1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፣ ማሊ እና ጊኒ ከአጎዋ የንግድ ሥምምነት ተሰረዙ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 24 2014

የኢትዮጵያ፣ የማሊና የጊኒ መንግሥታት "የአጎዋን ደንብ የሚጥሱ እርምጃዎች በመውሰዳቸው" ከታኅሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ከአጎዋ የንግድ ሥምምነት ውጪ መሆናቸውን የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር አስታወቀ። ኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፤ ማሊና ጊኒ መፈንቅለ-መንግሥት በአጎዋ በኩል የነበራቸውን ዕድል አሳጥቷቸዋል

https://p.dw.com/p/454Av
Äthiopien Der Industriepark Adama
ምስል Eshete Bekele Tekle/DW

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን ከአጎዋ የንግድ ሥምምነት መሠረዙን አስታወቀ። የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መሥሪያ ቤት ትናንት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ማሊ እና ጊኒ ከሥምምነቱ መሠረዛቸውን ይፋ እንዳደረገ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።  

በመግለጫው መሠረት የኢትዮጵያ፣ የማሊ እና የጊኒ መንግሥታት "የአጎዋን ደንብ የሚጥሱ እርምጃዎች በመውሰዳቸው" ከትናንት ታኅሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ከ22 አመታት በፊት ካበጀችው የንግድ ሥምምነት ውጪ ሆነዋል። 

አጎዋ የተወሰኑ የብቃት መሥፈርቶች የሚያሟሉ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከ1 ሺሕ 800 በላይ የሸቀጥ አይነቶችን ቀረጥ ሳይከፍሉ በአሜሪካ ገበያ እንዲሸጡ የሚፈቅድ የግብይት ሥርዓት ነው።

የአፍሪካ አገራት ከሥምምነቱ ተጠቃሚ ለመሆን ማሟላት ከሚጠበቁባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች መካከል ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ የሚለው ይገኝበታል። 

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መሥሪያ ቤት ትናንት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ "በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ምክንያት በመንግሥት እና ሌሎች አካላት ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ጥሰት" አሜሪካን እንደሚያሳስብ ገልጿል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአንድ ሣምንት በፊት አሜሪካ ውሳኔዋን እንድታጤን ጠይቆ ነበር። የኢትዮጵያ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ታኅሳስ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ "ኢትዮጵያን ከአጎዋ የንግድ ሥምምነት ማስወጣት አሁን በአገሪቱ ከተፈጠረው ቀውስ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንጹኃን ሰዎች ሕይወት እና ኑሮ ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን" አስጠንቅቋል። 

Conakry, Guinea | Mamady Doumbouya
በጊኒ እና በማሊ "ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የተፈጸሙ የመንግሥታት ለውጦች" በመግለጫው አሜሪካን ያሳስባሉ የተባሉ ጉዳዮች ናቸው። ምስል Xinhua News Agency/picture alliance

በጊኒ እና በማሊ "ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የተፈጸሙ የመንግሥታት ለውጦች" በመግለጫው አሜሪካን ያሳስባሉ የተባሉ ጉዳዮች ናቸው። ሶስቱ አገራት በአጎዋ በኩል የነበራቸውን ዕድል መልሶ ለማግኘት "ማሟላት የሚገቧቸው ግልጽ መለኪያዎች" መኖራቸውን የጠቆመው የአሜሪካ መግለጫ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ይኸን ዓላማ ለማሳካት ከመንግሥታቱ ጋር እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። 

በአሜሪካ የንግድ ተወካይ መሥሪያ ቤት መረጃ መሠረት 38 ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የአጎዋ የንግድ ሥምምነት ተጠቃሚ ናቸው። የአሜሪካ ኮንግረስ ከ22 አመታት በፊት የተፈረመውን ሥምምነት የሚያሻሽል እና ለቀጣዮቹ ሶስት አመታት በሥራ ላይ እንዲቆይ የሚፈቅድ አዋጅ አጽድቋል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ