1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐማራ ድርጅቶች ደብዳቤ ለዲፕሎማቲክ ማኀበረሰቡ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 17 2014

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለመቋጨት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሠላም ድርድር ላይ የዐማራ ሕዝብ ውክልና እንዲኖረው ተጠየቀ። በኢትዮጵያና በውጭ የሚገኙ የዐማራ ድርጅቶች፣ ለዐለም ዓቀፉ ማኀበረሰብ ሰሞኑን ባስገቡት ደብዳቤ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር የዐማራ ሕዝብ መገለሉ በእጅጉ አሳስቦናል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4Furx
USA Hone Mandefro
ምስል Tariku Hailu/DW

«የዐማራ ሕዝብ በዚህ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ነው።»

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለመቋጨት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሠላም ድርድር ላይ የዐማራ ሕዝብ ውክልና እንዲኖረው ተጠየቀ። በኢትዮጵያና በውጭ የሚገኙ የዐማራ ድርጅቶች፣ ለዐለም ዓቀፉ ማኀበረሰብ ሰሞኑን ባስገቡት ደብዳቤ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር የዐማራ ሕዝብ መገለሉ በእጅጉ አሳስቦናል ብለዋል። ድርጅቶቹ ባስገቡት ደብዳቤ፦ የዐማራ ሕዝብ የጦርነቱ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ኾኖ ሳለ እንዲገለል ተደርጎ ድርድር ማድረግ ከመርኅ አንጻርም ከፍተኛ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል። ስለጉዳዩ የተጠየቁት የዲኘሎማሲና የግጭት አፈታት ባለሞያው አቶ ብርሃነመስቀል ነጋ፤ የድርጅቶቹ ጥያቄ ሕጋዊና በዐለም ዓቀፍ ደረጃ የተለመደ አሠራር በመሆኑ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።  

የድርድር ሂደቱን ከክሽፈት ለማዳን ርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቀውን ደብዳቤው ለዲኘሎማቲክ ማኀበረሰቡ ያስገቡት የዐማራ ድርጅቶች፣ በመላው ዓለም የሚገኙ መሆናቸውን፣ የዐማራ ማኀበር በሰሜን አሜሪካ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር አቶ ሆነ ማንደፍሮ ለዶይቸ ቬለ (DW) ገልጸዋል። «ይህ ደብዳቤ፣ የእኛን ማኀበር የዐማራ ማኀበር በሰሜን አሜሪካን ጨምሮ 28 ድርጅቶች በጋራ መጥተው በግልጽ የጻፉት ደብዳቤ ነው። እነዚህ 28 ማኀበራት በተለያዩ የዐለም ክፍል የሚገኙ ናቸው።ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ፣ በኒውዚላንድ በአውስትራሊያ፣በጀርመን፣በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት እንዲሁም በካናዳና በአሜሪካ የሚገኙ ማኀበራት ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ፣ በአማራው ትግል ውስጥ ትልቅ ሚና ያላቸው ማኀበራት በአንድ ላይ መጥተው በአንድ ድምጽ የጻፉት ደብዳቤ ነው።»

ድርጅቶቹ፣ ጦርነቱ በዐማራውና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰውን ጉዳት ስለምናውቅ፣ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እናደንቃለን ብለዋል። ይሁንና፣ የዐማራ ሕዝብ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር መገለሉ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው በደብዳቤው ላይ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። 

USA Berhanemeskel Nega
ምስል Tariku Hailu/DW

አቶ ሆነ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ፣ በጦርነቱ ትልቁ ተጎጂዎች ዐማራዎች ናቸው ይላሉ። «የዐማራ ሕዝብ በዚህ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ነው። በቁጥር እናስገድፈው እንኳን ቢባል በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ያለው በአማራ ክልል ውስጥ ነው። ወደ ሰባት ሚሊዮን የዐለም ምግብ ፕሮግራም በቅርቡ ሐምሌ ላይ ባወጣው ቅኝት በዐማራ ክልል ብቻ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የነፍስ አድን ዕርዳታ ይፈልጋሉ፤ይህ እንግዲህ ከሌሎች ክልሎች አንጻር ስናየው፣ ከዓፋር ክልል በአምስት እጥፍ፣ከትግራይ ክልል ደግሞ በሁለት እጥፍ በሚባል ደረጃ ከፍ ያለ ነው።ስለዚህ ይህንን ጉዳት የደረሰበት ኅብረተሰብ አግልሎ ድርድር ማድረግ፣ከመርህ አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ፣ይህ ድርድር ዐማራው ያለውን ፍላጎት አቅርቦ ምክክር እንዳያደርግ ዕንቅፋት ይፈጥራል አለመወከሉ የሚል ዐሳብ ነው የሚያንጸባርቀው።»

ድርጅቶቹ፣ ሂደቱ በተሻለ ሕጋዊ ሁኔታ ካልተመራ እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የማይወክል ከሆነ የመክሸፍ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል። ስለጉዳዩ ዶይቸ ቨለ የጠየቃቸው፣ የዲፕሎማሲና የግጭት አፈታት ባለሞያ አቶ ብርሃነመስቀል ነጋ፣ የድርጅቶቹ ጥያቄ ሕጋዊና በዐለም ዓቀፍ ደረጃ የተለመደ አሰራር በመሆኑ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።
«ይህ በጣም መረሰታዊ የሆነ ጥያቄ ነው፣ሕጋዊ ጥያቄ ነው። ያቀረቡት ጥያቄ እነዚህ የተለያዩ የዐማራ ድርጅቶች ሕጋዊ ነው። በዐለም ዓቀፍ ደረጃ ባለው ልምድም ሆነ ለፍትህም ሆነ ለሰላም በሚደረገው ዐለም ዓቀፍ ጥረት፣የተለመደ ነው እና መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባው ነው።»

ከ35 ዓመታት በላይ በመንግሥታቱ ድርጅት የዐለም ዓቀፍ ሥራዎች በተለይም በአፍሪካ ግጭቶች አወጋገድ ላይ ያገለገሉት አት ብርሃነመስቀል፣ድርድሩ ሁሉንም አካታች መሆኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል። «አደራዳሪዎቹም ቢሆን ሊከተሉት የሚገባው፣አካታችነት ነው።ብዙ ጠቀሜታ አለው።በተለይም ያ ስምምነት ሕጋዊ እንዱሆን የሁሉንም ጥቅም ያካተተ ኮምፕሬሄንሲፍ የሆነ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚረዳ ነው የሚሆነው።ትልቁ ሁኔታ ደግሞ ተግባራዊነት ኃላ ስምምነት ላይ እንኳ ቢደረስ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው፣ቅቡልነት ሲኖረው ነው በሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች እና ይህ ጥያቄ መሠረታዊ ነው። ከመጀመሩ በፊት በተለይ አደራዳሪዎቹ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትም ሆኑ ሌሎች የሚገቡት ሁሉ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ፣ የቅድመ ዝግጅት ላይ ማነው መሳተፍ ያለበት የሚለውን ጥያቄ ሲመለከቱ ሊያጠኑና ውሳኔ ሊሰጡበት የሚገባ ነው ማለት ነው።»

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ