1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ሥራ ብዙው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምን ይዞ መጣ?

ረቡዕ፣ የካቲት 2 2014

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በ100 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመ ሥራ ብዙ ኩባንያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው። የቦርድ አባላትንም ይሾማሉ። የመንግስት ሀብቶችን የማስተዳደር፣ የውጪ ኢንቨስትመንት የመሳብ ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም አትራፊ ናቸው ብሎ በሚያምንባቸው ሥራዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ያፈሳል

https://p.dw.com/p/46lLN
Logo Ethiopian Investment Holdings
ምስል Ethiopian Investment Holdings

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ሥራ ብዙው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምን ይዞ መጣ?

"ባለቤትነታቸው የፌድራል መንግስት የሆኑ የተለያዩ ሀብቶችን" በማስተዳደር "ተገቢውን እና ውጤታማ አመራር" የመስጠት እንዲሁም "ከፍ ያለ የውጪ ኢንቨስትመንት እና ቴክኖሎጂ" የመሳብ ኃላፊነት የተጣለበት ሥራ ብዙው እና ግዙፉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሕጋዊ ተቋም ሆኗል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኩባንያው እንዲቋቋም ውሳኔ ያስተላለፈው ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ነበር።

"የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ለማሟላት በሚያግዝ አኳኋን የግል ኢንቨስትመንት ከመንግስት ጋር በጋራ ልማት ስራዎች ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የግል ኢንቨስትመንትን በተጠናከረ ሁኔታ ለመሳብ" የተቋቋመ መሆኑ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ጥር 23 ቀን 2014 በታተመው እና አደረጃጀቱን እና ተግባራቱን ለመደንገግ የወጣ ደንብ ላይ ሰፍሯል።

በማቋቋሚያ ደንቡ እንደሰፈረው "የተቀናጀ ስትራቴጂካዊ ቁጥጥር በማከናወን በመንግስት ባለቤትነት የተያዙ ሪል ስቴት፣ መሬት፣ መሠረተ-ልማቶች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና የመሳሰሉ ሀብቶችን የተሟላ እና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጡ" የማድረግ ኃላፊነት በዚሁ ኩባንያ ትከሻ ላይ ወድቋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ "የመንግስት የሆኑ ሀብቶችን እና የሀብት ምንጮችን በማስተዳደር ረገድ ተገቢውን የገበያ ሥርዓት በመከተል በጠንካራ የኩባንያ መልካም አስተዳደር መርሆዎች የሚመሩ እንዲሆኑ ለማስቻል" ጭምር የተቋቋመ ነው።

ይኸን ኩባንያ በማቋቋም ኢትዮጵያ ጥሪታቸውን ሰብሰብ አድርገው በመዋዕለ-ንዋይ ዘርፍ የሚሰማራ "ሶቭሪን ዌልዝ ፈንድ" ባለቤት ከሆኑ 25 የአፍሪካ አገራት አንዷ ሆናለች። የኢትዮጵያ ጎረቤት ጅቡቲ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ እና ርዋንዳን የመሳሰሉ አገራት ይኸው ባለቤትነቱ የመንግስት የሆነ የመዋዕለ-ንዋይ ኩባንያ ባለቤቶች ናቸው።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ "በመንግስት ደረጃ ለኢንቨስትመንት ፈንድ ሲዘጋጅ ሶቭሪን ይባላል። ብዙ አገሮች በተለያየ ኢንቨስትመንት ላይ መግባት ሲፈልጉ እንዲህ አይነት ፈንድ ያቋቁማሉ። ፈንዱ አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጪም ኢንቨስት ሊደረግበት ይችላል። በይበልጥ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከነዳጅ የሚያገኙት ብዙ ገንዘብ ስላላቸው በተለያየ አገራት ይበልጥ በአውሮፓ ሪል ስቴትን ጨምሮ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ የተለያየ ኢንቨስትመንት ላይ ያውሉታል" ሲሉ አስረድተዋል።

Video Still TV Magazin The 77 Percent
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በ100 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመ ሥራ ብዙ ኩባንያ ነው።ምስል DW

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአንድ መቶ ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመ ነው። ከዚህ ውስጥ ሃያ አምስት ቢሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና በዓይነት ተከፍሏል። ተቋሙን በበላይነት የሚመራው ቦርድ "ለኩባንያው የተፈቀደ ካፒታል ሊያሳድግ፣ ሊቀንስ ወይም ወደ ሌላ ቅርጽ ሊለውጥ ይችላል።" የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እንዲያስተዳድራቸው የተደረጉ የተለያዩ የመንግስት ሀብቶች፣ ከሀብቶች የሚገኝ ገቢ እና የኢንቨስትመንት ትርፍ፣ ከሀብቶቹ ወይም ከተቋማቱ ሽያጭ የሚገኝ ገቢ፣ ከቦንድ እና ከሌሎች የፋይናንስ ሰነዶች ሽያጭ የሚገኝ ገቢን ጨምሮ በብድር እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚገኝ ገቢ በሙሉ ለተቋሙ የገንዘብ ምንጭ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምን ይሰራል?

"የኢትዮጵያ መንግሥት ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ተቋም ሆኖ" የሚያገለግለው ይኸ ኩባንያ ዋና መቀመጫው በአዲስ አበባ ቢሆንም እንደ አስፈላጊነቱ በሀገር ውስጥ ወይም በሌላ ሀገር ቅርንጫፎች ሊኖሩት ይችላል። ተቋሙ "ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ የኩባንያ መልካም አስተዳደር መርሆዎችን በመከተል እና በመተግበር እንዲሁም ብቃት ያለው አስተዳደርን ተግባራዊ ባደረገ መልኩ የመንግስትን ሀብት" ማስተዳደር አለበት። "የጥምር ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መደላድልን በመፍጠር፣ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ሐብትን በማቀናጀት እንዲሁም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሀብቶች ላይ እሴት በመፍጠር የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደ ስትራቴጂያዊ መሳሪያ ሆኖ ማገልገል" ከዓላማዎቹ መካከል በማቋቋሚያ ደንቡ የሰፈረ ነው።

የሕግ ባለሙያው አቶ ምኅረተዓብ ልዑል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአገሪቱ የመዋዕለ-ንዋይ አሰራር መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ አላቸው። በኢትዮጵያ የቢዝነስ እና የመዋዕለ-ንዋይ ዘርፎችን በተመለከቱ የሕግ ጉዳዮች ላይ ከ20 አመት በላይ በአማካሪነት የሰራ ተቋም በኃላፊነት የሚመሩት ባለሙያው "እስከ ዛሬ ድረስ እኛ አገር ያለው አስተሳሰብ አንድ ኢንቨስተር ሲመጣ ፋብሪካ ከፍቶ፤ በራሱ ሰርቶ እንዲያመርት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አሰራር ደግሞ ያ አይደለም። ለምሳሌ አንድ ኢንቨስተር ይመጣና `እኔ አስር በመቶ ነው የምፈልገው´ ቢል እንዲህ አይነት ኢንቨስተርን የሚያስተናግድ ማዕቀፍ እኛ አገር አልነበረንም። ስለዚህ ይኸ ተቋም ፖርቶፎሊዮ ኢንቨስትመንትን ሊያስተናግድ ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል። "ብዙ መሬቶች፤ ብዙ ጥሪቶች በመንግስት እጅ አሉ። እነዚህ ጥሪቶች ማስገኘት የሚገባቸውን ያክል ገቢ እያስገኙ አይደለም" የሚሉት አቶ ምኅረተዓብ ልዑል "እነዚህን ጥሪቶች ከግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን የበለጠ ገቢ የሚያስገኙ እንዲሆኑ፤ የበለጠ ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ እንዲሆኑ ያደርጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ "ባለቤት የሆነባቸውን አክሲዮኖች፣ የዕዳ ሰነዶች፣ ቦንዶችን፣ የዋስትና ሰነዶችን" መያዝን ጨምሮ ከ20 በላይ ተግባር እና ኃላፊነቶች የተሰጡት ተቋም ነው። ኩባንያው እንደ ባለወረት "አትራፊ ናቸው ብሎ በሚያምንባቸው ማንኛቸውም የንግድ እና የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ያፈሳል።" ከዚህ በተጨማሪ "የካፒታል ገበያ፣ የገንዘብ ገበያ እና ሌሎች መሰል ዘርፎች ላይ በግዥ፣ በሽያጭ ወይም በሌላ የኢንቨስትመንት ተግባር ይሳተፋል።"

Äthiopien Währung Birr
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ "ባለቤት የሆነባቸውን አክሲዮኖች፣ የዕዳ ሰነዶች፣ ቦንዶችን፣ የዋስትና ሰነዶችን" መያዝን ጨምሮ ከ20 በላይ ተግባር እና ኃላፊነቶች የተሰጡት ተቋም ነው።ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ይኸ ተቋም "የሚተላለፉለትን የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ሌሎች የመንግስት ሀብቶች አደረጃጀት እና አሰራርን በመቀየር እና አዋጭ በሆነ መልኩ ስራ ላይ በማዋል ውጤታማ እና ትርፍ የሚያመነጩ አድርጎ" የመለወጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል። በአሁኑ ወቅት በርካታ ተቋማት የሚያስተዳድረው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ከሞላ ጎደል ይኸን ኃላፊነት እያከናወነ ይገኛል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መቋቋም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደርን የሚተካ ይመስላል። በሁለተኛው ተቋም እጣ-ፈንታ ላይ እስካሁን በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ ማብራሪያ የለም። ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

አቶ አብዱልመናን ግን "የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን ሪል ስቴቶችን፣ መሬት እና የገንዘብ ተቋሞችንም በአንድ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር የማድረግ ሥራ ነው። ከዚህ በፊት ከነበሩት ትንሽ የማዋቀር ነገር ነው እንጂ አዲስ ነገር የለውም። ምክንያቱም [የመንግሥት የልማት ድርጅቶች] ከዚህ በፊት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ይተዳደሩ ነበር" በማለት መሠረታዊ ለውጥ እንደሌለው እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አደረጃጀት እንዴት ያለ ነው?

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ሥራ አስፈጻሚ እና የሥራ አመራር አባላት ይኖሩታል። የተቋሙን የዳይሬክተሮች ቦርድ በሰብሳቢነት የመምራት ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠ ነው። የቦርዱ ስድስት አባላት የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ በታተመው ደንብ መሠረት የአገልግሎት ዘመናቸው በየሶስት አመቱ ሊታደስ ይችላል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ "ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። የቦርድ ሊቀ-መንበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። የቦርድ አባላት የሚሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። ወዲያውኑ ይኸ ድርጅት የፖለቲካ ቁጥጥር ውስጥ ነው ያለው ማለት ነው። በአገራችን ታሪክ እንደታዘብንው ደግሞ በፖለቲከኞች ሲተዳደሩ የነበሩት እንደ ሜቴክ፣ የስኳር ኮርፖሬሽን እና የልማት ባንክን የመሳሰሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የታየው ነገር የሀገር ሐብት ሲያባክኑ፣ ሙስና በጣም ሲንሰራፋ ነው" የሚሉት አቶ አብዱልመናን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ኃላፊነት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ሆኖ አግኝተውታል።

"አዲስ የተመሠረተው ይኸ ግዙፍ የሆነ ኩባንያ ከበፊቶቹ የተለየ ማሻሻያ ያመጣል የሚል ምንም ተስፋ አላደርግም" የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው  "እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርን መምራትን ያህል ነገር ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው።  ይኸን ግዙፍ ኩባንያ በሳቸው የቦርድ ሊቀ-መንበርነት እና የቦርድ አባላት ሿሚነት ወደ እርሳቸው ሥር መምጣቱ የበለጠ እሳቸው ላይ ጫና በመፍጠር እና ቁጥጥር በመላላት ከበፊቱ ያልተለየ ሁኔታ እንዳይፈጠር ነው የምፈራው" በማለት ሥጋታቸውን አጋርተዋል።

Äthiopien | Premierminister Abiy Ahmed Ali
በማቋቋሚያ ደንቡ እንደሰፈረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የዳይሬክተሮች ቦርድ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰብሳቢነት ይመራል። የቦርዱ ስድስት አባላት የሚሾሙትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነውምስል Office of the Prime Minister Ethiopia/UPI Photo/Newscom/picture alliance

የሕግ ባለሙያው አቶ ምኅረተዓብ በበኩላቸው "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ በዝቶባቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን ቦርድ የማይሰበስቡ ከሆነ የእሳቸው ሊቀ-መንበር መሆን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ማለት ነው። ግን ይኸን ሥራ ጊዜ ሰጥተውት ህጉ ላይ በተመለከተው ጊዜ መሠረት የቦርዱን ስብሰባ የሚያካሒዱ ከሆነ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ክንፍ መሪ እሳቸው ስለሆኑ የሚሰጡት ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ስለሚሆን ከዛ በኋላ በተወሰኑት ጉዳዮች ላይ የትኛውም የመንግሥት መስሪያ ቤት መሔድ አያስፈልግም። አሁን ባለው ሁኔታ የመንግስት ቢሮክራሲ ቀላል አይደለም" ሲሉ ጥቅምም ጉዳትም ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።

"የእሳቸው እዛ ቦታ ላይ መምጣት አንድ ውሳኔ ከተሰጠ የመጨረሻ ሆኖ ወደ ትግበራ ይሔዳል። ካላቸው የሥራ ብዛት አንጻር ይኸን ስብሰባ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይችላሉ ወይ የሚለው ነገር እንደ ሥጋት ይታያል። እኔ ግን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው ኃላፊነት በጣም ሰፊ ስለሆነ፤ ለኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ዕድገትም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብዬ ስለማስብ፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤትም የተወሰነ ነገር ስለሆነ የቦርድ ሰብሳቢነት ቦታ ሲሰጣቸው ትኩረት እንደሚሰጡት ወስነው የገቡበት ነገር ስለሚሆን ከመንግሥት ቢሮክራሲ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ነጻ ያወጣዋል" ሲሉ አቶ ምኅረተዓብ ተናግረዋል። 

አቶ አብዱልመናን ሥራው ብዙ የተቋቋመበት ካፒታልም ግዙፍ የሆነውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከፖለቲከኞች ይልቅ ባለሙያዎች ቢመሩት ይመርጣሉ። "በአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ማንንም ፖለቲከኛ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም" የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ባለፉት አመታት ከባድ ውሳኔዎች ያሳለፉ ሹማምንት ተጠያቂ ሲሆኑ አለመታየቱን ይጠቅሳሉ። ከዚህ ባሻገር ግን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በገበያው ውስጥ የሚኖረው ሚና ለአቶ አብዱልመናን ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖባቸዋል።

"መንግሥት አገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ያለው እኮ በግሉ ዘርፍ ወደሚመራ ኤኮኖሚ እንሔዳለን በሚል ነበር። ምክንያቱም ከዚህ በፊት መንግሥት በኤኮኖሚው የነበረው ጣልቃ ገብነት ሀገሪቱን ለከባድ ዕዳ፣ ለኪሳራ፣ ለሙስና እና ለብክነት ዳርጓታል የሚል ነው። ይኸኛው ኢንቨስትመንት ውስጥ ይገባል ሲባል አሁንም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኢንቨስትመንት ውስጥ ሊገቡ ነው እንዴ?" እያሉ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ይጠይቃሉ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሚመሩ ኃላፊዎች ማንነት እስካሁን ይፋ አልሆነም። የሕግ ባለሙያው አቶ ምኅረተዓብ ኩባንያው የሚቀርጻቸው ምክረ-ሐሳቦች በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ገበያ ተቀባይነት የሚያገኙ ሊሆኑ እንደሚገባ ይመክራሉ።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ