1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ግጭት የማቆም ውሳኔ አስተያየት ከመቐለ ነዋሪዎች

ማክሰኞ፣ መጋቢት 20 2014

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በኩል ግጭት ስለማቆም ውሳኔ በተናጠል መሰጠቱን አስመልክተው የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ነዋሪዎች ውሳኔው አሳሳቢ ሰብአዊ ሁኔታን ለማቃለል አጋዥ ሊሆን ይችላል ብለዋል። በተፈፃሚነቱ የተጠራጠሩም አልጠፉም።

https://p.dw.com/p/49Aqd
Äthiopien Tigray-Provinz Mekele
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

«እስካሁን እኛ ተቸግረን ነበር» ከነዋሪዎች አንዱ

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በኩል ግጭት ስለማቆም ውሳኔ በተናጠል መሰጠቱን አስመልክተው የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ (DW) እንደገለፁት ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት ግጭት ለማቆም በተናጠል ያስተላለፉት ውሳኔ በትግራይ ክልል ያለውን አሳሳቢ ሰብአዊ ሁኔታ ለማቃለል አጋዥ ሊሆን ይችላል ብለዋል። ይሁንና በተፈፃሚነቱ ጥርጥር ያላቸውም አልጠፉም። የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን አስከፊ ሰብአዊ ሁኔታ ለመፍታት የሚሻ ከሆነ ለወራት የታገዱትን የባንክ፣ የቴሌኮም እና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎቶችን መክፈት ይገባዋል የሚል አስተያየትም ከበርካታ ነዋሪዎች ተሰንዝሯል። 

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፦ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረውን የአየር በረራ በየቀኑ እንዲደረግ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ርዳታ አቅራቢ ተቋማት ፍቃድ መስጠቱን ገልጧል። «በዚህም መሠረት የመድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያዎች፣ ገንዘብና አልሚ ምግቦችን ረጂ ድርጅቶች በቻሉት መጠን በአየር ትራንስፖርት መጓጓዝ ጀምረዋል»ም ብሏል። ሌሎች በአየር ትራንስፖርት ሊጓጓዙ የሚችሉ የሰብአዊ ድጋፎችን እንዲያጓጓዙም የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ መስጠቱን አክሎ በመግለጫው ጠቅሷል። «ከዚህ አኳያ በረጂ ድርጅቶች አቅም ማነስ ወይም በራሳቸው አሠራር ሥርዓት የመዘግየት ሁኔታ ካልገጠመ በቀር በመንግሥት በኩል ፈጣን ርምጃ ተወስዷል» ሲል ይነበባል የዛሬው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ።

«የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያሉ ዜጎችን ለመታደግ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ርዳታውን ለማቅረብ እንቅስቃሴ ውስጥ የገባ» መሆኑን ገልጦ «የሌላኛውን ወገን ቅን ትብብር ማግኘት» እንዳልቻለ ዐስታውቋል። መንግሥት የዓለም የምግብ ድርጅት እንዲያጓጉዝ ተፈቅዶለታል ካለው 43 የጭነት መኪና የርዳታ እህል 20ው አፋር ክልል ሠመራ ከተማ ቢደርሱም «ለተረጂዎች መድረስ» አለመቻሉም በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል። መንግሥት ለዚህ «ዋናው ምክንያት» ሲል ሲያብራራም፦ «የአብኣላ የርዳታ ማቅረቢያ መንገድ በሕወሓት ታጣቂዎች በመዘጋቱ፣ ርዳታው በየብስ ትራንስፖርት ወደ ትግራይ ክልል ሊጓጓዝ አልቻለም» ብሏል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ