1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮሮና ከባዱ  የአውሮጳ ህብረት ፈተና 

ማክሰኞ፣ መጋቢት 22 2012

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ 101 ሺህ 779 በደረሰባት በኢጣልያ የ11,591 ሰዎች ሕይወት አልፏል።14 ሺህ 620 ሰዎች ደግሞ እያገገሙ መሆኑ ተገልጿል።ኢጣልያ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ከደረሰባት ከዚህ አስጊ አደጋ ለመውጣትና ኤኮኖሚዋንም ከችግር ለማዳን  ከአውሮጳ ህብረት መጠነ ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ ጠይቃለች።

https://p.dw.com/p/3aGrG
Belgien Lockdown  in Brüssel
ምስል Reuters/Y. Herman

ኮሮና ከባዱ የአውሮጳ ህብረት ፈተና 

ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮሮና ብዙ ዋጋ ካስከፈላቸው ክፍለ ዓለማት አንዷ አውሮጳ ናት።በፍጥነት በሚዛመተው በኮሮና  የሚያዘው ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨመሩ ቀጥሏል፤የሚሞተውም እንዲሁ።ኮሮና በአውሮጳ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የብዙ ሺህ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል።የክፍለ ዓለሙን ምጣኔ ሃብትም ክፉኛ እየጎዳ ነው።እነዚህና ሌሎችም ኮቪድ 19 ያስከተላቸው ችግሮች የአውሮጳ ህብረትን  በተለያየ መንገድ እየፈተኑት ነው።ወቅቱ ህብረቱ ከምሥረታው ወዲህ የደረሰበት እጅግ በጣም ከባድ እና ፈታኝ ጊዜ ሆኗል። በተህዋሲው ስርጭት የከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሃገራትን ባለመርዳቱ ህብረቱ እየተወቀሰ ነው። ኮሮና አውሮጳ ከተከሰተ በኋላ ጀርመን የኮሮና ተህዋሲን ስርጭት ለመከላከል የሚረዱ ምርቶች ለውጭ ገበያ እንዳይቀርቡ ማገዷ፣ የፈረንሳይ መንግሥት ደግሞ የተህዋሲውን ስርጭት ለመቀነስ የሚውሉ መከላከያዎችን ከያሉበት ሰብስቦ መያዙ፣ ችግሩ ጠንቶባቸው ከነበሩ የህብረቱ አባል ሀገራት በኩል  ልዩ ልዩ ቅሬታዎችን አስነስቶ ነበር። ያም ሆኖ አባል ሃገራት በሚችሉት ሁሉ  መደጋገፍ እና መተጋገዛቸው አልቀረም።ከቅሬታው በኋላ ጀርመን እና ፈረንሳይ የበሽታውን ሥርጭት መከላከያ ቁሳቁሶች ለኢጣልያ ልከዋል። ጀርመን እና ስዊትዘርላንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥራቸው ብዙም ባይሆን የኮሮና  ጽኑ ህሙማንን ከኢጣልያ እና ከፈረንሳይ ወስደው እያከሙ ነው።ሆኖም በተለይ ለኢጣልያ ከነርሱ ቀድመው ሩስያና እና ቻይና የህክምና እርዳታ ማድረጋቸው ኩባ እና አልባንያም ሀኪሞች ቀድመው መላካቸው ህብረቱን ማስወቀሱ አልቀረም። ችግሩ ያየለባቸው ኢጣልያን የመሳሰሉ ሃገራት በቅርቡ ለህብረቱ ያቀረቡት የብድር ተማጽኖ የገጠመው ተቃውሞም ሌላው ህብረቱ የሚተችበት ጉዳይ ሆኗል። በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ 101 ሺህ 779 በደረሰባት በኢጣልያ የ11,591 ሰዎች ሕይወት አልፏል።14 ሺህ 620 ሰዎች ደግሞ እያገገሙ መሆኑ ተገልጿል።ኢጣልያ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ከደረሰባት ከዚህ አስጊ አደጋ ለመውጣትና ኤኮኖሚዋንም ከችግር ለማዳን  ከአውሮጳ ህብረት መጠነ ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ ጠይቃለች።የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ በዚህ የጭንቅ ወቅት አቅመ ደካማዎቹ የህብረቱ አባል ሃገራት በአነስተኛ ወለድ ብድር    የሚያገኙበት የጋራ የብድር ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት እያደረጉ ነው።ኢጣልያ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ያቀረበችውን ይህን ሃሳብ  ከደገፉት መካከል ኮሮና በርካታ ዜጎቿን የገደለው እና የያዘው ስፓኝ እንዲሁም ፈረንሳይ፣ ፖርቱጋል እና ግሪክ ይገኙበታል።በአጠቃላይ 9 የህብረቱ አባል ሃገራት ያቀረቡት ኮሮና ቦንድ የተባለው የብድር ስርዓት ለሃገራቱ ኤኮኖሚ ማገገም ወሳኝ ነው ሲሉ የኢጣልያ የኤኮኖሚ ሚኒስትር ሮቤርቶ ግዋልቲሪ ባለፈው ቅዳሜ ተናግረዋል።
«እርግጥ ነው በመልሶ ግንባታው ዕቅድ መሠረት አውሮጳ ሁለት ነገሮችን ማድረግ አለባት።ሃገራትን መርዳት እና ማገዝ አለባት።ከዚሁ ጋርም ከዚህ አስቸኳይ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚካሄዱ ልዩ የኤኮኖሚ ድጋፎችን ማገዝ እና ኤኮኖሚው እንዲያገግም ማደረግ ይገባል።የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ጊዜያዊ ብቻ አይደለም።ወዲያውኑ የሚያስከፍለው ዋጋ አለ።ኤኮኖሚውም እንዲያንሰራራም የጋራ ልዩ ጥረት ያስፈልጋል።አውሮጳን መልሶ የመገንባት እቅድ ኤኮኖሚው እንዲያገግም ታላቅ የማርሻል ፕላን ያስፈልጋል።»
እናም ኢጣልያ እነዚህ እርምጃዎች በአስቸኳይ ካልተወሰዱ የህብረቱ አባል ሃገራት ዜጎች አውሮጳ ህብረት የተቋቋመባቸውን መሠረቶች ዓይናቸው እያየ ማጣቸው አይቀርም ስትል አስጠንቅቃለች።ኢጣልያ በአስቸኳይ ተግባራዊ ይደረግ የምትለው ና ዘጠኝ ሃገራት የደገፉት የኮሮና ቦንድ ፣እዚህ ጀርመን የሚኖሩት እና የሚሰሩት የኤኮኖሚ ምሁር ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ እንደሚሉት አባል ሃገራት በሙሉ በጋራ ገንዘብ የሚያዋጡበት የብድር ስርዓት ነው ። 
ሆኖም 9 የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ስምምነታቸውን የገለጹበት የኮሮና ቦንድ ፣ ጀርመን እና ኔዘርልንድስን በመሳሰሉ ሃገራት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።እነዚህ ሃገራት ህብረቱ ከዛሬ አስራ ሁለት ዓመት በፊት ከደረሰው የዓለም የገንዘብ ቀውስ በኋላ የዘረጋው የዩሮ ማረጋጊያ ስርዓት እያለ ሌላ የብድር አሰራር አስፈላጊ አይደለም ነው የሚሉት።
ባለፈው ሐሙስ የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች በቪድዮ ባካሄዱት ጉባኤ ላይ የጀርመን መራሂተ መንሥት አንጌላ ሜርክልን እና የኢጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴን በዚህ ጉዳይ ተፋጠው ነበር።ኮንቴ ጀርመን እና ሌሎች ሃገራት እንደ መፍትሄ  ያቀረቡት የፋይናንስ ማረጋጊያ ስርዓት በቂ አይደለም ሲሉ ሞግተው ህብረቱ ሌላ አማራጭ ይዞ እንዲቀርብ የ10 ቀን ጊዜ ሰጥተዋል። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የግሪክ ኤኮኖሚ እንዲያንሰራራ ተግባራዊ የሆነው ይህ ማረጋጊያ አሁን በኮሮና ስርጭት ምክንያት ችግር ውስጥ ለወደቁ ሃገራት ጥቅም ላይ ቢውል ነው የሚመርጡት።የሆላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩተም የእነ ኢጣልያን ጥያቄ እንደሚቃወሙና ከዚህ አቋማቸው ፈቅ እንደማይሉ አሳውቀዋል።የሩተን አስተያየት፣ የፖርቱጋሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶንዮ ኮስታ «ፍጹም ድንቁርና» ሲሉ አጣጥለው፣ የአውሮጳ ህብረት የተመሰረተበትን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ዝቅ አድርጎ የሚያይ በማለትም ነቅፈዋል።ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ እንደሚያስረዱት ጀርመንና ሌሎቹ የኮሮና ፈንድ ተቃዋሚዎች ፈንድን እምቢ ያሉበት መሠረታዊ ምክንያት አላቸው። 
በአንጻሩ የኮሮና ቦንድ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን የሚጠይቁት እነ ኢጣልያ ከዛሬ 12 ዓመቱ የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ በኋላ የቁጠባ እርምጃዎችን ማካተትን የሚያስገድደውን የፋይናንስ ስርዓት አሁን መተግበር አንችልም ሲሉ ነው የእነ ሜርክልን ሃሳብ የተቃወሙት።  
የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት በኮሮና ቦንድ የተለያየ አቋም በመያዛቸው በህብረቱ የሰሜን እና የደቡብ ሃገራት መካከል 
ቀድሞ   የነበረው ክፍፍል ዳግም እንዳያንሰራራ ያሰጋል። የአውሮጳ ህብረትም ይህን መሰሉን ቀውስ እንዴት ሊወጣ እንደሚችል ማሳሰቡ አልቀረም።የሕብረቱ አባል ሃገራት በኮሮና ሰበብ ድንበሮቻቸውን መዝጋታቸው እና ወደ ብሔራዊ ፖሊሲዎቻቸው ማፈግፈጋቸው ህብረቱ ከተመሰረተበት መርሆች እንዲርቁ እያደረገ ነው የሚሉ ስሞታዎች ይቀርቡባቸዋል። ይህም የሕብረቱን አንድነት የሚፈታተን ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።ያም ሆኖ የህብረቱን ህልውና አደጋ ላይ እንደማይጥል ነው ዶክተር ጸጋዬ የሚያስረዱት።
ባለፉት ዓመታት ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ያለፈው የአውሮጳ ህብረት አውሮጳን ክፉኛ ያጠቃው የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ መወጣቱ እንደማይቀር ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው ። 

Deutschland Merkel muss wegen Kontakt zu Corona-Infiziertem in Quarantäne
ምስል AFP/M. Kappeler
Italien Rom | Coronavirus | Giuseppe Conte, Ministerpräsident
ምስል Reuters/R. Casilli
Coronavirus | Internationale Hilfe für Italien
ምስል picture-alliance/AP/Russian Defense Ministry Press Service/A. Yereshko

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ