1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮሮና ያጠላበት የፈረንጆቹ ገና እና አዲስ ዓመት   

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 2013

ዋናዉ አላማችን በጤና መቆየት እና ሕዝቡን መታደግ ነዉ ። ከፍተኛዉ ግባችን ደግሞ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን በተቻለዉ ሁሉ በአፋጣኝ መቀነስ ነዉ። ይህን ግብ ልንደርስ የምንችለዉ በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ልንገኛቸዉ የምንፈልጋቸዉን ሰዎች ቁጥር፤ በስርነቀል እርምጃ ማቋረጥ አልያም መቀነስ ስንችል ነዉ።

https://p.dw.com/p/3msjv
BG Advent | Weihnachten in Coronazeiten | London Weihnachtsmann mit Maske
ምስል Jonathan Brady/PA Wire/dpa/picture alliance

የገና በዓልና የአዲስ ዓመት ድግስ ኮሮና አደናቅፎታል

« ዋናዉ አላማችን በጤና መቆየት እና ሕዝቡን መታደግ ነዉ ። ከፍተኛዉ ግባችን ደግሞ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን በተቻለዉ ሁሉ በአፋጣኝ መቀነስ ነዉ። ይህን ግብ ልንደርስ የምንችለዉ በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ልንገኛቸዉ የምንፈልጋቸዉን ሰዎች ቁጥር፤ በስርነቀል እርምጃ ማቋረጥ አልያም መቀነስ ስንችል ነዉ። ይህ ደግሞ ማድረግ ያለብን የጤና መሰረታችን ሳይንኮታኮት ፤ በአፋጣኝ ነገ ዛሬ ሳንል መፈፀም ስንችል ነዉ።»

የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር፤ በጀርመን አሳሳቢ እየሆነ የመጣዉን የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት ብሎም  በኮቪድ 19 በሽታ የሚያዘዉ ሰዉ ቁጥር መጨመርና የሟቾች ቁጥር መብዛትን ተከትሎ ለሕዝባቸዉ ካደረጉት ንግግር የተወሰደዉን ነበር።  ፕሬዚዳንቱ ለጀርመናዉያን ባደረጉት ንግግር የኮሮና ጉዳይ መራራ እዉነት ሆንዋል  ስለዚህም ጥንቃቄ ዉሰዱ ሲሉም አንዴም በመማፀን አንዴም በማዘን ተናግረዋል። ጀርመናዉያን በፀጥታ እና በጥሞና ከቤተሰብ ጋር ተሰባስቦ በድምቀት የሚያከበር በዓል የሚሉት የገና ዓመታዊዉ በዓል ዘንድሮ የኮሮና በትር አጥልቶበታል። የፈረንጆቹ ገና በዋለ በሳምንቱ የሚገባዉም አዲሱ የፈረንጆቹ 2021 እንደወትሮ በጭፈራ በርችት እና በየጎዳናዉ በትልልቅ የሙዚቃ ድግስ ላይከበር ነዉ። ይልቁንም ጥብቅ የዝዉዉር የገደብ ሕግ ተጥሎአል። ከሠላሳ አምስት ዓመት በላይ  በጀርመን ነዋሪ የሆኑት እና መዲና በርሊን በአንድ የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያ የቴክኒካል ቁሶች ሽያጭ ክፍል ዉስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ መስፍን አማረ፤ የፈረንጆቹን ገና ከጀርመናዉያን ቤተሰቦቻቸዉ እና እዚሁ ጀርመን ባቫርያ ነዋሪ ከሆኑት ከወንድማቸዉ እና ቤተሰባቸዉ ጋር ነበር።  

BG Advent | Weihnachten in Coronazeiten | Schoko-Weihnachtsmänner mit Maske
ምስል Christoph Hardt/Geisler-Fotopress/picture alliance

የምጣኔ ሐብት ባለሞያዉ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ጀርመንን ለሁለት የከፈለው ግንብ ከመፍረሱ ከአንድ ዓመት በፊት የነጻ ትምሕርት እድልን አግኝተው ነዉ ወደ ምሥራቅ ጀርመን የመጡት። በመጀመርያ የቋንቋ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ እና የመጀመርያ ዲግሪያቸዉን በምስራቅ ጀርመን ካገኙ በኋላ  በኋላ ለቀጣይ ትምህርት ምዕራብ ጀርመን በርሊን ሄደው እዚያው በርሊን ተማሩ የዶክትሪት ማዕረጋቸዉን አገኙ ከዓመታት ጀምሮ ማርቸዲስ ቤንዝ በሚባለዉ የመኪና አምራች ኩባንያ ዉስጥ እያገለገሉ ናቸዉ።   

Deutschland | Weihnachten in der Coronakrise 2020
ምስል SvenSimon/picture alliance

የዛሬ ሳምንት ሃሙስ ምሽት የሚጀምረዉ የጀርመናዉያኑ የገና በዓል ከመዋሉ ከአራት ሳምንት በፊት በጀርመን በሚገኙ ከተሞች ሁሉ የሚዘረጋዉ የገና ገበያ ዘንድሮ ከስንት መቶ ዓመታት በኋላ ሳይዘረጋ መብቃቱ ጀርመናዉያንን አሳዝኖአል። የጀርመናዉያኑ የገና ገበያ በማኅበረሰቡ ተወዳጅ ከመሆኑ ባሻገር ከተለያዩ የዓለም ሃገራት የሚመጡ የሃገር ጎብኝዎችን ማርኮ ወደ ጀርመን የሚስብ ነበር። ዘንድሮ ኮሮና የጀርመንን ብቻ ሳይሆን የአዉሮጳ ሃገራትም ብሎም የዓለም ሃገራትን ኤኮኖሚ አናግቶአል። በጀርመኑ የገና ገበያ ላይ የሚሸጠዉ በቀረፋና ቅርንፉድ የተፈላዉ ጣፋጭ ቀይ ወይን ገበያዉ ላይ ሽታዉ ሲያዉድ ገናን መጣሁ መጣሁ አዲስ ዓመት ደረስኩ ደረስኩ  እያለ የየከተማዉን የየቀበሌዉን አዉድ በዓል በዓል የሚያሰኝ ነበር። ኮሮና ጥላዉን ባሳረፈበት ደማቁ የገና እና አዲስ ዓመት በዓል ዘንድሮ ቀዝቀዝ በማለቱ ጀርመናዉያን አዝነዉ ይሆን?  በርሊን ነዋሪ የሆኑት አቶ መስፍን አማረ እንደሚሉት በዚህ ደማቅ ወቅት ቤተሰብን ሄዶ መጎብኘት ካልተቻለና ቤት ያፈራዉን አብሮ መቋደስ ካልተቻለ ማሳዘኑ አይቀርም። 

BG Advent | Weihnachten in Coronazeiten | Schoko-Weihnachtsmänner mit Masken
ምስል Nicolas Armer/dpa/picture alliance

ጀርመን የኮቪድ 19 በሽታን ለመከላከል የቀረበዉን ክትባት እሰጣለዉ ካለችበት ቀደም ብላ ለመስጠት እየተዘጋጀትች መሆኑን የሚያሳይ ዘገቦች እየወጡ ነዉ። የዚህ ደግሞ ምክንያቱ በሃገሪቱ በአንድ ቀን ብቻ ማለትም በ 24 ሰዓታት ብቻ በኮቪድ 19 በሽታ ከ 900 በላይ ሰዎች በመሞታቸዉ ምክንያት ነዉ። እስካሁን በጀርመን በኮቪድ 19 የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ 23,500 በላይ ሆንዋል። እንድያም ሆኖ ጀርመናዉያን አዲሱ የፈረንጆቹ 2021 ዓመት  ኮሮናን አባሮ የጤና ዓመት እንዲሆን በመመኘት ፤ የገናን በዓል በርጋታ ለማክበር በጉጉት እየጠበቁ ነዉ።

በጎርጎሮሳዊውን የቀን ቀመር የሚከተለዉ ዓለም በድምቀት የሚያከበረዉ የገና ወይም የክርስቶስ የልደት በዓል፤ ምሽት ላይ በቤተ-ክርስትያን የፀሎት ሥነ-ስርዓት ይጀምራል። ዘንድሮ ግን ያዉ የፀሎት ስነ-ስርዓቱ በኢንተርኔት አልያም በቴሌቭዥን በመታገዝ የሚሰራጨዉን ሁሉም በየቤቱ ነዉ የሚከናወነዉ። በአብዛኛዉ ጀርመናዉያን ቤት የገና ዛፍ ማለት ጥዱ ተሽቆጥቁጦ ቆምዋል።  የገና አባት የተባለዉ  ባለነጭ ሪዛሙ ሽማግሌም ስጦታዉን  አሸክሞ፤ እንደሚመጣ  ቤተሰብ ልጅ ወዳጅ ዘመድ ሁሉ የተረት ተረት ያህል በማመን ይጠብቃል። በተለይ ሕጻናት ልጆች እየጠበቁ ነዉ።  በጀርመን በዓሉ የሚከበረዉ በአዉሮጳዉያኑ ታህሳስ 24 ምሽት ጀምሮ ሲሆን፤ በነጋታዉ ታህሳስ 25 ቀዳማዊ ገና፤ ታህሳስ 26 ቀንን ደግሞ ዳግማዊ ገና ሲሉ በተከታታይ ቀናት ከቤተሰብ በመሆን ያከብሩታል ። ማለትም ሁለት ቀን ተኩል ገደማ አካባቢ በዓሉ ይከበራል።  

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ