1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓባይ ነገር…

ሰኞ፣ ሐምሌ 6 2012

በቤልጂግ የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ (GERD) ደጋፊዎች የግብፅን አቋም በመቃወም ዘመቻ ጀምረዋል።ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉን ሙሕራንና ታዋቂ ሰዎች ደግሞ መገናኛ ዘዴዎችና መንግሥታት ሥለግድቡ ግንባታ ተገቢዉን መረጃ ለሕዝብ እንዲያሳዉቁ በማለት ፊርማ አሰባስበዉ፣ ለጀርመን፣ለአዉሮጳ ሕብረትና ለኢትዮጵያ መሪዎች አቤቱታ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/3fFWR
Äthiopien Luftbild Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል DW/Negassa Desalegen

የሕዳሴ ግድብ፣ ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን አቤቱታ

 

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በምታስገነበዉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ማመጫ ግድብ ሰበብ ከግብፅ ጋር የገጠመችዉ ዉዝግብ አሁንም ሁነኛ መፍትሔ አላኘም።የሑለቱ ሐገራት እና የሱዳን ባለስልጣናት አለመግባባቱን ለማስወገድ ለብቻቸዉም፣ ታዛቢ ባለበትም መደራደር ከጀመሩ  ዘጠነኛ ዓመታቸዉን ይዘዋል።ግድቡ ዉኃ የሚሞላበት ጊዜ በተቃረበበት ባሁኑ ወቅት የሁለቱ ሐገራት አቋም ይበልጥ መራራቁ፣ እስካሁን የተደረገዉ ድርድርና ሽምግልና ለዉጤት አለመብቃቱን ያረጋግጣል።የሶስቱ ሐገራት ባለስልጣናት በአፍሪቃ ሕብረት አደራዳሪነት ባለፈዉ ሳምንት የጀመሩት ድርድርም እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ አለመጠናቀቁን የኢትዮጵያ የዉሐና መስኖ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ዛሬ በስልክ አረጋግጠዉልናል።ዝርዝሩን ግን፣ ሚንስትሩ፣ «እስከ ድርድሩ ፍፃሜ ድረስ» በማለት ከመናገር ተቆጥበዋል።የዉዝግቡ መፍትሔ ማጣት ዉጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉን በተለይም ሙሕራንና ታዋቂ ግለሰቦችን ሳያሳስብ አልቀረም።
 በቤልጂግ የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ (GERD) ደጋፊዎች የግብፅን አቋም በመቃወም ዘመቻ ጀምረዋል።ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉን ሙሕራንና ታዋቂ ሰዎች ደግሞ መገናኛ ዘዴዎችና መንግሥታት ሥለግድቡ ግንባታ ተገቢዉን መረጃ ለሕዝብ እንዲያሳዉቁ በማለት ፊርማ አሰባስበዉ፣ ለጀርመን፣ለአዉሮጳ ሕብረትና ለኢትዮጵያ መሪዎች አቤቱታ አቅርበዋል።በዛሬዉ ዝግጅታችን ሐሳቡን ካፈለቁት ሁለት ሙሕራን ካንዱ ጋር ያደረግነዉን ቃለ መጠየቅ እናቀርብላችኋለን።
                                    
«እኛ በጀርመን ሐገር የምንኖር ኢትዮጵያዉያንና ጀርመን ኢትዮጵያዉያን -----»ይላል አቤቱታ አቅራቢዎቹ ዋና ለመራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የፃፉት ደብዳቤ----አያይዞም፣ «እርስዎ» ሜርክልን ማለት ነዉ «እንደ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን እንደ ሳይንቲስትና እንደ አንድ የኢትዮጵያ ወዳጅ ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተሉት----» እያለ፤ «የእርስዎ አመለካከትና ሐሳብ በሁሉም ተሳታፊ ሐገሮች ዘንድ አድንቆትና እዉቅና እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነን።» ብሎ ያሳርጋል።አቤቱታዉን ሙሕራን፣የኃይማኖቶችና የማሕበራት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሙያዎችና ባለሐብቶች በድምሩ 60ሰዎች ፈርመዉበታል።ዶክተር ፀጋዬ ደግነሕ ከሁለቱ አስተባባሪዎች አንዱ ናቸዉ።ዶክተር ፀጋዬ ኤኮኖሚስት፣የዕዉቀት ሽግግር ባለሙያና በዓለም አቀፉ ኩባንያ የብዙኃነት ሥራ አስኪያጅ ናቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ