1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ጉድለት የተጫነው የ2015 የኢትዮጵያ በጀት

ረቡዕ፣ ሰኔ 8 2014

የኢትዮጵያ መንግሥት ለ2015 ያዘጋጀው በጀት 231.4 ቢሊዮን ብር የተጣራ ጉድለት ያጋጥመዋል ተብሎ እንደሚገመት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል። ይኸን ለመሙላት መንግሥታቸው 224.5 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ፤ 6.9 ቢሊዮን ብር ከውጪ አገር ለመበደር እንዳቀደ የገንዘብ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/4Ckab
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ጉድለት የተጫነው የ2015 የኢትዮጵያ በጀት

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባለፈው ሣምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2015 በጀት ድልድልን ሲያስረዱ ደጋግመው ኤኮኖሚው የተጫኑትን ሥጋቶች ከመጠቆም አልተቆጠቡም። ሚኒስትሩ የመንግሥታቸው ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት "ለታለመለት ዓላማ ብቻ" እንዲሁም "በቁጠባ" እንዲጠቀሙ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። አቶ አሕመድ "ለ2015 ተደግፎ የቀረበው ረቂቅ የፌድራል መንግሥት በጀት ባለፉት አመታት ከተበጀተው አንጻር ጭማሪ ቢኖረውም የልማት ፍላጎቶቻችንን ለማሳካት በቂ ነው ለማለት አዳጋች ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የ2015 በጀት 786.61 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ መደበኛ ወጪ 345.12 ቢሊዮን ብር ሲሆን የካፒታል ወጪ 218.11 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ለክልል መንግሥታት ድጋፍ 209.38 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 14.0 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። "የመደበኛ ወጪው አብዛኛው ለዕዳ ክፍያ፣ የአገር ደህንነትን ለማስጠበቅ፣ በጦርነቱ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ለሚያስፈልግ የዕለት ዕርዳታ ለአፈር ማዳበሪያ [ግዢ] እና ለስንዴ ድጎማ ትልቅ ትኩረት የሰጠ ነው" ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የ2015 የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የካፒታል በጀት በአንጻሩ በመካሔድ ላይ የሚገኙ ነባር ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ፣ በጦርነት ምክንያት የወደሙ መሠረተ-ልማቶች እና አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት እና መልሶ ለማቋቋም ቅድሚያ የሰጠ ነው።

Äthiopien Parlament Addis Abeba
አቶ አሕመድ ሽዴ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የመንግሥታቸው ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት "ለታለመለት ዓላማ ብቻ" እንዲሁም "በቁጠባ" እንዲጠቀሙ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ምስል Solomon Muche/DW

የበጀቱ ትኩረት ወዴት ነው?

ከ2015 መደበኛ እና ካፒታል በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው የዕዳ ክፍያ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ያዘጋጀው የበጀት ሰነድ እንደሚያሳየው ለዕዳ ክፍያ ብቻ 125.96 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። ይኸም ከአጠቃላይ በጀቱ አኳያ 22.36 በመቶ ድርሻ አለው። መከላከያ በአንጻሩ በ84 ቢሊዮን ብር የበጀት ድርሻ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባለፈው ግንቦት 30 ቀን 2014 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ "ከአጠቃላይ ተደግፎ ከቀረበው የፌድራል መደበኛ እና ካፒታል በጀት ውስጥ 37.5 በመቶው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለውኃ እና ኢነርጂ፣ ጤና፣ የከተማ ልማት እና ግብርና ዘርፎች የተመደበ ነው። ለእነዚህ ዘርፎች በ2014 ከተደለደለው የበጀት ድርሻ አንጻር የበጀት ድርሻው ቅናሽ ያሳየ ሲሆን ለዚህም ዋናው ምክንያት ለዕዳ ክፍያ፣ ለመከላከያ፣ ለመልሶ ማቋቋም፣ ለዕለት ዕርዳታ እንዲሁም ለማዳበሪያ እና ለስንዴ ድጎማ የተመደበው ድርሻ በመጨመሩ ነው" ሲሉ መንግሥት ያተኮረባቸው ዘርፎች ያሳደረውን ተጽዕኖ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚቀጥለው ዓመት ለመንገድ 66.23 ቢሊዮን ብር፣ ለትምህርት 64.67 ቢሊዮን ብር፣ ለጤና 19.33 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለግብርና 18.47 ቢሊዮን ብር መድቧል።

የክልሎች ድጋፍ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው የ2015 በጀት 209 ቢሊዮን 380 ሚሊዮን ብር ለክልሎች ድጋፍ መድቧል። ከዚህ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል በ71 ቢሊዮን ብር ቀዳሚ ሲሆን የአማራ ክልል 44.5 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል 26.5 ቢሊዮን፣ ሶማሌ ክልል 20.5 ቢሊዮን፣ ትግራይ ክልል 12.4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ሲዳማ 8.4 ቢሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል። በቅርቡ የተቋቋመው የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በተካተተበት የበጀት ድልድል 6.4 ቢሊዮን ሲመደብለት የአፋር ክልል 6.2 ቢሊዮን፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 3.7 ቢሊዮን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 3.2 ቢሊዮን፣ የጋምቤላ ክልል 2.7 ቢሊዮን፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 1.8 ቢሊዮን እንዲሁም የሐረሪ ክልል 1.5 ቢሊዮን ተመድቦላቸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቶ አሕመድ ሽዴ ማብራሪያ በሰጡበት ዕለት ለትግራይ ክልል የተመደበው 12 ቢሊዮን ብር በጀት ላይ ጥያቄ ተነስቷል። ሚኒስትሩ በጀቱ ለምክር ቤቱ የቀረበው በሕገ መንግሥቱ መሠረት መሆኑን አስረድተዋል።  ይኸ በጀት ለትግራይ ክልል የሚተላለፈው "ሕገ-መንግሥታዊ እና ሕጋዊ ሥርዓት ሲሟላ" እንደሆነ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። 

Tigray regional Gouvernement Emblem
ለትግራይ ክልል የተመደበው በጀት የሚተላለፈው "ሕገ-መንግሥታዊ እና ሕጋዊ ሥርዓት ሲሟላ" እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ምስል Tigray Communication affairs office

231 ቢሊዮን ብር ጉድለት የተጫነው በጀት

ጦርነት፣ ወረርሽኝ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በተከታተሉባቸው ዓመታት የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት ጭማሪ እያሳየ ሔዷል። የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት መንግሥት የሚበደረው ገንዘብ በአንጻሩ የዛኑ ያክል እያሻቀበ ይገኛል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የአገሪቱን ኤኮኖሚ በማዳከሙ፣ ጦርነቱ በሚካሔድባቸው አካባቢዎች ያሉ የኤኮኖሚ ተቋማት በመውደማቸው አሊያም እንቅስቃሴ በማቋማቸው 40 ቢሊዮን የሚደርስ የታክስ ገቢ በ2014 እንደማይሰበሰብ መገመቱን የመንግሥት የበጀት ሰነድ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ በዓመቱ "ዋና ዋና የልማት አጋሮች" የሚሰጡትን የበጀት ድጋፍ በማቋረጣቸው አገሪቱ 64 ቢሊዮን ብር ቀርቶባታል። ሁለቱ ምክንያቶች በኢትዮጵያ መንግሥት የዓመቱ በጀት ላይ የ104 ቢሊዮን ብር ጉድለት አስከትለዋል። ይኸን ለማካካስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዕቅዱ በላይ 278 ቢሊዮን ብር እንዲበደር ያስገድደዋል። ይኸ ከአጠቃላይ የአገሪቱ የምርት መጠን ያለው ድርሻ 5 በመቶ እንደሚደርስ የበጀት ሰነዱ ያሳያል።

አቶ አሕመድ ሽዴ "የፌድራል መንግሥት ለ2015 በጀት ዓመት 231.4 ቢሊዮን የተጣራ የበጀት ጉድለት እንደሚያጋጥመው ተገምቷል" ሲሉ ተመሳሳይ ጫና እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ይኸ የበጀት ጉድለት ከአmቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 3.4 በመቶ መሆኑን ያስረዱት የገንዘብ ሚኒስትሩ "የበጀት ጉድለቱ 224.5 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ፤ 6.9 ቢሊዮን ብር ከውጪ አገር ብድር በመውሰድ እንዲሸፈን የቀረበ ነው" በማለት መንግሥታቸው የሚከተለውን መንገድ ገልጸዋል።

Äthiopien North Wollo | Tigray Konflikt zerstörte Fahrzeuge
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአገሪቱ በጀት እና ምጣኔ ሐብት ላይ ብርቱ ጫና ካሳደሩ መካከል ይገኝበታል። ምስል Seyoum Getu/DW

ይኸ የበጀት ጉድለት መንግሥት ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ገበያው እንዲያስገባ በማስገደድ የዋጋ ንረትን እንደሚያባብስ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ በሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ "አመርቂ ውጤት ያልታየበት" ይኸው የዋጋ ንረት ጉዳይ እንደሆነ አሕመድ ሽዴ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። ምኒስትሩ እንዳሉት ታኅሳስ 2011 ከሶስት ገደማ ዓመታት በፊት 10.4 በመቶ የነበረው የዋጋ ንረት በሚያዝያ 2014 ወደ 36.6 በመቶ አሻቅቧል። በዓለም ገበያ የሸቀጦች ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረትን "የበለጠ አሳሳቢ" አድርጎታል። አሕመድ ሽዴ በበጀት ማብራሪያቸው እንዳሉት መንግሥት ለመቆጣጠር የሚወስዳቸው የመፍትሔ እርምጃዎች ውጤት የሚታየው "በረዥም ጊዜ" በመሆኑ የዋጋ ንረቱ በአጭር ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ላይፈታ ይችላል።"

አቶ አሕመድ ሽዴ "የዋጋ ንረቱን ለማርገብ ብድሩ በተቻለ መጠን በመንግሥት የግምጃ ቤት [ሰነድ] ሽያጭ እንዲወሰድ እና ሌሎች ጠንካራ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ በዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል" ሲሉ ተናግረዋል።

የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ፣ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ እና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር "ውጤት የሚጠበቀውን ያህል" እንዳይሆን እንዳደረገው የገንዘብ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሰነድ ያሳያል። ይኸው ሰነድ ተከታትለው በተፈጠሩት ቀውሶች "ከፍተኛ የፊሲካል ስጋቶች እየታዩ መሆናቸውን" ጠቁሟል።  

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ