1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

የኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያ መንገድ

ረቡዕ፣ ኅዳር 8 2014

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ እና በአገሪቱ ማክሮ ኤኮኖሚ ላይ በፈጠረው ተጽዕኖ ምክንያት ለአዲስ የድጋፍ መርሐ-ግብር ውይይት መጀመር እንደማይቻል አስታውቋል። ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ገንዘብ ከምትበደርባቸው ሁለት ማዕቀፎች አንዱ ባለፈው መስከረም ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ተቋርጧል። ኢትዮጵያም መተኪያ ጠይቃ ነበር።

https://p.dw.com/p/437JH
IWF Report Logo
ምስል Yuri Gripas/REUTERS

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያ መንገድ

በኢትዮጵያ ባለው አለመረጋጋት እና በማክሮ ኤኮኖሚው ላይ ባሳደረው ጫና ምክንያት በዚህ ወቅት ስለ አዲስ የድጋፍ መርሐ-ግብር ውይይት መጀመር አስቸጋሪ መሆኑን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አስታውቋል። የተቋሙ የኮምዩንኬሽን ክፍል ዳይሬክተር ጄሪ ራይስ ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ባለው መርሐ-ግብር ረገድ መሬት ላይ ባለው ከፍተኛ አለመረጋጋት እና በማክሮ ኤኮኖሚው ላይ ካለው ተጽዕኖ አንጻር ከፍተኛ የለጋሾች ድጋፍ ቢኖርም እንኳ በዚህ ደረጃ ወደ ፕሮግራም ውይይቶች መሔድ አስቸጋሪ ነው። ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ ለመወያየት ዝግጁ ሆነን እንጠብቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።

"የፖሊሲ ምክር እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማቅረብ ከባለሥልጣናቱ ጋር በተከታታይ ግንኙነት ማድረጋችንን እንቀጥላለን" ያሉት ጄሪ ራይስ "እንደ ሌላው ሁሉ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሥጋት እየተመለከትን ነው። ጉዳዩን መከታተላችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ ከምትበደርባቸው አንዱ የሆነው እና የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) የተባለው ማዕቀፍ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም ያለ ጊዜው ተጠናቋል። 

የገንዘብ ምኒስትር ድዔታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከቡድን 20 አባል አገራት ጋር በተደረገ ውይይት "እንደገና እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርባለች። በዚህ መሠረት ያንንው የገንዘብ መጠን በአዲስ መልክ እንደገና የሚቀጥል ይሆናል" ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸው ነበር። 

Äthiopien Addis Abeba
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ ከምትበደርባቸው ሁለት ማዕቀፎች አንዱ የሆነው እና የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) የተባለው ማዕቀፍ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም ያለ ጊዜው ተጠናቋል። ምስል DW/E. Bekele

ኢትዮጵያ ያለፉትን ሁለት አመታት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በገባችው ስምምነት በሁለት ማዕቀፎች ጠቀም ያለ ገንዘብ ስትበደር ቆይታለች። በተቋረጠው የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ከተፈቀደላት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ወስዳለች። ሁለተኛው እና የተራዘመ የፈንድ ቅርቦት (Extended Fund Facility) የተባለው ማዕቀፍ በአንጻሩ እስከ ታኅሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቆይ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ድረ-ገጽ የሰፈረ መረጃ ያሳያል።  

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኮምዩንኬሽን ክፍል ዳይሬክተር ጄሪ ራይስ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል ለኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ መቋቋሙን ተቋማቸው በይሁንታ እንደሚቀበል ተናግረዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከአበዳሪዎች ኮሚቴው ጋር አስፈላጊ ቴክኒካዊ ድጋፍ በማቅረብ ረገድ በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ይኸንንም እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። 

ይኸ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጥያቄ የሚመለከት እና የአገሪቱን አስራ ሁለት አበዳሪዎች አንድ ላይ ያሰባሰበ ነው። ይኸው ኮሚቴ ባለፈው መስከረም በቻይና እና በፈረንሳይ ሊቀ-መንበርነት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሒዷል። በቪዲዮ አማካኝነት በተካሔደው ስብሰባ የገንዘብ ምኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የኢትዮጵያን ጥያቄ  ለኮሚቴው አቅርበዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ማክሮ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች እና ከአገሪቱ ጋር ግንኙነታቸው የሚገኝበትን ደረጃ ለኮሚቴው እንዳቀረቡ በወቅቱ የቡድን 20 አገራት ፕሬዝደንት የነበረችው ጣልያን ያወጣችው መግለጫ ያሳያል።

Sambia | Straßenverkehr in Lusaka
ከዛምቢያ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን (GDP) 60 እጁ የውጭ ዕዳ ነው። በማዕድን ሐብት የናጠጠችው ደሐ አገር በአጠቃላይ 14.48 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ እንዳለባት የአገሪቱ መንግሥት ይፋ አድርጓል።ምስል Meng JinhPhotoshot/picture alliance

የኢትዮጵያ፣ የዛምቢያ እና የቻድ መንገድ 

እንደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጥያቄ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ ያቀረበችው ዛምቢያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) ለመጀመር ውይይት እያደረገች ነው። ተደጋጋሚ ድርቅ፣ በዓለም ገበያ የመዳብ ዋጋ ማሽቆልቆል፣ የአገሪቱ መንግሥት የተከተላቸው ፊስካል ፖሊሲዎች ከብርቱ የኮሮና ወረርሽኝ ዳፋ ጋር ተደማምረው የዛምቢያ ኤኮኖሚ በጎርጎሮሳዊው 2020 በብርቱ እንዲኮማተር አድርገውታል።

ከዛምቢያ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን (GDP) 60 እጁ የውጭ ዕዳ ነው። በማዕድን ሐብት የናጠጠችው ደሐ አገር በአጠቃላይ 14.48 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ እንዳለባት የአገሪቱ መንግሥት ይፋ አድርጓል። ከዚህ ውስጥ ወለድን ጨምሮ ዛምቢያ 6.8 ቢሊዮን ዶላር የቻይና ዕዳ አለባት። ፕሬዝደንት ሐካይንዴ ሒቺሌማ የሚመሩት መንግሥት ለዛምቢያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የገንዘብ ዕገዛ ይፈልጋል። ይኸ ግን ዛምቢያ ከጀመረችው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ የተቆራኘ እንደሆነ ጄሪ ራይስ ተናግረዋል።  

ጄሪ ራይስ "የዛምቢያ ዕዳ ዘላቂ አይደለም። ስለዚህ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለዛምቢያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት በባለሙያዎች ደረጃ ከመፍቀዱ በፊት ከአበዳሪዎቿ በቂ ገንዘብ እንደሚያገኝ ማረጋገጫ ማግኘት አለበት። ዛምቢያ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ አጠቃላይ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጥያቄ አቅርባለች። ይኸን ለማመቻቸት ከግል አበዳሪዎች ጋር በውይይት ላይ ትገኛለች። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዳሉት በውይይቶቹ መሻሻል ታይቷል። ይሁንና ከሚፈለገው ቦታ አልደረስንም" ብለዋል። 

ከኢትዮጵያ እና ከዛምቢያ ቀድማ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጥያቄ ያቀረበችው ቻድ ነበረች። በማዕከላዊ አፍሪካ የምትገኘው አገር ያቀረበችው ጥያቄ ፓሪስ ክለብን የመሳሰሉ አበዳሪዎቿ በይሁንታ ቢቀበሉትም ከግሉ ዘርፍ ግን ማረጋገጫ አላገኘችም። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዘላቂ አይደሉም ከሚላቸው ጎራ የመደበውን ዕዳ አከፋፈል ማሸጋሸግ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ለቻድ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ቅድመ ሁኔታ ነው። ቻይና፣ የቡድን 20 አባል አገራት እና የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች በተስማሙበት የጋራ ማዕቀፍ ቻድ ላለባት 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ የአከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረበችው ባለፈው ጥር ወር ነበር። 

Mali | Opération Barkhane
ቻይና፣ የቡድን 20 አባል አገራት እና የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች በተስማሙበት የጋራ ማዕቀፍ ቻድ ላለባት 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ የአከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረበችው ባለፈው ጥር ወር ነበር።ምስል Philippe de Poulpiquet/LE PARISIEN/PHOTOPQR/MAXPPP/picture alliance

"የቻድ ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለአገሪቱ ያቀደውን ማዕቀፍ በመደገፍ መግለጫ አውጥተዋል። የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ውሎችንም ለመደራደር ተስማምተዋል። ነገር ግን ቻድ በአስቸኳይ የምትፈልገውን ይፋዊ የገንዘብ ድጋፍ ለመጀመር ከግል አበዳሪዎች ተአማኒ የእዳ አከፋፈል ማሻሻያ ሂደት እንፈልጋለን" ሲሉ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኮምዩንኬሽን ክፍል ኃላፊ ተናግረዋል። ጄሪ ራይስ "ከታቀደው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የድጋፍ ማዕቀፍ መሥፈርቶች ጋር የተስማማ የግል አበዳሪዎች በዕዳ አከፋፈል ላይ ያለ ተጨማሪ መዘግየት በቁርጠኝነት የሚደረግ ድርድር ለቻድ ኤኮኖሚ ማገገሚያ እና የድህነት ቅነሳ ጥረት እጅግ ጠቃሚ ነው" በማለት ለጉዳዩ አጽንዖት ሰጥተዋል። 

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ የኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያን ዕዳ ለማሸጋሸግ የተጀመሩ ድርድሮች የግድ በስኬት መጠናቀቅ አለባቸው የሚል አቋም አላቸው። ኃላፊዋ በሶስቱ አገሮች የተጀመረው ጥረት ከተሳካ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉ ሊገፋፋ እንደሚችል ተናግረዋል።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እየተባሉ የሚጠቀሱት ደሐ አገራት ዕዳ በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ብቻ 12 በመቶ ጨምሮ 860 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የዓለም ባንክ ባለፈው ጥቅምት ወር ያወጣው ዳጎስ ያለ ሰነድ ያሳያል። የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ዴቪድ ማልፓስ ይኸን ቀውስ ለመፍታት የዕዳ ቅነሳ፣ በፍጥነት የአከፋፈል ሽግሽግ ማካሔድ እና ግልጽነትን ማጠናከርን ጨምሮ ሰፋ ያለ እርምጃ እንደሚፈልግ ሰነዱ ይፋ ሲሆን ገልጸዋል። 

እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ