1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን ሚሊዮኖች የተመለከቱት የሳሮን ደግነህ ፊልም

እሑድ፣ ጥቅምት 14 2014

ወጣት ሳሮን ደግነህ  በትወና ሙያ ላይ የተሰማራች ወጣት ስትሆን በጀርመን በርካታ ትያትሮችን ፊልሞችን እንዲሁም የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችን ሰርታለች።በጎርጎሪያኑ 2017 ዓ/ም በባርሴሎና ፕላኔት የፊልም ፌስቲቫል በአጫጥር ፊልሞች ምርጥ ተዋናይ ተብላ ተሸልማለች። ሳሮን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሆሊዩድ ፊልሞች የመተወን ዕቅድ አላት። 

https://p.dw.com/p/427eP
Saron Degineh Deutsche Schauspielerin
ምስል Privat

ሳሮን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሆሊዩድ ፊልሞች የመተወን ዕቅድ አላት


ወጣት ሳሮን ደግነህ  በጀርመን በትወና ሙያ ላይ የተሰማራች  ወጣት ስትሆን በርካታ ትያትሮችን ፊልሞችን እንዲሁም የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችን ሰርታለች።በጎርጎሪያኑ 2017 ዓ/ም በባርሴሎና ፕላኔት የፊልም ፌስቲቫል በአጫጥር ፊልሞች ምርጥ ተዋናይ ተብላ ተሸልማለች።በትወና ክህሎቷ ተስፋ የተጣለባት  ይቺ ወጣት  የዛሬዋ የመዝናኛ ዝግጅት እንግዳችን ነች። 
የ19 ዓመቷ ወጣት ሳሮን ደግነህ  የትወና ሙያን የጀመረችው በልጅነት ዕድሜዋ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለች በትምህርት ቤት የትያትር  ክበብ ውስጥ  ነበር ። ጀርመን በርሊን ከተማ ተወልዳ ያደገችው ሳሮን አባቷ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ እንደሚሉት በልጅነቷ ፈጣን ያየችውን ቶሎ የምትገገነዘብ እና የተገነዘበችውንም  ለሌሎች የምትገልፅ ናት። በማርሻል አርትም ጁዶ ከዚያም ጅትሱ የተሰኘውን  ስፖርት ተምራ ብርቱካናማውን ቀበቶ ለማግኘት ጊዜ አልፈጀባትም። ጊታር መጫወት የጀመረችውም ገና የሰባት  ዓመት ልጅ ሆና ነው።ይህንን የነብስ ጥሪዋን የተመለከቱት ወላጆቿ ታዲያ ከመደበኛ ትምህርቷ ጎን ለጎን የትያትር እና የዳንስ ትምህርት ቤት ገብታ ተሰጦዋን የበለጠ እንድታዳብር አደረጉ። ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችም በጀርመን ሀገር  የትወና ስራ የሚሰራው በአገናኝ ድርጅቶች በኩል ነውና  ይህንን ህልሟን ዕውን ለማድረግ ያመሩት የፊልም ስራ ወደ ሚያገናኙ ድርጅቶች ነበር። 
ያም ሆኖ የጓጓችለትን የትወና ስራ ቶሎ ማግኘት  ቀላል አልነበረም።
 ከብዙ ውጣ ውረድ  በኋላ ግን በ2017 ስቱፒድ ስማርት ፎን ቴራፒ፣ ጀንትል ስኪል ፣ ዴር ክርሚናሊስት፣ ኖት ሩፍ አው ዲ ካንተን  ጨምሮ ከአስር በላይ  የቴሌቪዥን ፊልሞችን እና ተከታታይ የቴሊቪዝን ድራማዎችን ሰርታለች።በእነዚህ ፊልሞች  ጥሩ የትወና ብቃቷን ያሳየችው ሳሮን ፤ ዶቼ ቲያትር በመባል በሚታወቀው ትልቁ የጀርመን ትያትር ቤትም ወደ ሁለት ዓመት ገደማ በተለያዩ ትያትሮች ላይ ተውናለች። የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን እንዲሁም በአንዳንድ የጀርመን የገበያ አዳራሾች ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁ ፎቶዎቿን ማየትም እየተለመደ መጥቷል። በቅርቡም  «ዳስ ኤርስተ»በተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ የተላለፈውን «ቢሊ ኩክኩክ አንጌሴልት» በሚል ርዕስ እሷ የተወነችበት የቴሌቪዝን ፊልም በአጭር ጊዜ ውስጥ  ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል። 90 ደቂቃ የሚፈጀው ይህ ፊልም በዝቅተኛ ኑሮ የሚገኙ እና ስደተኛ ወጣቶችን አሰባስቦ በሚያሰለጥን አንድ የቦክስ አሰልጣኝ የሚያጠነጥን ሲሆን ሳሮን በዚህ ፊልም በሁለተኛ መሪ ተዋንያንነት ሳሚ የምትባል እናትና አባቷን ያጣች እና ጥሩ የቦክስ ችሎታ ያላት አንዲት የአፍጋንሲታን ስደተኛ ወጣትን ወክላ ነው የተወነችው። የፊልሙ ውጤታማ መሆን ለሳሮን ጥሩ ስሜት ፈጥሮላታል።
«ያንን በመስማቴ በጣም ተደስቻለሁ።ብዙ ጓደኞቼ እና ዘመዶቼ ፊልሙን አይተውታል።ያ በእርግጥ እኔን አስደሰቶኛል።ለዚህ ፊልም ብዬ ተጨማሪ የቦክስ ስልጠና ወስጃለሁ። በእርግጠኝነት ብዙ ሥራ ነበር። እንዲሁም የኮሮና የእንቅስቃሴ ገደብም ብዙ  ነገር  ቀይሯል። በዚህ ሁኔታ ጥሩ ሆኖ በመታየቱ የበለጠ ደስተኛ ነኝ።»
በዚህ ፊልም ከጀርመናዉያንም ይሁን ከኢትዮጵያዉያን ያገኘችው ምላሽ የሚያበረታታ ሲሆን የትወና ብቃቷን ያደነቁ ህትመቶች መኖራቸውንም ገልጻለች።
«በእውነት በጣም ጥሩ ነበር። በመላው የጀርመን  ቤተሰቦቼ  ዘንድ  ፊልሙ በጣም ጥሩ፣በጣም  የሚወደድ  እና በጣም ልብ የሚነካ ሆኖ ተገኝቷል። የአፍጋኒስታንን ወጣት ሴት  ወክዬ በመጫወቴ ከኢትዮጵያዊያውያን ያገኘሁት ጥሩ ምላሽም አስደናቂ ነው። በእርግጥ ስለ ቢሊ ኩኩክ ፊልም ሀያሲያንን  ጨምሮ  መፅሄቶችና ጋዜጦችም ብዙ ፅፈዋል። ጥሩ ስለመተወኔ የፃፈ መፅሄትም አለ። ያ በጣም አስደስቶኛል።»ስትል ገልጻለች።
የምትጫወታቸው ገፀ ባህሪያት ጠንካራ ባህሪ ያላቸው ሲሆኑ አባቷ ዶክተር ፀጋዬ እንደሚሉት  እውነተኛ ባህሪዋም ቢሆን ጠንካራ፣ ተስፋ የማትቆርጥ፣ በራሷ የምትተማመን ለሰው ልጆች እኩልነት ዋጋ የምትሰጥ  እና ሰው አክባሪ ነች። ከጀርመናዊት እናቷ  እና ከኢትዮጵያዊ  አባቷ የወረሰችው የቀይ ዳማ መልኳ ለየት ያሉ ገፀ ባህሪያትን ለመጫወት ዕድል ቢፈጥርላትም በሌላ በኩል የምትጫወተውን ገፀ-ባህሪ ገድቦባታል ይላሉ። ያ በመሆኑ በአብዛኛው የምትጫወተው የሌላ ሀገር ቋንቋና ባህል ያላቸውን ገፀ-ባህሪያት በመሆናቸው ልፋትና ጥረቷንም እጥፍ  አድርጎታል።  
«አዎ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ በአንድ ተከታታይ ፊልም ውስጥ  ከኢራቅ የመጣች ሴት ልጅ ሆኘ ነበር የምጫወተው።በመሆኑም ሙሉውን ፅሑፍ በአረብኛ መናገር ነበረብኝ። አረብኛ ደግሞ ጨርሶ መናገር አልችልም። እናም መጀመሪያ ሁሉንም ነገር መማር ነበረብኝ። በተጨማሪም የኢራቅ ዘዬ ያለው አረብኛ በመሆኑ  ያ በእርግጥ ፈታኝ ነበር። »በማለት የሌላ ባህልና ቋንቋን ወክሎ መጫወት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግራለቸ።
መቶ ፐርሰንት ጀርመን መቶ ፐርሰንት ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትለው ሳሮን ካደገችበት የጀርመን ባህል በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ባህሏን ለማወቅ ከልጅነቷ ጀምሮ ከጀርመናዊት እናቷ አኒተ ደግነህ እና ከአባቷ ከዶክተር ፀጋዬ ደግነህ እንዲሁም ከታላቅ እህቷ ጋር በመሆን በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዛለች። ከምግብ የደሮ ወጥ ከድምፃዊ የፀጋዬ እሸቱ ፣ የቴዲ አፍሮ እና የዘሪቱ ከበደ፣ ከተዋናይ ደግሞ የደበበ እሸቱ አድናቂ ነች።ከፊልም ድፍረትን ከሙዚቃ ደግሞ የታሪኩ ጋንኪስ  ዲሽታ ጊና አድናቂ ነች።ለመሆኑ ሳሮን ከዓለም አቀፍ የፊልም ኢንደስትሪው እነማንን ታደንቃለች። 
«በመጀመሪያ ከሴቶች ስጀምር  ክሎይ ግሬስ ሞሪትስ  በጣም ጥሩ ተዋናይ ነች። እሷ እራሷ  በጣም ወጣት ሆና ነው የምትጫወተው፣  ጄኒፈር ላውረንስም በጣም ጥሩ ነች። ከወንዶች  ጆርጂያ ፊኒክስ በእውነት በጣም ጎበዝ ነው። ጆኒ ዴፕንም በጣም አደንቀዋለሁ። ከሆሊውድ ስንወጣ  ለምሳሌ ቦሊዉድ  ሻህሩክ ካን  በጣም ጥሩ  ተዋናይ ነው።ከኢትዮጵያ ደግሞ ደበበ እሸቱን «ሬድ ሊቭስ» ላይ በተጫወተው ገፀ-ባህሪው  በጣም ጥሩ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።» በማለት ገልጻለች።
በጎርጎሪያኑ 2017 ዓ/ም በባርሴሎና ፕላኔት የፊልም ፌስቲቫል በአጫጥር ፊልሞች ምርጥ ተዋናይ ተብላ ተሸልማለች።ሳሮን በትወናው ብቻ ሳይሆን በትምህርቷም የዋዛ አልነበረችምና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በከፍተኛ ውጤት አጠናቃ በበርሊን የህክምና ዩንቨርሲቲ የስነ-ልቡና ትምህርት የሶስተኛ ዓመት ትምህርቷን በመከታተል ላይ ትገኛለች።ትወና ሁለገብ ክህሎትን ይጠይቃልና  በውሃ ዋና  እንዲሁም  በፈረስ ግልቢያም ጥሩ ችሎታ አዳብራለች ።ለወደፊቱ አፍሪቃዊ እና ኢትዮጵያዊ ፊልሞች ላይ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሆሊዩድ ፊልሞች የመተወን ዕቅድ አላት።ለወጤታማነቷ የወላጆቿ እገዛ ከፍተኛ መሆኑን የምትገልፀው ሳሮን እሷ የመጣችበት መንገድ አልጋ በአልጋ ባለመሆኑ በዚህ የሙያ ዘርፍ መቀጠል የሚፈልጉ ወጣቶችም ተስፋ ሳይቆርጡ መስራት እንዳለባቸው መክራለች። 
«እኔ ማለት የምችለው የኔ መመሪያ ተስፋ እንዳትቆርጡ ነው። ምክንያቱም የፊልም ኢንደስትሪው በጣም ከባድ ነው።በእርግጠኝነት መገፋት ሊያጋጥማችሁ ይችላል።ቢሆንም  እራሳችሁን አትጣሉ። የግል ጉዳይ አድርጋችሁም አትውሰዱት።ነገር ግን ሁል ጊዜ መሞከርን ቀጥሉ።ሰው የሆነ ነገር አጥብቆ ከፈለገ፤ በእርግጠኝነት የፈለገውን ያገኛል ።ግቡንም ያሳካል። ለኔም እንደዛ ነበር።»በላለች ሳሮን ደግነህ። 

Saron Degineh Deutsche Schauspielerin
ምስል Privat
Saron Degineh Deutsche Schauspielerin
ምስል Privat
Saron Degineh Deutsche Schauspielerin
ምስል Privat
Deutschland Saron Tsegaye Degineh
ምስል Privat

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ