1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፋር ክልል በጦርነቱ ከ200,000 በላይ ነዋሪ ተፈናቅሏል

ዓርብ፣ ነሐሴ 27 2014

ባለፈው ሳምንት እንደ አዲስ ባገረሸው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአፋር ማዕከላዊ ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ከ200 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ክልሉ ዐስታውቋል። በአካባቢውበተተኮሱ የከባድ መሣሪያ እሩምታዎች የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ የመቁሰል አደጋም ገጥሟል።

https://p.dw.com/p/4GLqc
Äthiopien l IDPs in Afar region
ምስል Seyoum Hailu/DW

በከባድ መሣሪያ እሩምታዎች የሰዎች ሕይወት አልፏል

ባለፈው ሳምንት እንደ አዲስ ባገረሸው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአፋር ማዕከላዊ ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ከ200 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ክልሉ  ዐስታውቋል። ከአደጋው ሸሽተው በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች እንዳሉት ያሎ ከተማ ላይ በተተኮሱ የከባድ መሣሪያ እሩምታዎች የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ የመቁሰል አደጋም ገጥሟል። በአካባቢዎቹ አለመረጋጋት ተፈጥሮም በርካቶች ቀዬያቸውን ለቅቀው ተሰደዋል ብለዋል። ይሁንና ነዋሪዎች በጎርፍ ምክንያት የፈለጉበት ስፍራ ለመድረስ መቸገራቸውና ርዳታም ለማግኘት መፈተናቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በበኩሉ አማጺያን መንገድ በመዝጋታቸውና በሌላ አቅጣጫም ጎርፍ ድልድዮችን በመደርመሱ ድጋፍ የሚያሻቸው ሰዎች ጋ መድረስ አዳጋች እንደሆነበት ገልጧል። 

አቶ ዑመር ኢናህ-አባ ሰሙኑን በአፋርና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ በአፋር ማዕከላዊ ዞን (ፈንቲረሱ) ያሎ ወረዳ በከባድ መሳሪያ ክፉኛ የቆሰሉትን ሶስት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በዱብቲ ሪፌራል ሆስፒታል ይገኛሉ። አቶ ዑመር ጦርነቱ የተከፈተበትን እለት ሲያስታውሱ የትግራይ ኃይሎች በማለዳ ወደ ያሎ ከተማ አቅጣጫ ሲመጡ በአከባቢው በቂ የአፋር ልዩ ኃይልና የአገር መከላከያ ሰራዊት ስለነበር የከፋ ነገር ያደርሱብናል ብለን አልጠበቅንም ይላሉ። «ይሁንና የትግራይ ኃይሎች ተኩስ ሲከፍቱ ሰራዊቱ ወዳለበት ሳይሆን ቀጥታ ከተማ ላይ አነጣጥረው በመተኮሳቸው ኅብረተሰቡን ለአስገዳጅ መፈናቀል ዳርገዋል» ነው ያሉት።

ተጎጂው እንደሚሉት አስቀድሞ ህብረተሰቡን የሚከላከል በቂ ሰራዊት መኖራቸውን በመተማመን ማንም ከቤት እንዳይወጣ ብባልም የደረሰው የከባድ መሳሪያ ሀሩር በርካቶችን ሃሳባቸውን አስቀይሯቸዋል፡፡ 

Äthiopien l IDPs in Afar region
ምስል Seyoum Hailu/DW

በከተማው የሰው ቤት ላይ ያረፈው የከባድ መሳሪያ ተኩስ ተከትሎ ግን ማህበረሰቡ አከባቢውን ለቀው ወደ አፋር ደቡባዊ ዞን ለመሸሽ ጥረት ቢያደርጉም በጎርፍ የተጥለቀለቁ የአከባቢው ወንዞኝ ማህበረሰብ ወዳለመበት እንዳይደርስ እንቅፋት መሆኑን የአይን እማኙ አክለው ያብራራሉ፡፡ “በመቶ ብሮች ሲጓጓዙ የነበሩትን መንገድም ህዝቡ ከ7 ሺህ እስከ 10 ሺህ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ ተገደዋል” እንደ አስተያየት ሰጪው።፡

እስካሁን መዳረሻቸው ያልታወቀ ተፈናቃዮች ምንም አይነት ድጋፍም ሆነ የእለት ምግብ እያገኙ አለመሆኑ ነው የሚነገረውም፡፡ በላይ በሰሜናዊ የፈንቲረሱ ዞን በህወሓት ታጣቂዎች መንገድ መዘጋቱና ከአከባቢው ወደ ሌሎች ከተሞች የሚወስዱ መንገዶች በጎርፍ መጥለቅለቃቸው ደግሞ ለዚህ እንደ ምክኒያት ይቀርባል።

የያሎ ከተማ ተፈናቃዩ አቶ ዑመር እንደሚሉት አሁን ላይ ጦርነቱ ቁሟል ለማለት ቢከብድም የትግራይ ኃይሎች እንደከዚህ ቀደሙ በአከባቢው እንዳይስፋፉ በመንግስት ጥምር ጦር ታግደዋል ነው የሚሉት፡፡ ከያሎና ጎሊና ወረዳ ሶስት ቀበሌያት ግን ሰው ሙሉ በሙሉ መፈናቀሉን የአይን እማኙ አክለው ያብራራሉ፡፡

የአፋር ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነት አቶ መሃመድ ሁሴን በፊናቸው ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ እስከ ባለፈው ዓርብ ድረስ ለተከታታይ አራት ቀናት ከፍተኛ የነበረው ጦርነት ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ መጠነኛ መቀዛቀዝን አሳይቷል ብለዋል፡፡ እንደ አቶ መሃመድ መረጃ ከአከባቢው እስካሁን ባንድ ሳምንት ውስጥ 200 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ 

Äthiopien l IDPs in Afar region
ምስል Seyoum Hailu/DW

“ያሎ፣ ጎሊና፣ ኢዋ፣ አውራ እና መጋሌ ነዋሪዎች ከተፈናቀሉባቸው ወረዳዎች ዋንኞቹ ናቸው” እንደ ኃለካፊው ማብራሪያ፡፡ እንደ አቶ መሃመድ በያሎ ከተማ በተተኮሰው የከባድ መሳሪያ እሩምታ እስካሁን የሶስት ሰዎች ህይት ሲያልፍ ሌሎች ህጻናትና እናቶችም የከባድና ቀላል መቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ “ይሄ ደግሞ ከፍተኛ ዝናብ በሚጥልበት በአከባቢው ማህበረሰቡ በየጫካውና ጢሻ ለመሰደድ ዳርጓል” ነው ያሉት፡፡ 

መንገዶቹን የሚያገናኛቸው ድልድዮች በከባድ ጎርፍ መወሰዳቸውና በሌላ በኩል መንገዶች “ጁንታ” ባሉት የትግራይ ኃይሎች በመዘጋታቸው የእለት ምግብ እንኳ ለተፈናቃይ ማህበረሰቡ ማድረስና ድጋፍ ማድረግ አዳጋች ሆኗል ብለዋልም፡፡ በተለይም አፋርና አማራ ክልሎች የሚዋሰኑበት ዞብል ተራራ አከባቢ ህብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ መፈናቀሉንና አከባቢው ከጦር ስጋት ነጻ ባለመሆኑ እርዳታ የሚደርስበት መንገድም የለም ነው ያሉት ኃላፊው፡፡ በባለፈው ሳምንት የከባድ መሳሪያ ተጠቂ ከሆኑት በብዛት በአከባቢው ሲታከሙ የከፋ ጉዳት ያጋጠማቸው ወደ ዱብቲ ሪፌራል ሆስፒታል መጥተው እየተረዱ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡  

የትግራይ ኃይሎች ባለፈው ሳምንት ዳግም ላገረሸው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግስት ጥምር ጦርን ተጠያቂ ሲያደርግ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ተንኳሽ ያለውን ህወሓት መራሽ የትግራይ ኃይሎችን በጠብ አጫርነት ከሷል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጀመረ ለሁለት ዓመታት ለሚጠጉ ጊዜያት ሺዎች ሕይወታቸው ሲቀጠፍ በቢሊየኖች ገንዘብ የሚተመን ሃብት ደግሞ ወድሟል፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ