1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአጋምሳ ጥቃት የምርመራ ውጤት ዘገባ

ረቡዕ፣ መስከረም 11 2015

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፣ ኡሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) ታጣቂዎች ባለፈው ነሐሴ ወር ፈጸሙት ባለው ጥቃት 61 ዐማራዎች መገደላቸውን የዐማራ ማኀበር በሰሜን አሜሪካ ዐስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4HAHj
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ብሄር ተኮር ግድያዎችና አፈናዎች መፈጸማቸው ተገልጧል

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፣ ኡሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነግ ሸኔ)ታጣቂዎች ባለፈው ነሐሴ ወር ፈጸሙት ባለው ጥቃት 61 ዐማራዎች መገደላቸውን የዐማራ ማኀበር በሰሜን አሜሪካ ዐስታወቀ። ማኀበሩ፦ «ተበዳይ በዳይ ሆኖ የቀረበበት የአጋምሳ ከተማ የንጹሃን ዐማሮች የጅምላ ጭፍጨፋ» በሚል ርዕስ ባወጣው የምርመራ ውጤት ዘገባ ተገድለዋል ያላቸውን ሰዎች በስምና ጾታ ለይቶ ማረጋገጡን ገልጿል። ስለጉዳዩ ዶይቸ ቨለ (DW)ያነጋገራቸውና መንግስት «ኦነግ ሸኔ» በሚል በአሸባሪነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በበኩላቸው፣ የማኀበሩን ሪፖርት መሠረተ ቢስ ውንጀላ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። 

ባለፈው ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም በአጋምሳ ከተማ በሚገኝ ወታደራዊ ሠፈር ውስጥ የነበረ የኦሮሚያ  ልዩ ኃይል በድንገት ለነዋሪዎች አሳሳች መረጃ በመስጠት መውጣቱን፣የዐማራ ማኀበር በአሜሪካ ሪፖርት ያሳያል።

የኦሮሞ ልዩ ኃይልን መውጣት ዕግር በዕግር ተከትለውም፣መንግስት ኦነግ ሸኔ በማለት በአሸባሪነት የፈረጃቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች፣ወደ ከተማዋ በመግባት፣ካለፈው ነሐሴ 23 ቀን ጀምሮ ባሉት ቀናት ውስጥ ብሄር ተኮር ግድያዎች፣ አፈናዎች እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ብሏል። የማኀበሩ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር አቶ ሆነ ማንደፍሮ፣የዐማራ ማኀበር በአሜሪካ፣ በምርመራ ያረጋገጣቸው ያሉትን ጥቃቶች አስመልክቶ ለዶይቸ ቨለ ሲናገሩ፦ "የኦሮሞ ልዩ ኀይል መውጣቱን ተከትሎ፣ዕግር በዕግር የኦሮሞ ነጻነት ጦር ወይም ኦ ኤል ኤ በተለምዶ ኦነግ ሸኔ የምንለው ታጣቂ ቡድን ወደከተማዋ ገብቶ፣የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ፣ተኩስ በመተኮስና ኦሮሞ ነፃ ወጥታለች ይህ አካባቢ አዲሱ መንግስት እኛ ነን እያሉ የደስታ ተኩስ ይተኩሱ ነበር።ከዚሁ ጋር ተያይዞ የወጡ የኦሮሞ ወጣቶች፣ቄሮ የሚባሉት ከእነርሱ ጋር አብረው እየጨፈሩና እየተንቀሳቀሱ ዐማራዎችን ቤት ለቤት የማደንና የመግደል ዘመቻ አከናውነዋል።ይህ የሆነው እንግዲህ ነሐሴ 23 ቀን ነው።የእዛን ቀን ቤት ለቤት እየፈለጉ ዐማራዎችን ከመግደል በተጨማሪ ቤተክርስትያን ውስጥ ተጠልለው የነበሩና ቤተክርስትያን አገልጋይ የነበሩን ጨምሮ በርካታ ሰዎችተገድለዋል በነሐሴ 23 በነበረው ጭፍጨፋ።በስምና በጾታ የለየናቸው 61 ዐማራዎች  በዚህ ሪፖርት ውስጥ ተካትተዋል።ግን የተገደሉት ከዚያም በላይ እንደሚሆኑ እናምናለን።

USA Hone Mandefro
ምስል Tariku Hailu/DW

የምርመራ ሪፖርቱ፣ቢያንስ 20 ዐማራዎች፣በታጣቂዎች የዕገታ ተግባር ከተፈጸመባቸው በኋላ፣ ደብዛቸው መጥፋቱንም አመልክቷል።
አቶ ሆነ፣በወቅቱ ነበረ ስለተባለው የተኩስ ልውውጥ የሚከተለውን ተናግረዋል፤በግጭቱ ከዐሰር ያልበለጡ ኦሮሞዎች መገደላቸው ይነገራል።

"በአካባቢው ላሉ ዐማራዎች ከአጋምሳ ከተማ ውጭ፣ላሉ ገጠራማ ቀበሌዎች ሐሚኖሩ ዐማራዎች የአካባቢውን ገባገዳዎች በመሄድ ኦነግ ሸኔ ይህንን ግድያውን እንዲያቆምና ያገታቸውንም ዐማራዎች እንዲለቅ ልመና ሲያደርጉ ነበረ።ነገር ግን ይህ ውጤታማ አልነበረም።በመጨረሻም በማግስቱ በ24 እነዚሁ ዘመዶቻቸው የታፈኑባቸውና ዕጣፈንታቸውን ያላወቁ ዐማራዎች ተሰብስበው ወደ ከተማው ሲገቡ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከተማው በር ላይ ጠብቀው ተኩስ ከፍተውባቸው በሁለቱም ወገን ጉዳት እንደነበርና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተኩስ ልውውጡ ሂደት ከተማ ውስጥ የሚኖሩና የሚንቀሳቀሱ ዐስር ያልበለጡ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርታችን ያሳያል።"

Äthiopien Straße in Nekemt

ግድያውን በተመለከተ፣የዐማራን ሕዝብ እንደ በዳይ አድርገው የሚቆጥሩ ያሏቸውን ትርክቶች ዳይሬክተሩ በጽኑ ተቃውመዋል። ስለጉዳዩ ዶይቸ ቨለ የጠየቃቸው፣የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ አቶ ኦዳ ተርቢ በበኩላቸው፣የዐማራ ማኀበር በአሜሪካ በምርመራ አረጋገጥኹ ያለውን ሪፖርት መሠረተ ቢስ በማለት ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።
"ከዚህ ድርጅት የሚወጡ ሪፖርቶችን እንከታተላለን።በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ወቀሳውን ከራሱ ለማሸሽ ይሞክራል።በአጋምሳ የተከሰተውን ሁኔታ ስንመለከትም ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በርካታ የድንበር ወረራዎች ተፈጽመዋል።የጥቃት ሰለባዎቹም በመቶዎች ይቆጠራሉ።" ቃል አቀባዩ "የፋኖ ኀይሎች" ያሏቸውን ለጥቃቶቹ ተጠያቂ አድርገዋል።

ጥቃቶቹ፣የኦሮሞና የዐማራ ማኀበረሰቦችን ግንኙነት ለማበላሸት ሆን ብሎ የሚፈጸሙ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ አቶ ኦዳ ገልጸው፣እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ለማርገብ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። "ይህን በኦሮሞና ዐማራ ማኀበረሰቦች መኻከል ያለ አደገኛ ውጥረት እየተባባሰ መሄዱ በጣም አስጊ ነው።መፈታት ያለበትም በውይይት ነው"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ