1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመርሳ ተፈናቃዮች ተደጋጋሚ አበሳ

ረቡዕ፣ መስከረም 11 2015

አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በቆቦና አካባቢው በቅርቡ በነበረው ጦርነት ተፈናቅለው በመርሳ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች አንዳንዶቹ የሚቀርብልን የምግብ ርዳታ በቂ አይደለም ሲሉ፣ ሌሎች ከነአካቴው የምግብ ርዳታ አልደረሰንም ይላሉ። የአካባቢው አስተዳደር በመንግስትና በኅብረተሰቡ በተቻለ መጠን የምግብ እህል በየቀኑ በሚባል ደረጃ እየቀረበ ነው ይላል።

https://p.dw.com/p/4H9iR
Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

ተፈናቃዮቹ ቁጥራቸው ከ50,000 ይበልጣል ተብሏል


በህጻንነታቸው በሰፈራ ወደ ወለጋ ጊምቢ ተወሰዱ። ሰሜን ኢትዮጵያን ረሐብ በብርቱ የመታበት የ1977 ዓ.ም ወቅት ነበር። ወለጋ ጊምቢ አድገው፣ ጫካውን መንጥረው እና ከአውሬዎች ጋር ተታግለው በእግራቸው መቆም ጀመሩ። እናም ቤተሰብ መስርተውና ንብረት አፍርተው ኖሩ፤ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ። ከዚያ በኋላ ግን በአካባቢው በነበረው ዘር ተኮር ጥቃት ወለጋ መኖር አልቻሉም። ዳግም ተፈናቀሉ።  ከ38 ዓመታት በኋላ ሌጣቸውን ወደ ትውልድ ቦታቸው ቆቦ በዳግም ስደት ተመለሱ። እዚያም በተደጋጋሚ ተፈናቅለዋል። ጠንካራው አርሶ አደር አሁን ርዳታ ጠባቂ ናቸው። የእኚህ አርሶ አደር ሥንክሳር የብዙዎቹ ተፈናቃዮች ታሪክ መስተዋት ነው። 

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በቆቦና አካባቢው በቅርቡ በነበረው ጦርነት ተፈናቅለው በመርሳ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች አንዳንዶቹ የሚቀርብልን የምግብ ርዳታ በቂ አይደለም ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ከነአካቴው የምግብ ርዳታ አልደረሰንም ይላሉ፣ የአካባቢው አስተዳደር ደግሞ በመንግስትና በኅብረተሰቡ በተቻለ መጠን የምግብ እህል በየቀኑ በሚባል ደረጃ እየቀረበ ነው ይላል።

Äthiopien | Binnenvertriebene
ምስል Privat

አቶ ካሳዬ ሀሰን የተወለዱት ራያ ቆቦ ነው፣ ህፃን እያሉ በ1977 ዓ ም በሰፈራ ወደ ወለጋ ጊምቢ ወደተባለ አካባቢ እንደሄዱ ያስረዳሉ፣ በስፍራው አድገው ቤተሰብ መስርተውና ንብረት አፍርተው ሲኖሩ በ2010 ዓም በአካባቢው በነበረው ዘር ተኮር በሆነ ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው ከ38 ዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ ቦታቸው ቆቦ እንደመጡ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በቆቦ በነበረው ጦርነት እንደገና ወደ ደሴ ከተማ ተፈናቅለዋል። አካባቢውን መንግስት ሲቆጣጠረው ተመልሰው ወደ ቆቦ ሄደው ኑሮን ሀ ብለው ጀመሩ፣ በሬና መሬት እየተከራዩ ማረስም እንደጀመሩ ያስረዳሉ፣ በቅርቡ እንደገና የህወሓት ኃይሎች ቆቦንና አካባቢውን ሲቆጣጠሩ እኝህ አርሶ አደር 8 ቤተሰቦቻቸውንይዘው ንብረታቸውን ጥለው ወደ መርሳ እንደገና መፈናቀላቸውንና ለእንግልት መዳረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

“ 2010 ተፈናቅለን መጣን፣ አንዳንድ ነገር እየሰራን እንደፍየል እንደምንም፣ ተጋግዘን እያረስን ነበር ያንን ሁሉ በሮችም ገዝተን ነበረ፣ በሮችንም ወሰዷቸው፣ አሁን እኛ ዝም ብለን ራቁታችን አምናም ተቸገርነ፣ ዘንድርም ያው ተሰድደን ሁለት ዓመት ያው ስደት ነው አሁን ሶስተኛ መፈናቀሌ ነው ”

ሌላዋ ተፈናቃይም ከቆቦ ምንም ነገር ይዘው እንዳልወጡና ለሁለተኛ ጊዜ መፈናቀላቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡ ታጣቂዎቹ ለሁለተኛ ጊዜ ይመጣሉ ብለው እንዳላሰቡ የሚያስረዱት እኝሁ ተፈናቃይ ለሁለተኛ ጊዜ ተፈናቅለው በመርሳ ከተማ እንደሚገኙ ገልጠዋል፡፡ 

Äthiopien | Binnenvertriebene
ምስል Privat

ከቆቦ ተፈናቅለው በመርሳ የሚገኙት ሌላዋ ተፈናቃይ እንደሚሉት አንዳንድ ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች በአንዳንድ ድርጅቶች በኩል እገዛ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል፣ ሆኖም የምግብ አቅርቦቱ በቂ አይደልም፣ እስካሁንም እየተመገቡ ያሉት ተፈናቅለው ይዘው የመጡትን ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሌለዋ ተፈናቃይ ግን በምግብ በኩል፣ ምንም የተደረገ እገዛ እንደሌለ ነው ለዶይቼ ቬሌ ያስረዱት፡፡ “ያገኘነው ነገር የለንም፣ ርሀብ እየሞትን ነው ያለነው፣ የከረምነው ማለት ነው …ለእኛ አልደረሰንም እስካሁን በቃ የለም ትናንትና አንደኛው ድርጅት ብቻ ብርድልብስና የተወሰነ እቃ ነው ተሰጠነው ልጆቻችንን እስለቀስን ነው ያለነው፣ በምን ገንዘብም የለንም ዝም ብለን ነው የመጣን ራቁታችንን የምንበላው ምግብ የለንም፣ ዝም ብለን ነው ያለነው ርሀብ እሞትን ነው፡፡”

የህክምና እርዳታ እንደሌላቸውም ነው ተፈናቃዮቹ ያብራሩት፡፡ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ሀምሳ ሺህ ተፈናቃይ እንደሚገኙ አንድ የተፈናቃዮች አስተባባሪ ጠቁመው አብዛኛው ንብረቱ የተወሰደበትና በባዶ እጁ የመጣ ተፈናቃይ ነው ብለዋል፡፡

Äthiopien | Binnenvertriebene
ምስል Privat

በሰሜን ወሎ ዞን የመርሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መልካሙ ዓለሙ መንግስትና ህብረተሰቡ የምግብ እርዳታ በየቀኑ በሚባል ደረጃ እያደረገ እንደሆነ ገልጠዋል፣ የመጡበት አካባቢ ነፃ እስኪሆንና እስኪመለሱ ድረስ መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሌሎችም ባለሀብቶች እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አድርገዋል፡፡

በአማራ ክልል በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያቶች ከ11 ሚሊዮን በላይ ወገኖች የእለት ምግብ ርዳታ ፈላጊዎች መሆናቸውን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ