1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ምዕራብ ዘረጋች?

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 8 2012

ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት፤ ከዓለም ባንክና የልማት አጋሮች 8.9 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ርዳታ ማግኘቷን ባለሥልጣናቱ አስታውቀዋል። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያበድረው 2.9 ቢሊዮን ዶላር አገሪቱ ካላት ከተቋሙ የመበደር አቅም በ700% ይልቃል። ብድር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱን ጨምሮ ለተለያዩ ዘርፎች ማሻሻያ የታቀደ ነው።

https://p.dw.com/p/3V25K
Washington IWF Logo Symbolbild
ምስል Getty Images/AFP/M. Ngan

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ቦርድ የኢትዮጵያን ብድር ለመመርመር አርብ ይሰበሰባል

ባለፈው ረቡዕ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ለማበደር በባለሙያዎች ደረጃ መስማማቱን ሲያሳውቅ የተደሰቱ የመኖራቸውን ያክል ሥጋት የተሰማቸውም አልጠፉም። ጉዳዩን መልካም ዜናም ሆነ አሳሳቢ የሚያደርጉት በርካታ ምክንያቶች አሉ። አገሪቱ ያለባት የዕዳ መጠን እና መልሶ የመክፈል አቅሟ፤ ብድሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ምጣኔ-ሐብት እና ተቋማቱ የሚከተሉት መንገድ ገፋ ሲልም የገንዘብ መጠኑ ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ካላት የመበደር አቅም አኳያ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።

«የዓለም የገንዘብ ድርጅት ቃል የገባው ገንዘብ ኢትዮጵያ ካላት ከተቋሙ የመበደር አቅም 700%» የላቀ መሆኑን የገለጹት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካሪ እና የኢትዮጵያ የንግድ ተደራዳሪ ማሞ ምኅረቱ በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ውሳኔውን ተቋሙ በኢትዮጵያ የምጣኔ-ሐብት ማሻሻያ ያለው እርግጠኝነት ማሳያ አድርገው አቅርበውታል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አመራሮች አንዱ የሆኑት እዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት ማብራሪያ «ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ያላት የመበደር አቅም በጣም ዝቅተኛ ነው። አሁን የተሰጠው ወይም ይሰጣል ተብሎ ቃል የተገባው በ700 % የላቀ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።  «የዓለም የገንዘብ ድርጅት እንዲህ ሲያደርግ የተለመደ አይደለም» ያሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው  «ተቋሙ በማሻሻያ መርሐ-ግብሩ ትልቅ ዕምነት እንዳለው ያመለክታል» ሲሉ ተደምጠዋል።

አገር በቀሉ የምጣኔ ሐብት ማሻሻያ መርሐ-ግብር

ግዙፉ ብድር የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት "አገር በቀል" ላሉት የምጣኔ ሐብት ማሻሻያ የታቀደ እንደሆነ በዓለም የገንዘብ ድርጅት የእስያ እና ፓሲፊክ ጉዳዮች ክፍል ምክትል ኃላፊ ሶናሊ ጄን ቻንድራ አስታውቀዋል። ማሻሻያውን "ታሪካዊ" ያሉት የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዎርጂዬቫ ደግሞ የብድር ስምምነቱ "ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ ምጣኔ ሐብታዊ አቅም እንድታሳካ ይረዳታል ፤ለጠንካራ እና አካታች ዕድገትም መሠረት ይጥላል" ሲሉ ተስፋ ሰጥተዋል።

ለሶስት አመታት የሚዘልቀውን የምጣኔ ሐብት ማሻሻያ ለመደገፍ ኢትዮጵያ እና የዓለም የገንዘብድ ድርጅት ባለሙያዎች የተስማሙበትን የረዥም ጊዜ ብድር እጣ ፈንታ ለመወሰን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ቦርድ በመጪው ዓርብ ታኅሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ይሰበሰባል።

ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ እና ከልማት አጋሮች ቡድን (DAG) ተጨማሪ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እና አገሮችን ጨምሮ 30 አባላት ያሉት የልማት አጋሮች ቡድን (DAG) ባለፈው ሳምንት 3 ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ለመስጠት መስማማቱን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም እንደሚሉት ከሶስቱ ተቋማት ወደ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ገንዘብ ሁለት ዓላማዎች ይኖሩታል።

አቶ ጌታቸው «አንደኛ ነገር ባለፉት 20 አመታት ሲከናወን በነበረው የልማት አካሔድ ችግር የተፈጠረ የማክሮ ኤኮኖሚ መዛነፍ አለ። መንግሥት እሱን ለመፍታት ጥረት እያደረኩ ነው ግን እገዛ ያስፈልገኛል ይላል። በማክሮ ኤኮኖሚው ውስጥ የሚታዩ አለመጣጣሞችን እና ተያይዘው የመጡ ቀውሶችን ለማርገብ የሚመጣ ገንዘብ አለ። ሌላው የልማት እንቅስቃሴዎቹን ለማድረግ በበጀትም ከበጀትም ውጪ ላሉ ፕሮጀክቶች ለማከናወን የሚመጣ ድጋፍ አለ። የመጀመሪያው የማክሮ ኤኮኖሚ አለመጣጣምን ለመፍታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚሰጠው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቅ ነው። ዓለም ባንክ ከሚሰጠው ገንዘብ የተወሰነው ወደዚህ የሚመጣ ነው» ሲሉ ያብራራሉ።

«በሁለተኛው ማዕቀፍ የተወሰነው የዓለም ባንክ እርዳታ እና ሌላ ከልማት ድጋፍ ቡድን የሚመጣው ገንዘብ ደግሞ የልማት እንቅስቃሴዎችን ወደ መደገፍ እና ፕሮጀክቶችን ወደ ማከናወን የሚመጣ ድጋፍ ነው» ብለዋል።   

የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት እና በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋት ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በምትበደረው ገንዘብ የሚከወን አንዱ ሥራ ነው። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ተጋላጭነት ለመቀነስ የአስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማጥበቅ፤ የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማጠናከር፤ የመንግሥት ወጪ ለድህነት ቅነሳ እና መሰረታዊ የመሠረተ-ልማት ግንባታ በሚያመች መንገድ ማቀላጠፍ ሁለተኛ ዓላማዎቹ ናቸው።

የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ እና አገሪቱ የምትከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ የግል መዋዕለ-ንዋይን በሚያግዝ መንገድ ማሻሻል አራተኛ፤ የፋይናንስ አገልግሎት ደኅንነት ማዕቀፍን ቁጥጥር ማጠናከር ደግሞ አምስተኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በብድሩ ላይ ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

«እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ያሉ ተቋማት የሚሰጡት ድጋፍ እና እርዳታ ያለ ምንም ተጠየቅ የሚመጣ ገንዘብ አይደለም። ይልቁንም [ኢትዮጵያ] እንድታከናውናቸው የሚያስገድዷቸው ተያያዥ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። አሁን እያደረግን ያለንው የኤኮኖሚ ማሻሻያ የምንለው እንቅስቃሴ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ለረዥም አመታት የኢትዮጵያን መንግሥት እንዲከውኗቸው ሲፈልጓቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን በዋነኝነት እንደ ፖሊሲ መሰረት አድርጎ የሚነሳ ስለሆነ ያንን ለመደገፍ የሚመጣ ገንዘብ ነው» ሲሉ አቶ ጌታቸው ተያይዞ የሚመጣውን ግዴታ ይገልጹታ።

ወደ ምዕራብ ተመልከቱ!

አገር በቀል የተባለው የምጣኔ ሐብት ማሻሻያ የሶስት አመታት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ከ2003 እስከ 2012 ዓ.ም. የተመራችበትን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመተካት በመዘጋጀት ላይ ለሚገኘው አዲስ ውጥን «እርሾ» ሆኖ እንዲያገለግል ታቅዷል። የሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዋናነት «በ2017 ዓ.ም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት አገርን እውን የማድረግ ርዕይ» ነበረው። የገንዘብ ምኒስትር ድዔታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት "ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ትልልቅ ኤኮኖሚዎች አንዱ" የማድረግ ውጥን ያለው አዲስ ዕቅድ እየመጣ ነው።

«ይኸ አገር በቀል [የኤኮኖሚ] ማሻሻያ መንግሥት ላስቀመጠው የአስር አመት ርዕይ ዋናው መሠረት ሆኖ በዚሁ እርሾ ላይ የሚጣል ረዘም ያለ ዕይታ ያለው ደግሞ የአስር አመት ዕቅድ ከሚቀጥለው ጥር ጀምሮ በሰፊው ወደ ሕዝብ ቀርቦ ውይይት ውይይት የሚደረግበት እና ምን አልባትም ከአፍሪካ ትልልቅ ኤኮኖሚዎች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዱ እንድትሆን የሚያደርግ ነው»

«እርዳታ እና ብድርን ዝም ብለን ከቁጥር አንፃር መመልከት የለብንም» የሚሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ከእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የተፈጸመው ሥምምነት ኢትዮጵያ ፊቷን ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ በማዞር የአሰላለፍ ለውጥ የማድረጓ ምልክት እንደሆነ ይናገራሉ።

«በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ኤኮኖሚ የተቀየረ አሰላለፍ አለ። ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበናል በምንልባቸው ያለፉት አስራ አምስት እና አስራ ስድስት አመታት በዋንኛነት የፋይናንስ ምንጭ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ሁለት አካላት ናቸው። በአንድ በኩል እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት አሉ። በሌላ በኩል ግን ዋንኛ ተዋናይ የነበረው የቻይና እርዳታ እና ከቻይና የሚገኘው የብድር መጠን ነው። ስለዚህ ባለፉት አመታት ወደ ምሥራቅ አተኩረን ነበረ። ወደ ምሥራቅ መዞራችን ለምዕራቡ የማይዋጥ እንቅስቃሴ ነበር። አሁን የታየው ለውጥ የእሱን መቀየር የሚያሳይ ነው። አሁን የምዕራቡ ጎራ መንግሥት ለመንግሥት ባለ የዕርዳታ እና ድጋፍ ማዕቀፎች በሌላ በኩል በመልቲ ላተራል ተቋሞች በኩል ድጋፉን ለማስተካከል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታያል»

Äthiopien Addis Abeba im Bau
ምስል DW/E. Bekele

የበላችው ያገሳታል በላይ በላዩ ያጎርሳታል….?

የኢትዮጵያ ዕዳ ከአገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠን ወደ 58 በመቶ ገደማ አሊያም 1.4 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የኢትዮጵያ መንግሥት ካስታወቀ አንድ አመት ገደማ አለፈው። የዓለም ባንክ፣ ቻይና እና የአፍሪካ ልማት ባንክ እንደ ቅደም ተከተላቸው ለኢትዮጵያ ዳጎስ ያለ ብድር በመስጠት ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛሉ።

«ከጠቅላላ የዕዳ ክምችት አንፃር ስናየው በተወሰነ መልኩ ዕዳችንን የሚጨምር ነው» የሚሉት አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያም «ይኸ ልንደሰትበት የሚገባ ነገር አይደለም። ዕዳን በዕዳ መክፈል ዘላቂ አይደለም» ሲሉ ይናገራሉ።

«ዘላቂ የሚሆነው ዕዳን በአገር ውስጥ ሐብት በማሰባሰብ ለመክፈል ሙከራ ማድረግ ነው። ችግር ሲገጥመው ማንም ሰው ችግሩን ለመወጫ ያክል ይበደራል። ያንን ብድር አለመክፈል ችግር ሲሆን እሱን ለማሻሻል የተወሰነ ብድር መበደር ተፈጥሯዊ ነው። ኤኮኖሚያችን ተረጋግቶ፤ ከሀገር ውስጥ ሐብት ማፍራት ችለን ዕዳችንን በአግባቡ ከፍለን ኤኮኖሚያችንን ሊያሳድጉ የሚችሉ ተጨማሪ የፋይናንስ ዕገዛዎችን ልናገኝ የምንችልባቸው ነገሮች መፍጠር ነው ሊያስደስተን የሚገባው። አሁን ያለንበት ሁኔታ አስከፊ እንደሆነ ነው የሚያሳየው። አሁን እሱን ለመወጫ፤ ጊዜ ለመግዣ ነው ገንዘብ እየፈለግን እና ቀዳዳዎቻችንን ለመድፈን እየሞከርን ያለንው» ብለዋል።

እሸቴ በቀለ