1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የዉጪ ምንዛሪ እጥረትና የብሔራዊ ባንክ መመሪያ

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ መስከረም 4 2015

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርን ጠበቅ የሚያደርግ መመሪያ በሥራ ላይ አውሏል። መመሪያው የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የዋጋ ግሽበትና የበጀት ጉድለት በበረታበት ወቅት ገቢራዊ የሆነ ነው። ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ መመሪያው መንግሥት "አሉ በሚባሉ ቀዳዳዎች በሞላ የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ለመጨመር" ያደረገው ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4GqRx
Yinager Dessie Belay, äthiopischer Nationalplanungskommissar
ምስል picture-alliance/M.Kamaci

የኢትዮጵያ የዉጪ ምንዛሪ እጥረትና የብሔራዊ ባንክ መመሪያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክፍያ ለመፈጸም፣ በእርዳታ፣ በስጦታ ወይም አንዳች ግዴታ ለመወጣት የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ ወደ ሌላ ወገን ማስተላለፍ የሚከለክል መመሪያ ሥራ ላይ አውሏል። በብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ፊርማ ይፋ የሆነው ይኸ መመሪያ ከነሐሴ 30 ቀን 2014 ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ ነው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ "አሉ በሚባሉ ቀዳዳዎች በሞላ የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ለመጨመር ይመስላል። በተወሰነ ደረጃ ደግሞ አንዳንድ ሕጎቹን ላላ አድርጓቸዋል። ምን አልባት አላሰራ ብለው ይሆናል" ሲሉ ገፊ ምክንያቶቹን ያስረዳሉ።

የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ወይም ከአገሪቱ የሚወጡ መንገደኞች የሚይዙትን የብር እና የውጭ ምንዛሪ መጠን በዝርዝር አቅርቧል። በመመሪያው መሠረት ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ወይም ከኢትዮጵያ ለሚወጣ መንገደኛ በአንድ ጉዞ እስከ 3,000 ብር መያዝ ይፈቀዳል። ወደ ጅቡቲ የሚጓዙ መንገደኞች በአንጻሩ እስከ 10 ሺሕ ብር ድረስ በዚህ መመሪያ ተፈቅዶላቸዋል። ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረው መመሪያ ግን ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ወይም ከኢትዮጵያ ለሚወጡ መንገደኞች አንድ ሺሕ ብር ወደ ጅቡቲ ለሚጓዙ ደግሞ አራት ሺሕ ብር መያዝን የሚፈቅድ ነበር።

በአዲሱ መመሪያ እንደሰፈረው የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ወደ አገሪቱ በገቡ በ30 ቀናት ውስጥ የያዙትን የውጭ ምንዛሪ በሙሉ ፈቃድ ከተሰጠው የውጭ ምንዛሪ መሸጫ ቢሮ በመገኘት ወደ ብር መቀየር ወይም በውጭ ምንዛሪ መቆጠቢያ የባንክ አካውንት ማስገባት አለባቸው። ይሁንና የውጭ ምንዛሪው መጠን 4,000 ዶላር ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ የጉምሩክ ዲክላራሲዮን ማቅረብ ግዴታቸው ነው።

የጥቁር ገበያው ጥላ

በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ባንኮች አንድ ዶላር በ52 ብር ከ52 ሳንቲም ገደማ ይሸጣል። ከአንድ ዓመት በፊት በመስከረም 4 ቀን 2014 ባንኮች አንድ ዶላር በ45 ብር ከ78 ሳንቲም ገደማ ይመነዝሩ ነበር። ባለፉት አስራ ሁለት ወራት በባንኮች በኩል በሚከወነው የውጭ ምንዛሪ ግብይት የታየው ለውጥ 6 ብር ከ70 ሳንቲም ገደማ ጭማሪ መሆኑ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ያለበትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በቋሚነት ለመፍታት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር በተስማማው መሠረት ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን በሒደት ሲዳከም ቆይቷል። በተለምዶ "ጥቁር" እየተባለ በሚጠራው በጎንዮሹ ገበያ የአሜሪካው ዶላር የሚመነዘርበት ተመን ከቦታ ቦታ ቢለያይም ከባንክ ግብይቱ የመቀራረብ ምልክት እያሳየ አይደለም።

በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እየታደነም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ባልዋለው የትይዩ ገበያ በአዲስ አበባ አንድ ዩሮ እስከ 89 ብር፤ አንድ ዶላር እስከ 90 ብር ድረስ እየተመነዘረ እንደሚገኝ ዶይቼ ቬለ ባደረገው ማጣራት ለመረዳት ችሏል። ይኸ በመደበኛው እና የትይዩ ገበያ መካከል የሚታይ ልዩነት ታዲያ ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት ለመመሪያው ተግባራዊነት ትልቅ እንቅፋት ሊሆን ይችላል።

የመመሪያው ተግባራዊነት "ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ መንገደኞች የግል ምርጫ ላይ ነው" የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን "መንግሥት [የውጭ ምንዛሪ] ሊያገኝ ያሰበው [መንገደኞች] ራሳቸው ሰነድ ሞልተው፣ አሳውቀው ወይም ወደ ባንክ ሔደው በመመንዘር ነው። በይፋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመን እና በትይዩ ገበያው መካከል ካለው ስፋት አኳያ ሰዎች ፈቃደኛ ሆነው ወደ ባንክ በመሔድ ይመነዝራሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው" የሚል አቋም አላቸው። መመሪያው "ለማስገደድም አመቺ አይደለም" የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "እያንዳንዱን ሰው ለመፈተሽ ካሰቡ ተገቢ ባይሆንም ሌላ ጉዳይ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አብዱልመናን መመሪያው "ውጤት ያመጣል የሚል እምነት" የላቸውም።  

ይኸንን መመሪያ ተግባራዊ አለማድረግ ቅጣት እንደሚያስከትል ብሔራዊ ባንክ አስጠንቅቋል። ይኸ መመሪያ ላለፉት አምስት ዓመታት ገደማ ሥራ ላይ የነበረውን መመሪያ በመሰረዝ የተካ ነው። መመሪያው ከመውጣቱ በፊት የውጭ ምንዛሪ በእርዳታ ወይም በስጦታ ያገኙ ሰዎች ፈቃድ ባለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ቢሮ በመገኘት በ30 ቀናት ውስጥ ወደ ብር እንዲቀይሩ ታዘዋል። ይኸ መመሪያ በብሔራዊ ባንክ ልዩ ፈቃድ ካልሆነ በቀር በውጭ ምንዛሪ ግብይት መፈጸም ወይም የውጭ ምንዛሪን በእርዳታ እና በስጦታ መልክ ለሌላ ወገን ማስተላለፍን ይከለክላል።

ዶክተር ይናገር ደሴ የሚመሩት ብሔራዊ ባንክ ይኸንን መመሪያ ገቢራዊ ያደረገው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት በተጨማሪ በዋጋ ግሽበት፣ የመንግሥት የበጀት ጉድለት እና የዕዳ ጫና በሚፈተንበት ወቅት ነው። ብሔራዊው ባንክ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርን ጠበቅ የሚያደርጉ መመሪዎች ሥራ ላይ ሲያውል የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ፊርማ በጥር 2 ቀን 2014 ተግባር ላይ የዋለ መመሪያ የኢትዮጵያ ባንኮች በተለያዩ መንገዶች እጃቸው ከሚገባው የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶውን ወደ ማዕከላዊ ባንክ እንዲያስተላልፉ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የአገሪቱ ኤኮኖሚ ካሉበት መዋቅራዊ ችግሮች የሚነሳው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር የተወሰኑ መሻሻሎች ቢያሳይም ኹነኛ መፍትሔ ግን እስካሁን አላገኘም።

"ዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ በመጨመሩ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ከምታቀርበው ምርት ያገኘችው ገቢ ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ብዙ ጊዜ ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ነበረ" የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ "በአጠቃላይ ግን የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ችግር ብዙም የመሻሻል ለውጥ የለውም። የቡናም ይሁን ሌሎችም ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸው ሸቀጦች ዋጋ ቢሻሻልም እንደ ነዳጅ እና ስንዴ ያሉ የምናስገባቸው ሸቀጦች ዋጋቸው ስለ ጨመረ ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ከሰኔ 24 ቀን 2013 እስከ ሰኔ 23 ቀን 2014 ባለው አንድ አመት ወለድን ጨምሮ 2.1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ዕዳ ከፍላለች። ኢትዮጵያ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ ጥያቄ ካቀረቡ ሶስት የአፍሪካ አገሮች አንዷ ናት። ለኢትዮጵያ የተቋቋመው በቻይና እና በፈረንሳይ ተባባሪ ሊቀመንበርነት የሚመራ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ከመስከረም 2014 ጀምሮ ስብሰባዎች ቢያደርግም ሒደቱ ግን የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚለው "እንደሚጠበቀው ወደ ፊት አልተራመደም።"

"የአገሪቱ የኤኮኖሚ ማሻሻያ በተጠበቀው ፍጥነት" አለመሔድ ዶክተር አብዱልመናን ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ጋር ለሚደረገው ድርድር መዘግየት ዋና ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይናገራሉ። ዶክተር አብዱልመናን "አገሪቱ ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታም ሳይወስነው አይቀርም" የሚል እምነት አላቸው። "ኢትዮጵያ ተሳክቶላት የአከፋፈል ሁኔታው ቢስተካከል የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር ባይፈታም የተወሰነ" ፋታ ሊሰጥ ይችላል የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ "በአሁኑ ሰዓት 100 ሚሊዮን ወይም 200 ሚሊዮን ዶላር ማዘግየት ለውጥ ያመጣል። ነገር ግን አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ለውጥ ያመጣል ማለት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ባለፈው ሐምሌ 12 ቀን 2014 ባደረገው ስብሰባ ስለ አገሪቱ የምጣኔ ሐብት ይዞታ ማብራሪያ የሰጠው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አዲስ ስምምነት ለማበጀት ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጾ ነበር። ኢትዮጵያ በታኅሳስ 2012 ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) እና የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት (Extended Fund Facility) በተባሉ ሁለት ማዕቀፎች የ2.9 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራርማለች። ይሁንና አገሪቱ በሁለቱ ማዕቀፎች ለኢትዮጵያ የተከፈለው 309 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።  የተራዘመ የብድር አቅርቦት ባለፈው መስከረም 2014 የተቋረጠ ሲሆን ሁለተኛው ማዕቀፍ በአንጻሩ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ገደማ ያበቃል።

የኢትዮጵያን የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የሚያደርግ ፖሊሲ መጽደቁን የሚያስታውሱት ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ በአዲሱ ሥምምነት "እንደዚህ አይነት ከባባድ እርምጃዎች መካተታቸው አይቀርም" ሲሉ ይናገራሉ። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "በአጠቃላይ ተጠናቆ ወደ ተግባር እስኪገባ ሁለት ዓመት ሊፈጅ ይችላል። የኤኮኖሚ ችግር ብቻ አይደለም። የፖለቲካውን ጉዳይ ከግንዛቤ ሳያስገቡ አይቀሩም ብሎ ማሰቡ የዋህነት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ አገር በቀል የምጣኔ ሐብት ማሻሻያ የ2.9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሲያጸድቅ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በበኩሉ ተዘግቶ የቆየውን ገበያ የሚከፍቱ በርካታ ማሻሻያዎች ገቢራዊ ለማድረግ ተስማምቶ ነበር። ለውጭ ባንኮች ተዘግቶ የቆየው የባንክ አገልግሎት የሚከፍት ፖሊሲ የጸደቀ ሲሆን ወደ አገሪቱ ገበያ ብቅ የሚሉ ባንኮች እየተጠበቁ ነው።ከዚህ ቀደም ውድቅ የተደረገው ለሁለተኛ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ ፈቃድ የሚሰጥ ጨረታ ዳግም ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮ-ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻን ለግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ የኢትዮጵያ መንግሥት የደረሰበት ውሳኔ ሌላው ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎች በመጪዎቹ ወራት ተመሳሳይ እርምጃዎች ይጠብቃሉ።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ