1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

"በምን አፌ ነው ቤተሰቦቼን ደውዬ ከዚህ አለሁ የምላቸው?" ኢትዮጵያዊው ከሊቢያ እስር ቤት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 13 2014

በሊቢያ እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት የሰዎች አሸጋጋሪዎች በገመድ እየገረፉ፣ ፕላስቲክ አቃጥለው ከገላ ላይ እያንጠባጠቡ ስደተኞች ገንዘብ እንዲያስልኩ ያስገድዳሉ። "ተደብድቦ ማስላክ የማይችል" ከአንዱ አዘዋዋሪ "ትልቅ ጭካኔ" ላለው ይሸጣል። ገንዘቡ ከቤተሰቦች ለሰዎች አዘዋዋሪዎች ወይም ተባባሪዎቻቸው በኢትዮጵያ ባንኮች ይተላለፋል

https://p.dw.com/p/4EQ66
Migranten in Libyen
ምስል DW/N. Porsia

"በምን አፌ ነው ቤተሰቦቼን ደውዬ ከዚህ አለሁ የምላቸው?" ኢትዮጵያዊው ከሊቢያ እስር ቤት

ቴድሮስ በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል ከተንጣለለው የሜድትራኒያን ባህር ላይ በመስከረም 2013 ራሱን ያገኘ ለት ተስፋ ነበረው። ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ለመድረስ ሱዳን፣ ቻድ እና የሰሐራ በርሐን ያቋረጠው ወጣት "ከወደፊትህ የሆነ ተስፋ አለ። ከእንደዚህ ዓይነት ሲዖል ከሆነ አገር ሰላም ወዳለበት አገር እየሔድክ ነው" ሲል የተስፋውን ምንጭ መለስ ብሎ ያስታውሳል።

ቴድሮስ እና አብረውት አውሮፓ ለመግባት የጀልባ ጉዞ የጀመሩ ሰዎች ሶስት ዕድል አላቸው። አንድ እንዳቀዱት ባህሩን አቋርጦ አውሮፓ መግባት፤ ሁለት በባህሩ ላይ በሚፈጠር አደጋ እንደ በርካታ አፍሪካውያን ሁሉ ሰጥሞ ሞቅረት፤ ሶስት በሊቢያ የባህር ጠባቂዎች ጉዟቸው ተሰናክሎ ወደ ኋላ መመለስ።

"በሊቢያ ወታደሮች ተይዞ ከመመለስ ብዙ ሰዎች ባህር ላይ ጠልቆ መሞትን ይመርጣሉ። ምክንያቱም ወደ እስር ቤት ነው የምትገባው" ይላል ቴድሮስ። "ከእስር ቤት ካልከፈልክ አትወጣም። እስክትከፍል ያለውን ስቃይ እና መከራ ልነግርህ አልችልም" ሲል በተለይ የመጨረሻው አማራጭ እንደሚጠላ ያስረዳል።

ወጣቱ የተመኘው ቀርቶ የፈራው ደረሰ። ከትሪፖሊ አቅራቢያ ከሚገኘው የባህር ጠረፍ የተነሳው ጀልባ ስድስት ሰዓታት ገደማ እንደተጓዘ በሊቢያ ወታደሮች ተገታ። ቴድሮስ አውሮፓ አልሞ ሊቢያ እስር ቤት ገባ። እስር ቤት ግን አልቀረም።

"ከእስር ቤት እንደገና ከፍለን ወጣን" የሚለው ኢትዮጵያዊው ወጣት ገርጋሪሽ በተባለ የትሪፖሊ አካባቢ በመስከረም 2013 በሊቢያ የጸጥታ ኃይሎች ከታፈሱ ስደተኞች አንዱ ነው።  አካባቢው ኤርትራውያን፣ ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሊያውያን እና ሱዳናውያን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች ይኖሩበት የነበረ ነው።

Migranten in Libyen
እነዚህ የሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ በሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ከመስጠም የዳኑ ስደተኞች ናቸው። ስደተኞቹ ወደ ሊቢያ እስር ቤቶች ከተመለሱ በኋላ የሚገጥማቸው ፈተና ብርቱ እንደሆነ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ የገጠማቸው ተናግረዋል።ምስል DW/N. Porsia

መታሰር …መፈታት…መታሰር…መፈታት

ጎውት ሻል ወይም  አል-ምባኒ እና ሻራ ዛውያ የተባሉ ሁለት እስር ቤቶች የሊቢያ የጸጥታ አስከባሪዎች ገርጋሪሽ ከተባለው የትሪፖሊ አካባቢ በጅምላ ያፈሷቸውን ስደተኞች እና ፈላሲያ ያጎሩባቸው ናቸው። ድንበር የለሽ ዶክተሮች (MSF) የተባለ የግብረ ሰናይ ድርጅት በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት በአጠቃላይ 5 ሺሕ ገደማ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቆ ነበር። በሊቢያ የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ሴቶች እና ሕጻናት ይገኙበታል። በግብረ ሰናይ ድርጅቱ ሪፖርት መሠረት በእስር ቤቶች ስደተኞቹ ድብደባ እና ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ለአስከፊ የመብቶች ጥሰት ተጋልጠዋል። እጅግ በተጨናነቁት እስር ቤቶች እንደ ቴድሮስ ያሉ ስደተኞች የሚያገኙት ንጹህ ውኃ እና ምግብ እጅግ ጥቂት እንደነበር ድንበር የለሽ ሐኪሞች የግብረ ሰናይ ድርጅት ሪፖርት ይጠቁማል። ድርጅቱ "ኢ ሰብዓዊ" ያለውን አያያዝ ግን ስደተኞቹ የሚቋቋሙት አልሆነም።

"ብዙ እንግልት፣ ስቃይ እና ሞት ነበር" የሚለው ቴድሮስ እስር ቤቱን ሰብረው በመውጣት ማምለጣቸውን ያስታውሳል። "ከዚያ በኋላ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሊቢያ ቢሮ ፊት ለፊት ሶስት ወር ሙሉ መንገድ ላይ በመተኛት አሳለፍን። ከዚህ አገር እንዲያስወጡን ብዙ ነገር አደረግን። ነገር ግን ምንም አይነት [መፍትሔ] አልተሰጠንም" በማለት ከሊቢያ ለመውጣት የተደረገውን ጥረት ያብራራል። ጥረታቸው መፍትሔ ሳያገኝ የቀረው እነ ቴድሮስ በስተመጨረሻ በሊቢያ ወታደሮች ተይዘው ኢይን ዛራ የተባለ እስር ቤት ገቡ።

እስራኤል ተመኝቶ ሊቢያ እስር ቤት መቅረት

ቴድሮስ ያለፉትን ሰባት ወራት  በትሪፖሊ ከተማ የሚገኘው እስር ቤት ካሉት በርካታ መጋዘኖች በአንዱ ከሌሎች 320 ሰዎች ጋር ኖሯል። በዚያ እስር ቤት ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና ሱዳናውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ዜጎች ይገኛሉ። ከኢትዮጵያ ሲወጣ ግብጽን አቋርጦ እስራኤል ለመግባት የተመኘው ክርስቲያን አንዱ ነው።

Libyen Schießerei in libyschem Haftzentrum nach Übergriffen von Migranten
በመስከረም 2013 በጸጥታ አስከባሪዎች የተያዙ ስደተኞች ቁጭ ብለው ይታያሉ። በወቅቱ በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ ከሚገኘው ገርጋሪሽ የተባለ ቦታ 5,000 የሚደርሱ ስደተኞች በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። ምስል Ayman Al-Sahili/REUTERS

"የደሐ ልጅ ነኝ" የሚለው ክርስቲያን "ከግብጽ ወደ እስራኤል ትሔዳለህ ብለውኝ ነው እንጂ ሊቢያ አስቤ አይደለም መጀመሪያ የወጣሁት" በማለት የጉዞው አቅጣጫ ሌላ እንደነበር ይገልጻል። ክርስቲያን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገረው ግብጽ ያደርሱኛል ብሎ ያመናቸውን የሰዎች አሸጋጋሪዎች መንገድ ተከትሎ ኻርቱም ገባ። ከኻርቱም በተመሳሳይ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በኩል ኡምዱርማን ደረሰ። ከኡምዱርማን ሲነሳም ሀሳቡ ግብጽ ቢሆንም የደረሰው ግን ሊቢያ ነበር።

"ከግብጽ በኋላ ወደ እስራኤል ልንሔድ ብለን ነው ያሰብንው። ደላላው ግን ግብጽ እልካችኋለሁ ብሎን ወደ ሊቢያ ነው የላከን" የሚለው ወጣት በሰዎች አዘዋዋሪዎች ድብደባ ተፈጽሞበታል። የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ስደተኞች በሚያከማቹበት "መክዘን" ገብቶ እንደነበር የተናገረው ክርስቲያን "ብር አስልኩ" የሚል ትዕዛዝ ከደረሳቸው መካከል አንዱ ነው።

"ተደብድቦ፤ ተገርፎ ገንዘብ ማስላክ የማይችል" ከአንዱ የሰው አዘዋዋሪ ለሌላው "ትልቅ ጭካኔ" ላለው ይተላለፋል። የመጀመሪያው የሰው አዘዋዋሪ "እንደዚህ አይነት ሰዎች አልከፍልም ብለዋል። አንተ ማስከፈል አቅም አለህ ወይ? ስንት ትከፍለኛለህ?´ [ይለዋል።] [ጨካኙ ደላላ] ´አይ አምጣልኝ እኔ አስከፍላለሁ" ብለው በመነጋገር እንደ ስምምነታቸው አንዱ ለሌላው ገንዘብ ከፍሎ ስደተኛው ተላልፎ እንደሚሰጥ ክርስቲያን ይናገራል።

አሁን ከቴድሮስ ጋር ኢይን ዛራ በተባለው እስር ቤት የሚገኘው ክርስቲያን እንደሚለው የሰዎች አዘዋዋሪዎች ስደተኞች ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲያስልኩ ለማስፈራራት ሰው ይገድላሉ፤ "እርጉዟን አይተው ጽንሷን አውቀው ያስወርዳሉ።"

በኤሌክትሪክ ገመድ እየገረፉ፣ ፕላስቲክ አቃጥለው ከሰውነት ገላ ላይ እያንጠባጠቡ ስደተኞች ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲያስልኩ የሚያስገድዱ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እንዳሉ ክርቲያን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። ወጣቱ እንደሚለው ይኸ አይነቱ ኢ-ሰብዓዊ ስቃይ የሚበረታው በኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ላይ ነው።

"ደላሎች አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በፊት ኤርትራውያን እና ሶማሊያዊም ነበሩ። ሴቶች አሉ፤ ወንዶች አሉ። አብዛኛው መጥፎ መጥፎ የሚባሉት ከኢትዮጵያ የሚባሉ ናቸው። ስማቸውን ይቀይራሉ" ሲል ኢይን ዛራ እስር ቤት የሚገኘው ስደተኛ ይናገራል። "እዚህ አገር እጃቸው ረጅም ነው። የህግ አካልም አብሯቸው ነው ያለው። የፈለጉትን ነገር ያስደርጋሉ። ደላሎች ከሌሉ አንድ ሊቢያዊ ስደተኛን ምንም ማድረግ አይችልም። በባንክ አካውንት ብር ተልኮ ኢትዮጵያዊው ደላላ ለሊቢያዊው ሲከፍለው እንጂ፤ አንድ ሊቢያዊ ከኢትዮጵያ ብር ማስወረድ፤ ማስላክ አይችልም" ሲል ያስረዳል።

Libyen Schießerei in libyschem Haftzentrum nach Übergriffen von Migranten
የርስ በርስ ጦርነት ባፈራረሳት ሊቢያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ባለመኖሩ ስደተኞች የታጣቂዎች ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ታጣቂዎቹ ስደተኞችን እየያዙ ገንዘብ እንዲያስልኩ እንደሚያስገድዱ ይናገራሉ። ምስል Ayman Al-Sahili/REUTERS

"…እንደ ልቤ ተንቀሳቅሼ መሥራት ስላልቻልኩ…"

በእነ ክርስቲያን ሕይወት የሚነግዱት የሰዎች አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን አስገድደው ስልክ ያስደውላሉ። የስደተኞቹ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች እና ወዳጆች ዒላማ ሊደረጉ ይችላሉ። የስደተኞች ለቅሶ እና ዋይታ ቤተሰቦች የተጠየቁትን ገንዘብ እስከ መክፈል ያደርሳቸዋል። ገንዘቡ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የስደተኞች ቤተሰቦች በኢትዮጵያ ባንኮች እዚያው ኢትዮጵያ ወደ ሚገኙ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ወይም ተባባሪዎች ይተላለፋል። ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ የስደተኞች ቤተሰቦችም ካሉበት ሆነው ገንዘብ እንዲያስተላልፉ ይደረጋል። የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ በተራቸው በሊቢያ ለተመሳጣሪዎቻቸው የድርሻቸውን ይሰጣሉ።

ክርስቲያን ግን እንደዚያ የማድረግ አቅም ያለው ቤተሰብ የለውም። ሲጀመርም በጥር 2008 ገደማ ከኢትዮጵያ የወጣው ድህነትን ሽሽት ነው። ኑሮን ለማሸነፍ። ዛሬ ቤተሰቦቹ ልጃቸው የት እንዳለ አያውቁም። የሰሐራ በርሐን ሲያቋርጥ፣ የሜድትራኒያን ባህርን ሲሻገር ብርቱ ፈረናዎች በተደጋጋሚ የተጋፈጠው ወጣት "ሊቢያ ይኸን ያክል ጊዜ አባከንኩ" ብሎ አይቆጨውም። በተደጋጋሚ እስር እና ድብደባ መንፈሱ አልተሰበረም። ቤተሰቦቹ ያለበትን አለማወቃቸው ግን ያንገበግበዋል።

"ከኢትዮጵያ ያስወጣኝ ነገር ቢኖር አንደኛ ነጻነት ነው። እንደ ልቤ ተንቀሳቅሼ መሥራት ስላልቻልኩ ነው" የሚለው ቴድሮስ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና የትግሪኛ ቋንቋዎች እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል። "ትግራይ ላይ ዘመዶች አሉኝ፤ ኦሮሚያ ላይ ዘመዶች አሉኝ። አማራ ክልል ዘመዶች አሉኝ" የሚለው ቴድሮስ ኢትዮጵያ "እንደፈለኩ ዘመዶቼ ጋ እየተንቀሳቀስኩ መጠየቅም ሆነ መስራትም የማልችልበት አገር ስለሆነ" ለስደት እግሩን እንዳነሳ ገልጿል። ቴድሮስ ከኢትዮጵያ የወጣው በሱዳን በኩል ነው። በሱዳን ለሶስት አመታት ሥራ ሞካክሯል። ከሱዳን በቻድ በኩል በሰዎች አዘዋዋሪዎች መንገድ ሊቢያ ሲደርስ በየርስ በርስ ጦርነት የታመሰችው አገር ለስደተኞች "ሲዖል" መሆኗን ቀድሞም ያውቃል።

Migranten in Libyen
በሊቢያዋ ሚስራታ በእስር ቤት የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ምስል DW/N. Porsia

የምግብ ሽሚያ እና የፖሊስ ዱላ በኢይን ዛራ እስር ቤት

የተሻለ ነጻነት ፍለጋ መንገድ የገባው እግሩ ግን ቴድሮስን ያደረሰው ለጊዜው በሊቢያ ዋና ከተማ ከሚገኙ እስር ቤቶች ከአንዱ ነው። የሰባት ወራት ማረፊያው የሆነው አይን ዛራ እስር ቤት ውኃ ጥም እና የምግብ እጥረት የበረታበት ነው። በቂ መጸዳጃ የለም። ከአይን ዛራ እስር ቤት የሚገኘው ቴድሮስ "ቢያንስ በሳምንት ሶስት መቶ እና አራት መቶ ሰው ይመጣል። በሳምንት ሶስት መቶ እና አራት መቶ ሰው ደግሞ ይወጣል። ከፍሎ የሚወጣ፤ የት እንደሚወስዷቸው የማይታወቅ ነፍ ነው" ሲል ያስረዳል።  "አዲስ ሰው በሚመጣበት ሰዓት የተዘጋጀው ምግብ ያንሳል። በሚያንስ ሰዓት ሽሚያ ነው የሚሆነው። በሰልፍ ይባላል፤ እንደገና ሰልፉ ይበታተን እና ተሻምተህ የምትወስድበት አጋጣሚ አለ" በማለት ተናግሯል። እንዲህ ለምግብ ሽሚያ ሲሆን አቅመ ደካሞች እና ህሙማን ምግብ ላይደርሳቸው ይችላል። 

ክርስቲያን እና ቴድሮስን መሰል ስደተኞች በእስር ቤት ኑሯቸው በሊቢያ ፖሊሶች ድብደባ እና ውክቢያ አያጣቸውም። "አንድ ሰው ስለጮኸ ወታደሮች ሰላሳ እና አርባ ሰው እዛ ክፍል ውስጥ ያስገቡና የሚደበድቡበት ሁኔታ አለ። አንድ ሰው ታሞ በሩን አንኳኩተን እንዲከፈት፣ እንዲናፈስ ወይም ደግሞ ህክምና እንዲያገኝ ብንጠይቅ ለስለስ ያለ ነገር አይመልሱልንም። ቀጥታ ወደ ዱላ ነው። ከዱላ በኋላ ነው አንተ የምትፈልገው ነገር ሊመጣልህ የሚችለው" ይላል ቴድሮስ።  

"መብት የሚባል ነገር የለም። አይታሰብም" የሚለው ወጣት የሜድትራኒያን ባህርን ለመሻገር ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ከእስር ቤት ለማምለጥ እንደሚሞክሩ አስረድቷል። እርሱ እና መሰሎቹ ግን አይሞክሩትም። ቴድሮስ "ወጥተህ የሚያጋጥምህ ነገር መከራ እና ስቃይ ነው። ማንም ሰው እዚህ ታጣቂ ነው። ስራ ልውሰድህ ይልህና አንድ ክፍል ውስጥ አሽጎህ ብር አሳውል [አስልክ] ነው የሚልህ። ወይም ደግሞ በግድ ያሰራኻል። ስለዚህ እኛ ለማምለጥ ወይም ለመውጣት አላሰብንም" በማለት ይናገራል።  "እዚህ ቆይተን ፈጣሪ ያለልንን ነገር ወይ በዩኤንኤችሲአር የምንወጣበትን መንገድ እንጠብቃለን" የሚለው ቴድሮስ አሁን ሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክር የነበረውን ያክል ተስፋ እንኳ የለውም። ስለ ነገ ሲጠየቅ "ምንም መፈናፈኛ የለም" የሚል ተስፋ መቁረጥ የተጫነው መልስ ከአንደበቱ ይሰማል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ