1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ቦርድ የኢትዮጵያን 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር አጸደቀ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 11 2012

የዓለም የገንዘብ ድርጅት አስተዳደር ቦርድ የኢትዮጵያን 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር አጸደቀ። ገንዘቡ ኢትዮጵያ ካላት ከተቋሙ መበደር አቅም 700 እጅ የላቀ ነው። ከብድሩ 308.4 ሚሊዮን ዶላር በአፋጣኝ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ የዓለም የገንዘብ ድርጅት አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3VC30
IMF Exekutivdirektorium
ምስል IMF/Cliff Owen

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የምጣኔ-ሐብት ማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚሰጠውን 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር አጸደቀ። ከብድሩ 308.4 ሚሊዮን ዶላር በአፋጣኝ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ የዓለም የገንዘብ ድርጅት አስታውቋል።

ትናንት በዋሽንግተን የተሰበሰበው የዓለም የገንዘብ ድርጅት አስተዳደር ቦርድ ባለፈው ሳምንት የተቋሙ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የደረሱበትን የረዥም ጊዜ የብድር ሥምምነት አጽድቋል።

ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የገንዘብ መጠን አገሪቱ ካላት ከተቋሙ የመበደር አቅም 700% የላቀ መሆኑን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ላለፉት አስር አመታት የድኅነት መጠንን የቀነሰ እና የዜጎቿን የአኗኗር ደረጃ የቀየረ ፈጣን ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት እንደነበራት ያስታወሱት የዓለም የገንዘብ ድርጅት ተቀዳሚ ምክትል የአስተዳደር ዳይሬክተር ዴቪድ ሊፕተን «መንግሥት መር የዕድገት ሥልት ከገደቡ ደርሷል» ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከየዓለም የገንዘብ ድርጅት የፈጸመችው ሥምምነት ከሌሎች የልማት አጋሮች የረዥም ጊዜ ብድር ለማግኘት እንደሚያግዛት ዴቪድ ሊፕተን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት እና በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋት ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በምትበደረው ገንዘብ የሚከወን አንዱ ሥራ ነው።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ተጋላጭነት ለመቀነስ የአስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማጥበቅ ሁለተኛ፤ የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማጠናከር፤ የመንግሥት ወጪ ለድህነት ቅነሳ እና መሰረታዊ የመሠረተ-ልማት ግንባታ በሚያመች መንገድ ማቀላጠፍ ሶስተኛ ዓላማዎቹ ናቸው።

የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ እና አገሪቱ የምትከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ የግል መዋዕለ-ንዋይን በሚያግዝ መንገድ ማሻሻል አራተኛ፤ የፋይናንስ አገልግሎት ደኅንነት ማዕቀፍን ቁጥጥር ማጠናከር ደግሞ አምስተኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በብድሩ ላይ ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ምዕራብ ዘረጋች?

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ በተካሔደ ሀገር አቀፍ የሰላም ውይይት ላይ «ከዓለም የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ መበደር ከእናት እንደ መበደር ነው» ቢሉም የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች አገር በቀል በተባለው የማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚከወኑ ሥራዎች የአገሪቱ ኤኮኖሚ ያሉበትን መሠረታዊ ችግሮች መቅረፍ ስለመቻሉ ጥርጣሬ አላቸው። በተለይ ኢትዮጵያ በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መከተል ስትጀምር የብር የመግዛት አቅም መዳከም እና የዋጋ መናር ሊከሰቱ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ