre-Madhin
ጀርመን፤ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን የግሎባል ኢኮኖሚ ሽልማትን አሸነፉ ምስል Zega Ras-Work

ይህ የተቀበልኩት ሽልማት ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን ይችላል ያሉት ዶ/ር እሌኒ በ 15 ዓመታቸዉ ለሃገራቸዉ ብሎም ለአፍሪቃ አበረክታለሁ ብለዉ እቅድ አዉጥተዉ፤ ዓላማዬንም  አሳካለሁ ብለዉ መነሳታቸዉን አስታዉሰዋል።

 «ስለዚህም በወጣትነት የምናልመዉ፤ የምንመኘዉ እና የምናስበዉ ነገር በጣም ትልቅ ቦታ ሊሰጠዉ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። በዚህ ረገድ ወጣቶችን ማበረታታት እፈልጋለሁ። ወጣቱ ዉስጡ የሚሰማዉን፤ እደርስበታለሁ ብሎ የሚመኘዉን ስሜት፤ ይመንበት፤ ይቀጥልበት፤ ይታገልለት። ያ ምኞት አንድ ቀን እተፈለገዉ ቦታ ይደርሳል» ሲሉ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን መልክታቸዉን በተለይ ለወጣቱ አስተላልፈዋል።

 

ከዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ጋር የተካሄደዉን ሙሉ ቃለ ምልልስ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!