1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህል ሎሬት ተሸላሚው ተወዛዋዥ

እሑድ፣ ጥር 9 2013

ተውዝዋዥና የውዝዋዜ አሰልጣኝ  ባለሙያው መላኩ በላይ፤ ለበርካታ አመታት ፈንድቃና ኢትዮ-ከለር የሚል የሙዚቃ ባንድ በመመስረት በተለያዩ ሀገራት ተዘዋውሮ  የኢትዮጵያን ባህል አስተዋውቋል። በዚህ ስራውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል። በተሸኘው የጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም ደግሞ የኔዘርላንዱ« ፕሪንስ ክላውስ ፋውንዴሽን»የባህል ሎሬት ተሸላሚ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/3nzbj
Melaku Belay 2020 Prince Claus  Laurat
ምስል Handout

መዝናኛ፦ «ተውዝዋዥና የውዝዋዜ አሰልጣኝ ባለሙያ መላኩ በላይ»


ተውዝዋዥና የውዝዋዜ አሰልጣኝ  ባለሙያው መላኩ በላይ ለበርካታ አመታት በሙያው ሰርቷል።ፈንድቃና ኢትዮ-ከለር የሚል የሙዚቃ ባንድ በመመስረትም በተለያዩ ሀገራት ተዘዋውሮ  የኢትዮጵያን ባህል አስተዋውቋል።በዚህ ስራውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል። በተሸኘው የጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም መጨረሻ ደግሞ  በባህል ዘርፍ ጥሩ ለሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች በየአመቱ ሽልማት የሚሰጠው የኔዘርላንዱ« ፕሪንስ ክላውስ ፋውንዴሽን»የባህል ሎሬት ተሸላሚ ሆኗል።
ተወዛዋዥ ወይም እሱ እንደሚለው  «የጭፈራ ባለሙያ»ው መላኩ በላይ ከ20 ዓመታት በላይ በሙያው የሰራ የጥበብ ሰው ነው።ይህንን የጥበብ ስራ በፍቅር ሲጀምር  በነበረው ድንቅ ችሎታ ከሰዎች ከሚያገኘው ምስጋና፣አድናቆትና አነስተኛ ሽልማት ውጭ ምንም ክፍያ አልነበረውም።በዚህ ሁኔታም በመሀል አዲስ አበባ፤ ካሳንችስ አካባቢ በሚገኘው «ፈንድቃ»  የባህል ጭፈራ ቤት በነፃ  ሰርቷል ።
መላኩ ፤ምንም እንኳ ክፍያ ባያገኝበትም በዚሁ የባህል  ቤት ባንኮኒ ስር እያደረ የሚወደውን ስራ ለዓመታት ቀጠለ ።ስራውን የተመለከቱ የፈንድቃ ታዳሚዎች የሚሰጡትን አነስተኛ የገንዘብ ሽልማትና በየሰፈሩ እየዞረ በማስተማር የሚያገኘውን ጥቂት ገንዘብ በማጠራቀም ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት የፈንድቃ የባህል ማዕከል ባለቤት ለመሆን በቅቷል።
ይህ የባህል ማዕከል ሙያውን ከማሳደግ በተጨማሪ ስራውን በውጭ ሀገራት ለማቅረብም እድል ፈጥሮለታል።
«ዜማ ካለ ጭፈራ አለ» የሚለው መላኩ ፤ለየት ያለ የአጨፋፈር ስልት የሚከተል  የቁሳቁስ መጋጨት በሚፈጥሩት ድምፅ ሳይቀር ድንቅ ጭፈራ ማሳየት የሚስችል ለየት ያለ ተሰጦ ያለው ተወዛዋዥ ነው።በዚህም በባህል ማዕከሉና በተጓዘባቸው የውጭ ሀገራት የረባ ጥሪት ባይቋጥርም አድናቆትን አትርፏል።ያም ሆኖ በሄደበት ሀገር መቅረትን  አልመረጠም።በዚህም ለጥበቡና ለሀገሬ ኢትዮጵያ ያለኝ ፍቅርና ታማኝነት ገልጨበታለሁ ይላል። 
ኢትዮ-ከለር በሚል ስም በመሰረተው የሙዚቃ ባንድ አማካኝነት የኢትዮጵያን ባህል ለተለያዩ የዓለም ሀገራት ተዘዋውሮ በማስተዋወቅ ላይ የሚገኘው መላኩ፤በፈንድቃ  የባህል ማዕከልም ከሙዚቃ ባሻገር የስዕል፣የግጥምና ሌሎች የጥበብ ስራዎችንና ዝግጅቶች እንዲቀርቡም በማድረግ ላይ ይገኛል።በዚህ ስራውም  በጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም መጨረሻ  በየአመቱ በባህል ዘርፍ ጥሩ ለሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች ሽልማት የሚሰጠው የኔዘርላንዱ« ፕሪንስ ክላውስ ፋውንዴሽን»የባህል ሎሬት ተሸላሚ ሆኗል።
በዚህ ውድድር በባህሉ ዘርፍ አወንታዊ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ሰባት ሀገሮች የተመረጡ ሲሆን ከአፍሪቃ ኢትዮጵያና ጋና ውድድሩን ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ አራት ሽልማቶች ለፓኪስታን፣ ለቱርክ፣ ለኮሎምቢያ፣ ለቶንጋና ለአርጀንቲና  ተሰጥቷል።
የባህል ሎሬት ተሸላሚው መላኩ በላይ፤ ሽልማቱን ኔዘርላንድ ሄዶ የሚቀበል ቢሆንም በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ሀገር ቤት በሚገኜው ኢምባሲ ነበር የሽልማት ሥነ-ስርዓቱን የታደመው።መላኩ፤ ጥበቡንና ኢትዮጵያን  ሽልማቱ የኔ ብቻ ሳይሆን የፈንድቃ ታዳሚዎች፣ የጥበቡ አፍቃሪያንና የመላው ኢትዮጵያውያን ነው ይላል። 
የጥበብ ባለሙያው ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ የበጎ ሰው ሽልማትን፣ከፈረንሳይ መንግስት የክብር መዳሊያን፣ከአረብ ኤሜሬትስ ዋንጫን ፣ባለፈው ዓመት በሞሮኮ በተካሄደው ስድስተኛው «ቪዛ ፎር ሚዩዚክ »በተባለው ፌስቲቫል ላይም  ምርጥ የአፍሪቃ የጥበብ ሰው በሚል የዋንጫ ተሸላሚ ነበር።
ከሽልማቶቹ በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ሙያውን በቀላሉ «ይረዱታል ድጋፍም ያደርጉኛል»ይላል። ያም ሆኖ፤ በሀገር ቤት ለሙያው የሚሰጠው ቦታና ክብር  አሁንም ዝቅተኛ  መሆኑን ይናገራል።ይህ ቁጭትም እሱ በፕሬዝዳንትነት የሚመራውን የኢትጵያ ተወዛዋዦች የጥበብ ማኅበርን ከዓራት አመት በፊት እንዲመሰርት አድርጎታል።ሙያው በሚቀጥለው ትውልድ እዲከበር ለማድረግም የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጿል። 

Melaku Belay 2020 Prince Claus  Laurat
ምስል Handout
Melaku Belay 2020 Prince Claus  Laurat
ምስል Pressefoto

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ