1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በ3.8% እንደሚያድግ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ተነበየ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 12 2014

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከዚህ ቀደም የገደፈውን የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ትላንት ይፋ ባደረገው ሰነድ አካቷል። በትንበያው መሠረት በ2022 ኢኮኖሚው 3.8 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። በሚቀጥለው ዓመት ዕድገቱ 5.7 በመቶ ይደርሳል። የሸማቾች የዋጋ ግሽበት መለኪያ እና የውጭ ንግድ ሚዛን ጉድለትን የተመለከቱ መረጃዎችም አቅርቧል

https://p.dw.com/p/4A8zl
Video Still TV Magazin The 77 Percent
ምስል DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በ3.8% እንደሚያድግ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ተነበየ

በጎርጎሮሳዊው 2022 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት 3 ነጥብ 8 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ ትላንት ማክሰኞ ይፋ ባደረገው የዓመቱ ሁለተኛ የአገራት የምጣኔ ሐብት ዕድገት ትንበያ መሠረት በ2023 የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ 5 ነጥብ 7 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከዚህ ቀደም ለዓለም አገራት በሰራው ትንበያ "ባልተለመደ ከፍተኛ የእርግጠኝነት መጥፋት" ምክንያት የገደፋቸውን የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት የተመለከቱ መረጃዎች ማክሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2014 ይፋ በሆነው ሰነድ አካቷል። በሸማቾች የዋጋ ግሽበት መለኪያ (Consumer Prices) ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ 26 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው የሸቀጦች ዋጋ ንረት በተያዘው ዓመት ወደ 34 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚደርስ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ያሳያል። ይኸ በጎርጎሮሳዊው 2023 በአንጻሩ 30 ነጥብ 5 በመቶ ይሆናል።

ባለፈው አመት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 3 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የውጭ ንግድ ሚዛን ጉድለት (Current Account Balance) በጎርጎሮሳዊው 2022 በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ መሠረት ወደ 4 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ይላል። በሚቀጥለው ዓመት ወደ 4 ነጥብ 4 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል የተቋሙ ትንበያ ይጠቁማል። 

ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ምጣኔ ሐብት ዕድገት

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2022 ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ምጣኔ ሐብት በ3 ነጥብ 8 በመቶ ያድጋል። ይኸ ዕድገት በሚቀጥለው ዓመት ጥቂት ጭማሪ አሳይቶ ወደ 4 በመቶ ከፍ የማለት ዕድል ይኖረዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሰሐራ በርሐ በታች ከሚገኙ 35 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት 20 ገደማዎቹ በዕዳ ጫና ውስጥ የገቡ አሊያም የመግባት ሥጋት የተጫናቸው ናቸው። የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት በቀጠናው በሚገኙ አገራት ከሚያሳድረው ጫና መካከል ይኸው ተጨማሪ ፋይናንስ የሚፈልጉ ግን ዕዳ ያጎበጣቸው አገራትን ሁኔታ እንደሚገኝበት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኤኮኖሚ አማካሪ እና የጥናት እና ምርምር ክፍል ኃላፊ ፒየር ኦሊቪዬ ተናግረዋል።

USA Weltbank-Zentrale in Washington
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከዚህ ቀደም ለዓለም አገራት በሰራው ትንበያ "ባልተለመደ ከፍተኛ የእርግጠኝነት መጥፋት" ምክንያት የገደፋቸውን የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት የተመለከቱ መረጃዎች ትላንት ማክሰኞ ይፋ በሆነው ሰነድ አካቷል። ተቋሙ የሸማቾች የዋጋ ግሽበት መለኪያ እና የውጭ ንግድ ሚዛን ጉድለትን የተመለከቱ መረጃዎች አቅርቧልምስል Reuters/Y. Gripas

ኃላፊው ትላንት ማክሰኞ ተቋማቸው ትንበያውን ይፋ ሲያደርግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካሳደረባቸው ዳፋ በማገገም ላይ ሳሉ የተቀሰቀሰው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ብርቱ ጫና አሳድሮባቸዋል። በተለይ የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ መጨመር ደሐ ቤተሰቦች ላይ የሚያሳድረው በትር የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አማካሪ የጠቀሱት ብርቱ ፈተና ነው። ፒየር ኦሊቪዬ "ነዳጅ እና ኃይል የሚሸምቱ አገሮች የበለጠ ተጋላጭ እንደሚሆኑ እንጠብቃለን። ከፍ ያለ ዕዳ ያለባቸው አገሮች ወይም ለዕድገት ከፍ ያለ ፋይናንስ የሚፈልጉት እና ሕዝባቸውን ለመደገፍ በቂ አቅም የሌላቸው የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። እነዚህ አገሮች የውጪ ድጋፍ ወይም የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ይፈልጉ ይሆናል" ብለዋል።

የጦርነቱ ዳፋ ከሰሐራ በርሐ በታች ወደሚገኙ አገራት በዋናነት የተዛመተው በምግብ እና በነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ በኩል አድርጎ ነው። እንደ ተቀረው ዓለም ስንዴ ዋንኛ የገበታ ምግብ ባይሆንም በአፍሪካውያን ፍጆታ ከፍ ያለ ቦታ አለው። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሰነድ የምግብ ዋጋ መናር የሸማቾችን የመግዛት አቅም እና ፍላጎት በመጪዎቹ ጊዜያት እንደሚፈታተን አስጠንቅቋል። ይኸ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ አገራት ፖለቲካዊ ቀውስ የመቀስቀስ ዕድል አለው። የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ እንደ ናይጄሪያ ላሉ አምራች አገራት የዕድገት ተስፋን ከፍ አድርጓል።

አንድ ጦርነት የደቆሰው የ143 አገራት ምጣኔ ሐብት ትንበያ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትላንት ማክሰኞ ይፋ ያደረገው ምጣኔ ሐብታዊ ትንበያ ሩሲያ ጎረቤቷን ዩክሬንን በመውረሯ ያስከተለው መዘዝ የተጫነው ሆኖ ታይቷል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ "ምጣኔ ሐብታዊ ትንበያው በዋናነት በጦርነቱ እና ባስከተለው ጫና ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። የዋጋ ንረት፣ የፋይናንስ ቁጥጥር እንዲሁም በዓለም የአቅርቦት ገበያ ማነቆ ያስከተሉ በቻይና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ገቢራዊ የተደረጉ ሰፋፊ ገደቦች በኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ጫና አሳድረዋል" ሲሉ ትንበያው ይፋ ከመሆኑ በፊት ተናግረው ነበር። ጦርነቱ ባስከተለው ዳፋ ምክንያት "የ2022 እና 2023 የዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያን ቀንሰናል። እንደ መታደል ሆኖ ለአብዛኞቹ አገሮች ዕድገታቸው አዎንታዊ ሆኖ ይቆያል። የጦርነቱ ጫና ከዓለም አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) 86 በመቶ የሚሆነው የ143 [አገራት] ኤኮኖሚዎች ትንበያ እንዲቀንስ አድርጓል" ሲሉ ተደምጠዋል።

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ካስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር የዓለም የኤኮኖሚ ዕድገትን በማቀዛቀዝ የዋጋ ንረትን እንደሚጨምር የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ትላንት ማክሰኞ ተናግረዋል። በተቋሙ ትንበያ መሠረት የዓለም ምጣኔ ሐብት በጎርጎሮሳዊው 2022 እና በቀጣዩ አመት በ3.6 በመቶ ያድጋል። ብርቱ ጦርነት የሚካሔድባት ዩክሬን እና በውጊያው ምክንያት ኃይለኛ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሩሲያ ምጣኔ ሐብታቸው ከፍተኛ መኮማተር ይጠብቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት ኤኮኖሚ ጦርነቱ በተዘዋዋሪ በሚያደርስበት ጫና ዕድገቱ በ1 ነጥብ 1 በመቶ ብቻ ይገደባል።

"ሩሲያ የነዳጅ፣ ጋዝ እና ብረታ ብረቶች ዋንኛ አቅራቢ አገር ነች። ዩክሬን እና ሩሲያ በጥምረት ለዓለም ገበያ በሚያቀርቡት ስንዴ እና በቆሎ ቀዳሚ ናቸው።  የእነዚህ ሸቀጦች አቅርቦት መቀነስ ዋጋቸው እጅግ እንዲንር አድርጎታል" ያሉት ፒየር ኦሊቪዬ ግሪንቼስ በአውሮፓ፣ በማዕከላዊ እስያ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሰሜን አፍሪካ እና ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት የሸቀጥ አስገቢዎች ብርቱ ጫና እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። "የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ መናር የበለጠ የሚጎዳው ግን በአሜሪካ እና እስያን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦችን ነው" በማለት ሁኔታው በተለይ የሚበረታባቸው የማኅበረሰቡ ክፍሎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

Bilderchronik des Krieges in der Ukraine | Mariupol
የሩሲያ እና የዩክeሬን ጦርነት በዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ብርቱ ጫና ማሳደሩን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሹማምንት ገልጸዋል። "የጦርነቱ ጫና ከዓለም አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) 86 በመቶ የሚሆነው የ143 [አገራት] ኤኮኖሚዎች ትንበያ እንዲቀንስ አድርጓል" ሲሉ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ ተናግረዋል። ምስል Alexander Ermochenko/REUTERS

ከሩሲያ የጠበቀ የንግድ እና የሐዋላ ትሥሥር ያላቸው የምሥራቅ አውሮፓ እና የመካከለኛው እስያ አገራት የበረታ ጫና የሚደርስባቸው አገራት ናቸው። ከጦርነቱ በፊት በሸቀጦች ዋጋ መጨመር፤ በአቅርቦት እና በፍላጎት አለመጣጣም የበረታው የዋጋ ንረት ለበርካታ አገራት "ግልጽ እና ወቅታዊ አደጋ" ሆኖ እንደሚቆይ የዓለም አቀፉየገንዘብ ተቋም ሹማምንት አስጠንቅቀዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ማዕከላዊ ባንኮች የገንዘብ ፖሊሲ ቁጥጥራቸውን ለማጥበቅ እንደተገደዱ ፒየር ኦሊቪዬ ተናግረዋል። በዚህ ላይ ከጦርነት የተያያዙ ምጣኔ ሐብታዊ ረብሻዎች ይኸን ጫና ያባብሱታል። በአሜሪካ እና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ይኸው የዋጋ ንረት በ40 ዓመታት ከፍተኛ ከሚባለው ደረጃ ላይ መድረሱን የተናገሩት ፒየር ኦሊቪዬ ለረዥም ጊዜ ዓለምን እየተገዳደረ እንደሚቆይ ጠቅሰዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯ በሶስት ዋና ዋና መንገዶች ወደ ዓለም ኤኮኖሚ የተሻገረ ጫና እንደፈጠረ የተናገሩት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ "የመጀመሪያው ስንዴ፣ ነዳጅ ዘይት፣ ጋዝ እና ብረታ ብረት የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ ላይ የተፈጠረ ነው። ሁለተኛው በዋጋ ግሽበት ላይ ያሳደረው ጫና፣ ማዕከላዊ ባንኮች ከሌላው ጊዜ በተለየ በፍጥነት ጥብቅ ቁጥጥር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስገደድ እና በማደግ ላይ በሚገኙ ገበያዎች ያስከተለው መዘዝ ነው። ሶስተኛው በገንዘብ ዝውውር እና በሐዋላ ላይ ያስከተለው ነው። ከጦርነቱ በኋላ የገንዘብ ሥርዓቱ ምን ሊመስል እንደሚችል ጭምር ጫና አሳድሯል" ሲሉ ተናግረዋል። ዳይሬክተሯ የጦርነቱን መዘዝ ከሰብዓዊነት አኳያ ሲታይ ከፍተኛ ጫና ያስከተለው በምግብ ዋጋ ላይ ነው። ምክንያቱም ይኸ ቀድሞም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ብርቱ በነበረ የምግብ ዋስትና እጦት ላይ የታከለ ነው። በተወሰኑ አገሮች መጥፎ የምርት መጠን እንደነበረ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ አገራት የአንበጣ መንጋ ያስከተለውን ጫና ልብ ማለት ያስፈልጋል። አሁን ደግሞ ጦርነቱ የዓለምን ደሐ ቤተሰቦች የበለጠ እየተጫነ ነው" ብለዋል።

እሸቴ በቀለ