1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ኦሮሚያ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹት ተፈናቃዮች

ሰኞ፣ ነሐሴ 30 2014

በምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ የተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚሹ አስታወቁ። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በደረሰ ጥቃት ነው የተፈናቀሉት። አጋምሳ ቀበሌ ተፈናቅለው በአሙሩ ወረዳ ከተማ ውስጥ የተጠለሉ ዜጎች እስከ ዛሬው ዕለት 10,200 ሰዎችን መመዝገባቸውን ተናግረዋል። ከመንግሥት ምንም ድጋፍ እንዳላገኙም አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/4GRM2
Karte Äthiopien englisch

«ከመንግሥት ርዳታ እንዳላገኙ ይገልጻሉ»

ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከተማ ሻምቡ ከተማ በ92 ኪ.ሜ ገደማ ርቅት ላይ የሚትገኘው አሙሩ ወረዳ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም አንስቶ አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ጥቃቶች ነዋሪዎች ተፈናቀለው እንደበር ተገልጿል። በወረዳው ጃቦ ዶበን እና አጋምሳ ቀበሌዎች ውስጥ የጸጥታ ችግር በተደጋጋሚ መከሰቱንም ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከሰሞኑ ጥቃት የደረሰበት አጋምሳ ቀበሌ ከአሙሩ ወረዳ ከተማ በ24 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ማክሰኞ በደረሰው ጥቃት ከ10ሺ በላይ ሰዎች መፈናላቸውን እና ለረሀብ መጋለጣቸውን ገልጸዋል። በትናትው ዕለት 2 ሕጻናት ሕይወት ማለፉን  የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል እና ከአጋምሳ መፈናቀላቸውን የተናገሩ ነዋሪ አመልክተዋል።  

አስራ ስድስት የሚደርሱ የቁም እንስሳትና እና እህል እንደተዘረፉ የነገሩን ሌላው የተፈናቀሉ ነዋሪ ታጣቂዎች ባለፈው ቅዳሜም ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡ በአሙሩ አጎራባች በሆነው አንድ ወረዳ ውስጥ በተመሳሳይ በቅዳሜ ዕለት በደረሰው ጥቃት በርካታ ወደ አሙሩ ወረዳ መፈናቀላቸውን አክለዋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በደረሰው ጥቃት በጫካው ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች እየተገኘ መሆኑንና የሞቱት ቁጥርም እየጨመረ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ መንግሥት ድጋፍ እንዲያርግላቸውም ሀሳብ አቅርቧል።

በአሙሩ ነዋሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ አስመልክቶ ማብራርያ እንዲሰጡን ከወረዳው አስተዳደር፣ ከሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አስተዳደር ፣ ከክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ወይም አደጋ ስጋት ሥራ አመራር  እና የጸጥታ ዘርፍና ሌሎች ከሚመለከታቸወ አካላት መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካም።  የአሙሩ ወረዳ ቡሳ ጎኖፍ/የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዱኛ ደክስሳ በወረዳው ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸው ዝርዝር መረጃ  ለማግኘት ከሰዓት እንድንደውል ቃል ከገቡ በኋላ መልሰን ስንደውል ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በምዕራብ ኦሮሚያ  በተለያዩ ጊዜያ የተለያዩ ስም ባላቸው ታጣቂዎችና የጸጥታ አካላት ይደርሳል በተባለው ጥቃት በርካታ የሰው ሕይወት ሲያልፍ መቆየቱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። መንግሥት እና ሸማቂዎችም በአካባቢው በሚደርሰው ጉዳት እርስ በርሳቸው ሲወነጃጀሉም ማስተዋል የተለመደ ነው።

ነጋሳ ደሳለኝ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ