1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ግድያ የኢሰመኮ መግለጫ

ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 1 2014

በሲቪል ሰዎች ላይ ለደረሰው ግድያ፣ ጉዳት እና መፈናቀል ተጠያቂነት ሊረጋገጥ አንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ፡፡ ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ቀበሌያት ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በታጣቂ ኃይሎች ንጹሃን ላይ በደረሰ ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ20 ሺህ በላይ መፈናቀላቸውን አመልክቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4GUZk
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ከ20 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል

በሲቪል ሰዎች ላይ ለደረሰው ግድያ፣ ጉዳት እና መፈናቀል ተጠያቂነት ሊረጋገጥ አንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ቀበሌያት ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በታጣቂ ኃይሎች ንጹሃን ላይ በደረሰ ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ20 ሺህ በላይ መፈናቀላቸውን አመልክቷል፡፡

ኮሚሽኑ አክሎም መንግስት የፀጥታ አካላት ስምሪት ሲያካሄድ የሰዎች ስጋት ላይ ስጋት በማያሳድር መልኩ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያመለከተው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ ዛሬ አመሻሹን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ባለፈው ሳምንት ከማክሰኞ ጀምሮ እስከ ሃሙስ ቀጥሎ ነበር ባለው ንጹሃን ዜጎች ላይ ባነጣጠረው የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማው የታጣቂዎች ጥቃት፤ ቢያንስ ከ60 በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ሲገደሉ ከ70 በላይ ከከባድ እስከ ቀላል የመቁሰል አደጋን አስተናግደዋል፡፡ እንደ ኮሚሽኑ መግለጫ ከ20 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ ወደ ወረዳው ከተማ ኦቦራ ተፈናቅለዋል፡፡

በአከባቢው የነበሩ የመንግስት የፀጥታ አካላት አስቀድሞ ከስፍራው መነሳታቸው ዜጎችን ለጥቃት ዳርጓልም እንደ ኢሰመኮ መግለጫ፡፡ በኢሰመኮ ምርመራው የተሳተፉት የኮሚሽኑ የጂማ ጽ/ቤት ኃላፊ በዳሳ ለሜሳ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ ነሃሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ተብሎ የሚጠራው የታጣቀ ቡድን የወረዳዋን ከተማ ኦቦራን ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት የተነሳው ግጭት በመስፋቱ ነው ለንጹሃን እልቂት መነሻ የሆነው፡፡

ከዚያን ቀጥሎም በአገምሳ፣ ጆግ ምግር፣ ታም ኢላሙ፣ ጀቦ ዶበን፣ ጦምቤ ዳነጋበ፣ ጃዋጅ፣ ኛሬ፣ ለገ ሚቻ፣ ሉቁማ ዋሌ በሚባሉ ቀበሌያት ከነሃሴ 23-25 ቀን 2014 ዓ.ም. ነዋሪዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት የፈጸሙት ከአሙሩ ወረዳ ሀሮ አዲስ ዓለም ከተባለች ቀበሌ እና አጎራባች የአማራ ክልል ቡሬ ወረዳ የመጡ ታጣቂዎች ናቸው እንደ የኮሚሽኑ ተወካይ ማብራሪያ፡፡

በነዚህ የሁለት ቀናት የታጣቂዎች ጥቃት በአከባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የግድያ፣ ዝርፊያ እና ማፈናቀል ተፈጽሟል እንደ ኃላፊው ገለጻ፡፡

ኢሰመኮ በመግለጫው አክሎም፤ የደህንነት ስጋት ያልተቀረፈባቸው አከባቢዎች ውስጥ የሚጠቀሱት በዞኑ ውስጥ ካሉ ወረዳዎች በጃርደጋ ጃርቴ፣ ኪረሙ እና አቤ ዶንጎሮ ወረዳዎች ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈፀሙ እንደሚችሉ ስጋቶች አሉኝ ብሏል፡፡ በመሆኑም የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ወደ አከባቢዎቹ እንዲሰማሩ እና ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ነዋሪዎችን ወደ ተረጋጋ ህይወት የመመለስና ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል ነው ያለው፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳኒኤል በቀለ ኮሚሽኑ ስለጉዳዩ ክትትል ማድረጉን የሚቀጥል መሆኑንና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው ጥቃት እንዳሳሰባቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ የመንግስት የፀጥታ አካላት ስምሪት ስደረግም የነዋሪዎች ደህንነት የመጠበቅ መብት ለአደጋ እንዳይጋለጥ አሳስበዋል፡፡

ኢሰመኮ መግለጫ ያወጣበት ስለጥቃቱ ከዞንና ከክልል የፀጥታ እና የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን ዛሬም አልተሳካም፡፡

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ