1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ከኢትዮጵያ መንግሥት እጅ ሳይገባ የቀረው የአውሮፓ ኮሚሽን የልማት ዕርዳታ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 6 2014

የአውሮፓ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ግጭት በበረታባቸው አካባቢዎች የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ለመደገፍ ከ80 ሚሊዮን ዩሮ በላይ መድቧል። ገንዘቡ ለኢትዮጵያ ከታቀደ አንድ ቢሊዮን ዩሮ የልማት ዕርዳታ ላይ የሚቀነስ ነው። የልማት ዕርዳታው በሰባት ዓመታት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የታቀደ ቢሆንም ኅብረቱ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው አልጸደቀም

https://p.dw.com/p/4E4FI
Friedensnobelpreis EU Europäische Union Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ከኢትዮጵያ መንግሥት እጅ ሳይገባ የቀረው የአውሮፓ ኮሚሽን የልማት ዕርዳታ

የአውሮፓ ኮሚሽን በጎርጎሮሳዊው ከ2021 እስከ 2027 ባሉት ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዩሮ የልማት ዕርዳታ አዘጋጅቶ እንደነበር ይፋ አድርጓል። ይኸ "መልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም" በተባለ የኅብረቱ ማዕቀፍ የተዘጋጀ የልማት ዕርዳታ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ ሳይጸድቅ የቀረ ነው።  

የአውሮፓ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ባለፈው ሰኞ በኢትዮጵያ ጉዳይ በመከረበት ስብሰባ የተገኙት በአውሮፓ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ክፍል የምሥራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ዘርፍ ኃላፊ ዲዴየር ቬርሰ ምክንያቱን አብራርተዋል። 

"በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት እንደተቀሰቀሰ ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲፈቀድ፣ ግጭት እንዲቆም እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ ለህግ እንዲቀርቡ በመጠየቅ የበጀት ድጋፍ ክፍያ እንዲቆም ወስነዋል" ያሉት ዲዴየር ቬርሰ ኮሚሽነሯ በጥቅምት 2021 "በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በተመሳሳይ መርኅ ለኢትዮጵያ የታቀደው የመልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም የማጽደቅ ሒደት መራዘሙን ነግረዋቸዋል" ሲሉ ይኸ አንድ ቢሊዮን ዩሮ የልማት ዕርዳታ ያልጸደቀበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም በተባለው እና የአገሪቱን የልማት ሥራዎች በሚደጉመው የአውሮፓ ኅብረት መርሐ ግብር በጎርጎሮሳዊው ከ2014 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት 745 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች።

ወደፊት ኢትዮጵያ ከኅብረቱ የምታገኘውን የልማት ዕርዳታ ለማስቀጠል ከስምምነት ከደረሰች በየትኞቹ ዘርፎች ላይ ሊያተኩር እንደሚችል ዲዴየር ቬርሰ ጥቆማ ሰጥተዋል። "40 በመቶ ቅድሚያ የሚሰጠው ከባቢ አየር ለውጥን ለመቋቋም፣ ዘላቂ ግብርና እና አረንጓዴ ዕድገትን ለሚያካትተው ለአረንጓዴ ልማት ይሆናል" ያሉት ቬርሰ የጤና፣ የትምህርት አገልግሎቶች እና የስደተኞች እና ፈላሲያን ጉዳይ የሚያካትተው ሰብዓዊ ልማት ዘርፍ 40 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዴሞክራሲ የሰላም ግንባታ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮችን የሚያካትተው ዘርፍ ሶስተኛ ይሆናል። ይኸ ዕቅድ ከቀውሱ በፊት የነበረ መሆኑን የጠቆሙት ቬርሰ "ጊዜው ሲደርስ እነዚህን ማሻሻል አስፈላጊ ነው" በማለት ለውጥ ሊደረግበት እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።

Äthiopien Afar Zerstörung Gesundheitsbüro
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ባዳረሳቸው የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የትምህርት እና የጤና ተቋማት ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል። የአውሮፓ ኮሚሽን የመደበው ገንዘብ በተለይ በሁለቱ መሠረታዊ አገልግሎቶች የታቀደ ነው። ምስል Afar Health Bureau

የአውሮፓ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍ ያቋረጠው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተቀሰቀሰ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር። የተቋረጠውን የበጀት ድጋፍም ሆነ የልማት ዕርዳታ ለማስቀጠል ኮሚሽኑ እና የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል። የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት፣ ግጭት ማቆም እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው የሚጠረጠሩትን ተጠያቂ ማድረግ ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል ይገኙበታል።

ባለፈው ሐምሌ 4 ቀን 2014 የተካሔደውን ውይይት በሰብሳቢነት የመሩት የአውሮፓ ምክር ቤት የልማት ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር ፒየሬት ሔርበርገር ፎፋና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቅድመ-ሁኔታዎቹን እንዳላሟሉ ተናግረዋል። "የተቋረጠውን የበጀት ድጋፍ ለማስቀጠል እና ከ2021 እስከ 2027 የታቀደውን የመልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም ለማጽደቅ የአውሮፓ ኅብረት ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እስካሁን በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ባለመሟላታቸው እናዝናለን" ያሉት ፒየሬት ሔርበርገር ፎፋና "ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አኳያ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ተጋላጭ የሆነውን ማኅበረብ ለማገዝ የአውሮፓ ኅብረት አማራጭ ሐሳቦች መመልከት መጀመሩ መልካም ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ለድርድር የታየውን ዝግጁነት፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ረገድ የተደረገውን መሻሻል እና ግጭት ማቆምን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ለውጦች መኖራቸውን ገልጸዋል። በአውሮፓ ኅብረት የውጭ ግንኙነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ቀንድ ምክትል ኃላፊ ካሪን ዮሐንሰን ታይተዋል ያሏቸውን መሻሻሎች ኅብረቱ እንደሚደግፍ አስገንዝበዋል። የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ "አካታች የሰላም ድርድር" ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም እንዳለው የተናገሩት ካሪን ዮሐንሰን ለትግራይ የሚቀርበው ሰብዓዊ ዕርዳታ መሻሻል ቢያሳይም በግጭት ብቻ ሳይሆን በድርቅ ጭምር ችግሩ በመባባሱ በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። በክልሉ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮምዩንኬሽን እና ባንክን የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ መሆናቸውን በነዳጅ እና የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ "ገደብ" መደረጉንም ለአውሮፓ ምክር ቤት አስረድተዋል።

Pressebild Red Cross, Rotes Kreuz | Äthiopien Tigray, Hilfe
ለትግራይ የሚቀርበው ሰብዓዊ ዕርዳታ መሻሻል ቢያሳይም በግጭት ብቻ ሳይሆን በድርቅ ጭምር ችግሩ በመባባሱ በቂ እንዳልሆነ የአውሮፓ ኅብረት ኃላፊዎች ተናግረዋል። ምስል ICRC

ካሪን ዮሐንሰን "በአደባባይም ይሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባለን ግንኙነት አቋማችን ሁልጊዜም ግልጽ እና የማይዋዥቅ ነው። በአገሪቱ የሚታየውን መሻሻል በዋናነት በሶስት ጉዳዮች እንከታተላለን። የመጀመሪያው የተኩስ አቁም እና የኤርትራ ወታደሮች ከአገሪቱ መውጣት ነው። ሁለተኛው የተሟላ እና የማይተጓጎል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሲሆን ሶስተኛው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙትን ተጠያቂ ማድረግ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ባለፈው ሰኞ በተካሔደው ስብሰባ የአውሮፓ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ መንግሥት ለመስጠት ካዘጋጀው ገንዘብ ውስጥ ቆንጠር በማድረግ በአገሪቱ ግጭት በበረታባቸው አካባቢዎች የትምህርት እና የጤና አገልግሎትን ለመደገፍ 81.5 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ መመደቡን ይፋ አድርጓል። ገንዘቡ በዋናነት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በደረሰባቸው የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ለሚከናወኑ ሥራዎች የታቀደ ነው።

በአውሮፓ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ክፍል የምሥራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ዘርፍ ኃላፊ ዲዴየር ቬርሰ "የመልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም (multiannual indicative program) ማዕቀፍ አንድ ቢሊዮን ዩሮ ነው። በዚህ ላይ የታገደው 142 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጋፍ አለ። ከዚህ ውስጥ በተለይ ለትምህርት እና ለጤና 81.5 ሚሊዮን ዩሮ የተናጠል እገዛ ለማድረግ አቅርበን ዛሬ ጸድቋል" ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ለምግብ ዋስት እና የሰላም ግንባታ ዘርፎች ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን እንደሚመድብ ኃላፊው ተናግረዋል። ለሁለቱ ዘርፎች የሚመደበው ለኢትዮጵያ የልማት ዕርዳታ ከተዘጋጀው ገንዘብ ላይ የሚቆነጠር ሲሆን እስከ መጪው ታኅሳስ መጨረሻ ሊጸድቅ እንደሚችል ዲዴየር ቬርሰ ጥቆማ ሰጥተዋል። ይሁንና የአውሮፓ ኮሚሽን ገንዘቡን በቀጥታ ለኢትዮጵያ መንግሥት የመስጠት ሐሳብ የለውም። ቬርሰ "ገንዘቡን በመንግሥት አገልግሎት በኩል ወጪ የምናደርግ አይሆንም። በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ሥራ ላይ የሚውል ነው" ብለዋል። የአውሮፓ ኮሚሽን የመደበው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን ያመኑት ዲዴየር ቬርሰ ነገር ግን መነሻ እንደሆነ ጠቁመዋል።

እሸቴ በቀለ