1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮሮና የታገደዉ የጀርመኑን ባህላዊ የገና ገበያ  

ሐሙስ፣ ኅዳር 10 2013

የዓለምን ኤኮኖሚ ብሎም ማኅበራዊ መስተጋብርን ቀስፎ የያዘዉ የኮሮና ወረርሽኝ ፤ አዉሮጳ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በመቀስቀሱ የተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት ተኅዋሲዉ ይበልጥ ተሰራጭቶ ማኅበረሰብን እንዳይገድል ፤ የታማሚዉን ሕዝብ ቁጥርም እንዳይጨምርና  ሆስፒታሎች እንዳይጣበቡ የተለያዩ የዝዉዉር እገዳ ደንቦችን አጥብቀዉ እየተገበሩ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3lZbx
BdT Deutschland Magdeburg Weihnachtsmarkt
ምስል Klaus-Dietmar Gabbert/dpa/picture alliance

የጀርመን የተለያዩ ፌደራል ግዛቶች ገበያዉን አንዘረጋም ሲሉ እያስታወቁ ነዉ

 

የዓለምን ኤኮኖሚ ብሎም ማኅበራዊ መስተጋብርን ቀስፎ የያዘዉ የኮሮና ወረርሽኝ ፤ አዉሮጳ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በመቀስቀሱ የተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት ተኅዋሲዉ ይበልጥ ተሰራጭቶ ማኅበረሰብን እንዳይገድል ፤ የታማሚዉን ሕዝብ ቁጥርም እንዳይጨምርና  ሆስፒታሎች እንዳይጣበቡ የተለያዩ የዝዉዉር እገዳ ደንቦችን አጥብቀዉ እየተገበሩ ነዉ። በጀርመን የምግብ ቤቶች እና ቡና ቤቶች ፤ ማኅበራዊ የስፖርት አዳራሾች እና የመዋኛ አዳራሾች ዝግ ናቸዉ። ምግብን አዞ በመልክተኛ  ገዝቶ እቤት ወስዶ አልያም ፓርክ ዉስጥ ቁጭ ብሎ መብላት ይቻል እንደሁ  እንጂ ሆቴል ተዝናንቶ መቀመጥ እና መብላት ቢያንስ  ለአንድ ወር የተከለከለ ሆንዋል። የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት ጠበቅ ያለ የዝዉዉር እገዳ ለረዘም ላለ ጊዜ መተግበር አለበት እያሉ እየወተወቱ ነዉ። በጀርመን ሕዝብ በሚበዛባቸዉ አካባቢዎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈና ማድረግ የግድ ነዉ። ይህ የኮሮና ወረርሽን ለሁለተኛ ጊዜ የተቀሰቀሰዉ ደግሞ አሁን የበጋዉ ወራት አልቆ ክረምት መግብያ ላይ ባለንበት የዛፍ ቅጠሎች አረንጓዴ ቀለማቸዉን ትተዉ ወደ ወርቅማ እና ቀጋ በሚመስሉበት ጊዜ ነዉ። የቀኑ የምትፈንጥቀዉም ፀሐይ ብርሃንዋን ደማቅ ሰማዩም ጥርት ያለ ሰማያዊ ቢመስልም ብርዱ ካፖርታ ያስደርብ ጀምሮአል። ዛሬ ከካፖርታዉ በላይ ጭንብል አጥልቆ ማር ቆራጭ መስሎ መንቀሳቀሱ የተለመደ ሆንዋል። ወሩ አሁን ጀርመናዉያን ዓመት ሙሉ የሚጠብቁት የሚወዱት የገና በዓል መዳረሻ ነዉ። በታሪክ ከ 500 ዓመት በላይ እንደሆነዉ የሚነገረዉ የጀርመናዉያን የገና ገበያ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ የጀርመን ፊደራል ግዛቶች በየከተሞቻቸዉ እንደማይዘረጉ ይፋ እያደረጉ ነዉ። የጀርመን ፓርላማ ግን ገና በጉዳዩ እየመከረ ቢሆንም በርካታ ዜጎች በተለይ መዲና በርሊን ላይ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዳግም የፀደቀዉን የዝዉዉር እገዳ ሕግን በመቃወም የተቃዉሞ ሰልፍ ይታያል። በአዉሮጳ የኮሮና የሁለተኛ ዙር ወረሽኝ ማገርሸት እና በጀርመን በከፊል የዝዉዉር እገዳ መጣል የማኅበረሰቡን መስተጋብሮች ባህላዊ እንቅስቃሴ ያህል ጎድቶት ይሆን?  ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ የኮሮና ወረርሽኝ በተለይ በጀርመን የሚደረገዉን ጥንቃቄ ብሎም በኤኮኖሚ ባህላዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያሳደረዉን ተጽኖ በተመለከተ በዘጠኝ ምዕራፍ  በአማርኛ ሰፊ ጽሑፍን አቅርበዋል። 

BdT Deutschland Weihnachtsbaum Dortmund
ምስል Bernd Thissen/dpa/picture alliance

የገና በዓልን እንኳን ደህና መጣህ ሲል በዓሉ ከመድረሱ ከአራት ሳምንታት በፊት ጀምሮ በጀርመን ከተሞች የሚዘረጋዉ ባህላዊዉ የገና ገበያ የኮሮና ወረርሽኝን ይበልጥ ሊያስፋፋ ይችላል በሚል በርካታ የጀርመን ከተሞች ገበያዉ ዘንድሮ እንደማይኖር እያሳወቁ ነዉ። በጀርመን በለሁለተኛ ጊዜ የተንሰራራዉን የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ተከትሎ በከፊል ተግባራዊ እየተደረገ ያለዉ የተጣለዉ የዝዉዉር እገዳ ቀነ ገደብ ከአስር ቀን በኋላ ይጠናቀቃል። የትኞቹ ከተሞች አልያም ፌደራል ግዛቶች ይህን ባህላዊ ገበያ ይዘረጉ ይሆን?  ገበያተኛ ሕዝብስ ባህላዊዉን የገና በዓል ያለምንም የኮሮና ስጋት ይጎበኝ ይሆን ? የምናየዉ ይሆናል! ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህን ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማድመቻ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ