1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ውይይት በተባባሰ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ሊካሔድ እንደማይችል" ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለጹ

እሑድ፣ ኅዳር 5 2014

የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለኢትዮጵያ ግጭት መፍትሔ ለማበጀት "ውይይት ብቸኛው አስተማማኝና ዘላቂ መንገድ ነው። ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔ የለም። በውጊያ አውድማ የሚገኝ አሸናፊነት ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መረጋጋት ዋስትና አይሆንም" ብለዋል። "ውይይት በተባባሰ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ሊካሔድ እንደማይችል" ኦባሳንጆ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/42ykz
Porträt - Olusegun Obasanjo
ምስል Getty Images

የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የኢትዮጵያን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጋራ መግባባት ሊፈጠር ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገለጹ። ልዩ ልዑኩ ትናንት ቅዳሜ ባወጡት እና የአፍሪካ ኅብረት ዛሬ በድረ ገጹ ባሰራጨው መግለጫቸው በሁሉም ወገን ያነጋገሯቸው ወገኖች "በኢትዮጵያ ሰላም፣ ደህንነት እና መረጋጋት እንዲሰፍን ምኞታቸውን ገልጸዋል" ብለዋል። 
ይሁንና አንድ አመት ለዘለቀው ግጭት እንዴት መፍትሔ ይበጅ በሚለው ረገድ ልዩነት መኖሩን የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጠቁመዋል። 

"ጦርነት የፖለቲካ ውድቀት ውጤት" መሆኑን የገለጹት ኦባሳንጆ "ውይይት ብቸኛው አስተማማኝ እና ዘላቂ መንገድ ነው። ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔ የለም። በውጊያ አውድማ የሚገኝ አሸናፊነት ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መረጋጋት ዋስትና አይሆንም" የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። 

የሁሉም ወገኖች አመራሮች ወታደራዊ ጥቃት እንዲያቆሙ የጠየቁት ኦባሳንጆ ይኸ ውጊያ በገጠሙ ኃይሎች መካከል የሚደረግ "ውይይት ወደ ፊት እንዲራመድ ዕድል ይሰጣል" ብለዋል። አለበለዚያ "ውይይት በተባባሰ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ሊካሔድ እንደማይችል" ኦባሳንጆ ገልጸዋል። 

የቀድሞዉ የናጄሪያ የጦር ጄኔራል፣ ፕሬዝደንትና ዕዉቅ ፖለቲከኛ በአፍሪቃ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር የሙሳ ፋኪ መሐማት ልዩ መልዕክተኛ ሆነዉ የተሾሙት ባለፈው ነሐሴ 2013 ዓ.ም. ነው። ልዩ መልዕክተኛው ባለፈው ሣምንት ከኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተገናኝተው ተወያይተዋል። ወደ ትግራይ ክልል ተጉዘው ከህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ጭምር ተነጋግረዋል።  

ኦባሳንጆ ትናንት ባወጡት መግለጫ ከአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች መሪዎች ጋር "አበረታች" ውይይቶች ማድረጋቸውን፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከአፋር ክልል መሪዎች ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸውን ገልጸዋል። 

ልዩ ልዑኩ በመግለጫቸው እንደጠቆሙት ከኢትዮጵያ የክልል መስተዳድሮች በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ ኬንያ ከዩጋንዳ፣ ከጅቡቲ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ ፕሬዝደንቶች እና ከሱዳን አመራር ጋር ውይይት አድርገዋል። 

የአፍሪካ መሪዎች እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማሸማገል ጥረታቸውን እንዲደግፍ ጥያቄ ባቀረቡበት መግለጫቸው ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እነዚሁ አካላት "በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች ወይም ንግግሮች እንዲቆጠቡ" አሳስበዋል።