1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ክሽፈትና ያገረሸዉ ጦርነት

እሑድ፣ ነሐሴ 29 2014

ያሁኑ ዉጊያ የተጀመረዉ በቀዳሚዉ ጦርነት ያለቀዉ ሕዝብ ብዛት፣ የተደፈሩ ሴቶች ስትነት፣ የደረሰዉ ሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የጠፋዉ ሐብት መጠን በዉል ሳይታወቅ፣ ተፈናቃዮች በየመጠለያ ጣቢያዉ እንደሰፈሩ ነዉ።ተፋላሚ ኃይላት ለዉጊያዉ መጀመር አንዳቸዉ ሌላቸዉን እየወቀሱ፣ ለተጨማሪ ዉጊያ ከመዛዛት ባለፍ ለሕዝቡ ስቃይና ሰቆቃ ብዙም የተጨነቁ አይመስሉም።

https://p.dw.com/p/4GN8j
Tigray-Krise in Äthiopien
ምስል Ben Curtis/AP/dpa/picture alliance

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ክሽፈትና ዳግም ያገረሸዉ ጦርነት

 

የኢትዮጵያ መንግስት፣ የአማራ ልዩ ልዩ ኃይላትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሰሜን ወሎ ቆቦ አካባቢ ባለፈዉ ሳምንት እንዳዲስ የገጠሙት ዉጊያ አድማሱን እያሰፋ ከመቀሌ እስከ ሑመራ ጥግ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ ነዉ።ከሕዳር 2013 ጀምሮ እስከ ዘንድሮ መጋቢት ድረስ የዘለቀዉ የመጀመሪያዉ ዙር ዉጊያ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕይወት፣በቢሊዮን ብር የሚገመት ሕብት ንብረት ማጥፋቱ፣ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸዉ ማፈናቀሉ በሰፊዉ ይታመናል።

የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች መጋቢት አጋማሽ ላይ «ለሰብአዊነት» ያሉትን  ተኩስ አቁም አዉጀዉ ለመደራደር መፍቀዳቸዉን አስታዉቀዉ፣ አደራዳሪዎች ሰይመዉም ነበር።የርስበርስ ጦርነት፣ የጎሳና የኃይማኖት ጥቃት፣ረሐብና ስደት ያንገፈገፈዉ ኢትዮጵያዊ  የድርድሩን ጊዜና ሒደት በተስፋ ሲጠብቅ  አዲስ ዉጊያ መጫሩ በርግጥ ለብዙዎች አስደንጋጭ፣ አሳሳቢ፣ አስፈሪም ነዉ የሆነዉ።

ያሁኑ ዉጊያ የተጀመረዉ በቀዳሚዉ ጦርነት ያለቀዉ ሕዝብ ብዛት፣ የተደፈሩ ሴቶች ስትነት፣ የደረሰዉ ሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የጠፋዉ ሐብት መጠን በዉል ሳይታወቅ፣ ተፈናቃዮች በየመጠለያ ጣቢያዉ እንደሰፈሩ ነዉ።ተፋላሚ ኃይላት ለዉጊያዉ መጀመር አንዳቸዉ ሌላቸዉን እየወቀሱ፣ ለተጨማሪ ዉጊያ ከመዛዛት ባለፍ ለሕዝቡ ስቃይና ሰቆቃ ብዙም የተጨነቁ አይመስሉም።

Tigray-Krise in Äthiopien
ምስል UGC/AP/picture alliance

የኃይማኖት መሪዎች፣የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣የሲቢልና የሙያ ማሕበራት፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም አዲሱ ዉጊያ ባስቸኳይ ቆሞ ድርድር እንዲጀመር ያደረጉና የሚያደርጉት ጥሪም እስካሁን በተፋላሚ ኃይላትና በየደጋፊዎቻቸዉ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም።አዋቂዎች እንደሚሉት ጦርነት የፖለቲካ ክሽፈት ዉጤት ነዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ በየጊዜዉ የሚፈራረቁት ገዢዎች ጠብ-ልዩነታቸዉን በድርድርና ወይይት የማይፈቱበት፣ ሰጥቶ በመቀበል የፖለቲካ ባሕል የማይመሩበት ምክንያት እንዳጠያያቀ ነዉ።ፖለቲከኞች ሕዝብ ለማፋጀት፣ ሕይወት፣ ሐብት ንብረት ለማጥፋት የጨከኑበት ምክንያትም ለብዙዉ ታዛቢ ሲበዛ ግራ አጋቢ ነዉ።በዛሬዉ ዉይይታችን አዲሱ ዉጊያ የፈጠረዉን ስሜት፣መሠረታዊ ምክንያቱንና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ክሽፈት እንቃኛለን።

ነጋሽ መሐመድ