1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን 398.7 ቢሊዮን ብር ዕዳ የተረከበው ኮርፖሬሽን ማነው?

ዓርብ፣ ነሐሴ 21 2013

የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ስድስት መንግሥት የልማት ድርጅቶች ያለባቸውን 398.7 ቢሊዮን ብር ዕዳ ባለፈው ሳምንት ተረክቧል። በየካቲት የተቋቋመው ኮርፖሬሽን ያስተዳድራቸዋል የተባሉ ሰባት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ 780 ቢሊዮን ብር ወይም 19.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ዕዳ አለባቸው።

https://p.dw.com/p/3zU68
Äthiopien Commercial Bank of Ethiopia in Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ግዙፍ ኃላፊነት የተጣለበት የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን

ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ከተዘፈቁ ሰባት የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል ስድስቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደሩትን 398.7 ቢሊዮን ብር አዲስ የተቋቋመው የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ባለፈው ሳምንት በይፋ ተረክቧል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ኢትዮ-ኢንጂኔሪንግ በሚል ስያሜ እንደገና የተዋቀረው የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዕዳቸውን ለአዲሱ ተቋም ካዛወሩ መካከል ናቸው። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን በተመሳሳይ ዕዳቸው ለአዲሱ ተቋም ተዛውሮላቸዋል። 

ስድስቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ አበዳሪያቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴር ሥምምነቱን መፈራረማቸውን ሚኒስቴር ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ይኸ እርምጃ ግን የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹን ሙሉ በሙሉ ከዕዳ ነጻ አያደርጋቸውም። ለምሳሌ ያክል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወሰደው ብድር ወደ ዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የተዛወረው 50 በመቶው ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከጎርጎሮሳዊው 2004 እስከ 2016 ባሉ አመታት ከንግድ ባንክ የተበደረው ብድር ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በ2017 ዓ.ም. የተበደረው በከፊል እንደተዛወረለት አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመግለጫው "የዕዳ ስረዛው ተቋሙን 191.8 ቢሊየን ብር ከነወለዱ የሚያስቀርለት ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት 17.25 ቢሊየን ብር እንዲሁም በቀጣይ በጀት ዓመት 18.81 ቢሊየን ብር ወለድ ከመክፈል ታድጎታል" ብሏል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያለባቸውን ዕዳ ለአዲሱ ኮርፖሬሽን የተዘዋወረበትን መንገድ "የወረቀት ሥራ" ሲሉ ይገልጹታል። አቶ አብዱልመናን "ዕዳው ከእነዛ ድርጅቶች ይፋቅ እና ወደዚህ ድርጅት ዕዳነት ይዘዋወራል። ግን ለእነዛ ድርጅቶች ላበደረው ለንግድ ባንክ ወይም ለውጪ አበዳሪዎች በቀጥታ ክፈል አይባልም። ነገሩን መሸፋፈን ነው። እንጂ ክፈል ቢባል ከየት አምጥቶ ነው የሚከፍለው? የወረቀት ሥራ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የገንዘብ ምኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ሥምምነቱ በተፈረመበት ዕለት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዕዳ አከፋፈል ላይ የተደረገውን ማስተካከያ የአገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያውን ለመተግበር ትልቁ ምዕራፍ እንደሆነ መናገራቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መግለጫ ላይ ሰፍሯል። 

በመግለጫው መሠረት እርምጃው የፋይናንስ ዘርፉን በማረጋጋት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የፋይናንስ ይዞታ በማሻሻል እና ዕዳቸው በመንግሥት ላይ የሚፈጥረውን ተጓዳኝ ጫና በማቃለል አጠቃላይ ኤኮኖሚውን ለማረጋጋት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው ወደዚህ [የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን] ይመጣል። ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የሚነጋገረው ነገር አይኖርም ማለት ነው። ከዚህ ጋር ይነጋገራል ማለት ነው። ይኸ ድርጅት ደግሞ ወዲያው ይከፍለዋል ማለት አይደለም። የበፊቱ የብድር አከፋፈል ሥምምነት ሊሰረዝ ይችላል። ለምሳሌ በአምስት አመት የነበረ ብድር ይሰረዝ እና ወደ 20 አመት 30 አመትም ሊደረግ ይችላል" የሚሉት አቶ አብዱልመናን "የወረቀት ሥራ ነው የተሰራው እንጂ በተጨባጭ የገንዘብ ምንጩን መጠነ ሰፊ ማስተካከያ አልተካሔደም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ ገቢራዊ ማድረግ የጀመረው አገር በቀል የምጣኔ ሐብት ማሻሻያ ዋንኛ ትኩረቶች መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሽያጭ ወደ ግል ማዛወር ይገኝበታል። በእርግጥ ውሳኔው ኢሕአዴግ ከመፍረሱ በፊት በምኒስትሮች ምክር ቤት የተላለፈ ነው።

Äthiopien Omo Kuraz Zuckerfabrik
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን በተመሳሳይ ዕዳቸው ለአዲሱ ተቋም ተዛውሮላቸዋል። ምስል Ethiopian Sugar Corporation

አሁን የስድስቱን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ ወደ አዲሱ ተቋም ለማስተላለፍ የተወሰደው እርምጃ የሒሳብ መዝገባቸውን በማስተካከል ይኸንንው ወደ ግል የማዛወር ሒደት ለማሳካት ሊሞከር እንደሚችል አቶ አብዱልመናን ይናገራሉ። ይሁንና ባለሙያው እንደሚሉት "ውጤታማ አይደሉም" የሚል ብርቱ ትችት ለሚደርስባቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኹነኛው መፍትሔ አይደለም።  

"ሁለተኛ ተቋም ከመፍጠር እዚያው ላይ ማሻሻያውን ማድረግ ይሻል ነበር። መንግሥት የፈለገው ዋናዎቹን ተበዳሪዎች የሒሳብ መዝገብ ንጹህ እንዲሆን ነው። የሒሳብ መዝገባቸውን ንጹህ ካልሆነ፤ መበደር ቢፈልጉ ወይም ለመሸጥ ቢፈለግ እንኳ ብዙ ዕዳ ስላለባቸው ቀላል አይሆንም። ስለዚህ ሁለተኛ ተቋም ተፈጠረ እና የእነሱን ዕዳ ወደዚያ አዞሩ። ስለዚህ [የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን] የሒሳብ መዝገብ የማሳመር ጉዳይ እንጂ የእነሱን የፋይናንስ ይዞታ ያሻሽለዋል የሚል ዕምነት የለኝም" ሲሉ አቶ አብዱልመናን አስረድተዋል።  

ኮርፖሬሽኑ ማነው?

የዕዳ እና የሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የምኒስትሮች ምክር ቤት በጥር ወር ካሳለፈው ውሳኔ በኋላ በየካቲት 2013 ዓ.ም. የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው። ኮርፖሬሽኑ ሲቋቋም 570 ቢሊዮን ብር የተፈቀደለት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 142 ቢሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና በዓይነት የተከፈለ ነው።  

በማቋቋሚያ አዋጁ እንደሰፈረው ኮርፖሬሽኑ "ከገንዘብ ሚኒስቴር በሚደርሰው ዝርዝር መሰረት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ ይረከባል፤ ከኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ የሚመደብለትን ካፒታል፤ ከንግድ ሥራ እንቅስቃሴ የሚያገኘውን ገቢ እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች የሚመደብለትን ገንዘብ በመጠቀም ይህንኑ ዕዳ ይከፍላል።" 

ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል የሚተላለፉ እንዲሁም የሚፈርሱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ንብረት እና ዕዳ በመረከብ ማጣራት እና ማስተዳደርም በዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ጫንቃ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነው። ይኸው ኮርፖሬሽን "ከመንግሥት የሚመደበው ካፒታል እና ሌሎች ገቢዎች ለዕዳው ክፍያ እስከሚውል ድረስ አዋጭነታቸው በተረጋገጠ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲውል ያደርጋል።" ከዚህ በተጨማሪ ለአበዳሪ ተቋማት የዕዳ ማሰባሰብ እና ማስተዳደር አገልግሎት ይሰጣል። 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉት ዶክተር ተገኘ ወርቅ ጌጡ የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሊቀ-መንበር ሆነው ተሾመዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር "የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የዕዳ ጫና በማቃለል ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁ" ያግዛል ላለው የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን አቶ ሙሉአለም ጌታሁን በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ተሾመዋል። 

ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የተዘፈቁ ሰባት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የማስተዳደር ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ባለፈው ሳምንት ዕዳቸውን ለኮርፖሬሽኑ ካዘወሩ ስድስት ተቋማት በተጨማሪ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሰባተኛው የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው። የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው መጋቢት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት እነዚህ ሰባት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ 780 ቢሊዮን ብር (19.5 ቢሊዮን ዶላር) የሚጠጋ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ዕዳ አለባቸው።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹ "በዋናነት ከንግድ ባንክ የተበደሩ ናቸው። በፊት ቀጥታ ግንኙነታቸው ከንግድ ባንክ ነበር። ዕዳም መክፈል ያለባቸው ለንግድ ባንክ ነው። ውላቸውም ከንግድ ባንክ ነበር። አሁን ይኸ አዲስ ኮርፖሬሽን በአበዳሪው እና በተበዳሪው መሀል በሚገባበት ሰዓት ዋናውን የአበዳሪውን ዕዳ ኃላፊነት ይወስዳል። ምን አልባት በአዲስ ውል። ከመጀመሪያ ተበዳሪዎቹ መካከል ደግሞ ሁለት አይነት አማራጭ አለው። አንደኛ ባለቤት መሆን ነው። ባለቤት የሆንክ እንደሆነ እንደ አበዳሪ አታስጨንቅም። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ለእነሱ የረዥም ጊዜ አበዳሪ መሆን ነው" ሲሉ ሊኖረው የሚችለውን ግንኙነት አስረድተዋል።

አቶ አብዱልመናን የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ሰባቱ ተቋማት ያለባቸውን ብድር ሰብስቦ ሲረከብ የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹን ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ወደ ግል ለማዛወር መንገድ ቢጠርግም ይዞት የሚመጣው ሥጋት መኖሩን ይናገራሉ። 

"ከፌድራል መንግሥት በጀት መድቦ የሚሰረዝ ከሆነ መሰረዝ ነው። ችግሩ እዚያው እያለ የሚሸጥ ከሆነ መሸጥ ነው። አሁን [ዕዳው] አንድ ቦታ ተሰብስቧል።" የሚሉት አቶ አብዱልመናን ከክትትል እና ቁጥጥር ሊርቅ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። ኮርፖሬሽኑ የተከማቸውን ዕዳ መክፈል ቢያቅተው ትልቁ አበዳሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጎጂ ሊሆን እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። 

የስድስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ ሰብስቦ የተረከበው የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ይኸን ጨምሮ በተቋሙ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች እና ስለሚከተላቸው አሰራሮች ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም። አቶ አብዱልመናን ግን ጉዳዩ በቂ ውይይት እና ክርክር ሳይደረግበት ተግባራዊ መሆኑ ተገቢ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ። 

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ