1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የሁለት ዓመት ጦርነት፦ የሚሊዮኖች ሰቆቃ

Eshete Bekele
ሐሙስ፣ ጥቅምት 24 2015

የሁለት ዓመት ጦርነት ያስከተለው ዳፋ የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ነዋሪዎችን ለብርቱ ሰቆቃ ዳርጓል። "ልጆቻችን ይራቡ ይሆን?" ብለው የሚሰጉ የአይደር ሆስፒታል የሕክምና ዶክተር ሕሙማኖቻቸውን ማከም አለመቻላቸው ያብሰለስላቸዋል። በውጊያ የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ገበሬዎች፤ በጦርነት የወደሙ የአፋር የጤና ተቋማት ጠባሳቸው አልሻረም።

https://p.dw.com/p/4J29g
Äthiopien Tigray Panzer Wrack
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP

የሁለት ዓመት ጦርነት፦ የሚሊዮኖች ሰቆቃ

በመቐለ የአይደር ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ፋሲካ አምደስላሴ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ለሁለት ዓመታቱ ጦርነት መቋጫ ያበጃል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሥምምነት ሊፈራረሙ ሲዘገጃጁ "ተኩስ ለማቆም እንዲስማሙ ተስፋ አደርጋለሁ" የሚል ምኞት ነበራቸው። ዶክተር ፋሲካ በትዊተር የጻፉት መልዕክታቸው ግን ይኸ ብቻ አይደለም። "እባካችሁ" አሉ ዶክተር ፋሲካ "እባካችሁ መድሐኒቶች ላኩልን…ኢንሱሊን፣ አንቲ ባዮቲክስ፣ አይቪ ፍሉይድ፣ ክትባት…"

በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው እና ሁለት ዓመታት ያስቆጠረው ጦርነት ያስከተለው ቀውስ ዶክተር ፋሲካን ተስፋ አስቆርጧቸዋል። ለ730 ቀናት ገደማ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚል ውጊያ ውስጥ የቆዩት ተፋላሚ ኃይላት ከተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲደርሱ ይመኙ እንጂ መፍትሔ የሚጠብቁት ከፈጣሪ ነው። ተስፋ ያስቆረጣቸው ታመው ሕክምና የሚሹ ሕጻናትን መርዳት አለመቻላቸው ነው።

የሕክምና ባለሙያው የትግራይ የጤና አገልግሎት በጦርነቱ የደረሰበት ጫና ያስከተለው ዳፋ "የሚወልዱ ሴቶች፣ እርጉዞች፣ ሕጻናት እና ልጆች ላይ ይብሳል" ሲሉ ከመቐለ በዋትስአፕ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል። መድሐኒት ባለመኖሩ "ገንዘብ ያለውም ቢሆን መታከም አይችልም" የሚሉት ዶክተር ፋሲካ "በተለይ ገንዘብ የሌላቸው የታችኛው ማኅበሰብ ክፍል አባላት በጣም ተጎድተዋል" ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ ሬድዋን ሑሴን እና አቶ ጌታቸው ረዳ በደቡብ አፍሪካ የሰላም ሥምምነት ሲፈራረሙ
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ሥምምነት ቢፈራረሙም ይዘቱ እና አተገባበሩ ገና በውል አለየም። ሥምምነቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ለተፈጸመባቸው፤ አካላቸው ለጎደለ፤ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚፈይደው ካለ ወደፊት ይታያል።ምስል Themba Hadebe/AP/picture alliance

 

"አሁን እንባችን አልቋል"

ጥቅምት 24 ቀን 2013 በትግራይ የተቀሰቀሰው ውጊያ የሕክምና መምህር እና የቀዶ ሕክምና ባለሙያውን በሁለት ስለት ላይ አቁሟቸዋል። ፈተናው እንደ ሕክምና ባለሙያነታቸው ብቻ የገጠማቸው አይደለም። "ከቤተሰብ ጋር ተቆራርጠን አንገናኝም። ስልክ እና ኢንተርኔት የለም። ደሞዝ አይከፈለንም። ልጆቻችን እንዳይራቡ እንፈራለን። የተራቡ ሰዎች ሲለምኑ ስናይ በጣም እንከፋለን። የአገሪቱ ሁኔታም ያሳስበናል። ወዴት እየሔዱ እንደሆነ አናውቅም" ይላሉ ዶክተር ፋሲካ እርሳቸው እና የክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበትን ነባራዊ ሁኔታ ሲያስረዱ። "እንደ ጤና ባለሙያ እውቀቱ አለን፣ የማከም ክህሎቱ አለን" የሚሉት የአይደር ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ባለሙያ ቃል የገቡለትን ሥራ ማከናወን ሲያቅታቸው ፈታኝ እንደሆነ ገልጸዋል። "አሁን እንባችን አልቋም። በጣም ሐዘኔታ ውስጣችን አለ። ምንም ነገር ማድረግ አለመቻላችን በጣም ይረብሸናል" ብለዋል።

በትግራይ ክልል ከሚገኙ የጤና ተቋማት በአሁኑ ወቅት 9 በመቶው ብቻ በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። የመድሐኒት ብቻ ሳይሆን የህክምና እና የነዳጅ እጥረት ተቋማቱ አንገብጋቢውን ግልጋሎት እንዳይሰጡ ያገዷቸው ችግሮች ናቸው። መዳንን ሽተው ሕክምና ፈልገው ወደ ሆስፒታሎች የሚያመሩ ቢኖሩም ዶክተር ፋሲካ እንደሚሉት ተቋማቱ አገልግሎት መስጠት ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የትግራይ ክልል ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል የነበረውን ግንኙነት ቆርጦታል። የመንግስት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች እና ገበሬዎች ውትድርና ገብተው ተዋጊ ሆነዋል። ከመድሐኒት እና የሕክምና ግብዓቶች እጥረት ባሻገር ኤሌክትሪክ፣ ባንክ እና ቴሌኮምዩንኬሽንን የመሳሰሉ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል። ይኸ እንደ ክብሮም ያሉ በውጭ አገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን እየተብሰለሰሉ ኑሯቸውን በሰቀቀን የሚገፉ አድርጓቸዋል። ለዚህ ዘገባ ሲባል ስሙ የተቀየረው ክብሮም እንደ ከዚህ ቀደሙ ባሻው ሰዓት በትግራይ የሚገኙ እናት እና አባቱ ጋ ደውሎ ማውራት አይችልም። 

የትግራይ ኃይሎች አባላት በሐውዜን ከተማ
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የትግራይ ክልል ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል የነበረውን ግንኙነት ቆርጦታል። የመንግስት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች እና ገበሬዎች ውትድርና ገብተው ተዋጊ ሆነዋል።ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

"ማድረግ የምችለውን ነገር ሳላደርግ [ቤተሰቦቼን] ከዚህ ዓለም ባጣቸው ወንጀለኛነት ይሰማኛል" የሚለው ክብሮም ማገዝ እና መርዳት ባለመቻሉ ራሱን ይወቅሳል። "ትግራይ በሙሉ እንደ እኔ ቤተሰብ መሆኑን ነው የማውቀው። እናት ስትሞት እናቴ እንደሞተች ይሰማኛል። አንዲት ሕጻን ስትሞት የእኔ እህት ወይም የእኔ ልጅ  እንደሆነች ነው የማስበው" ይላል ክብሮም ከትውልድ ቀዬው ርቆ ያለበትን ሁኔታ ሲያስረዳ።

በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በሚመራው የትግራይ መስተዳድር መካከል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ጦርነት ሲቀሰቀስ መቐለ ነበር። የግል ሥራውን ለመከወን እና ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው ክብሮም በጦርነቱ ምክንያት ከመቐለ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ እናት እና አባቱን ማየት ሳይችል ተመልሷል። ክብሮም የጦርነት ዳፋ እየጠቀሰ "እናቴ ምን አደረገች? እህቴ ምን አደረገች? አባቴ ምን አደረገ? ቤተ ክርስቲያን እና መስጂዶች ምን አደረጉ?" እያለ ይጠይቃል።

ተጠያዊው ማነው?

ኢሕአዴግ ፈርሶ ብልጽግና እና ህወሓት በየፊናቸው መንገድ ሲገቡ ፍቺያቸው ቢያሰጋም እንዲህ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያመራል ብሎ የጠበቀ ከነበረ በእርግጥም ነቢይ ነበር። በዚህ ጦርነት ከ500,000 እስከ 600,000 የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን እንዳለቁ ይገመታል። ይኸ ቁጥር እንዴት እንደተሰላ ለጊዜው የሚታወቅ ባይኖርም ከጦርነቱ ብርታት፣ ከተሳታፊዎቹ ብዛት አኳያ አይሆንም ብሎ መሞገት አይቻልም። አካሉ የጎደለው፣ ንብረቱ የወደመበት፣ ለብርቱ የስነ ልቦና ቀውስ የተዳረገው የትዬለሌ ነው።

በወሎ ሐይቅ በጦርነት ከወደመ ተሽከርካሪ አጠገብ እንጀራ የተሸከሙ ሰዎች ሲያልፉ
ጥቅምት 24 ቀን 2015 ሁለት ዓመት የደፈነው ጦርነት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ያስከተለው ሰብዓዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ለመመለስ፤ የወደመውን መልሶ ለመገንባት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያሻታል። ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ሒውማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሠሯቸው ምርመራዎች ጦርነቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ዘረፋዎች መፈጸማቸውን ይፋ አድርገዋል። በተቋማቱ የምርመራ ሰነዶች ብርቱ ጥሰት ፈጽመዋል የሚል ክስ የሚቀርብባቸው ወገኖች ግን ውንጀላውን በተደጋጋሚ ያስተባብላሉ።

ጠባሳው ግን ጦርነቱ በደረሰባቸው በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ዛሬም አለ። ጦርነት ሲበረታ ቀያቸውን ጥለው የሸሹ ገበሬዎች ማሳቸው የውጊያ አውድማ ሲሆን አይተዋል። ከእነዚህ መካከል የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ሲገሰግሱ ከመርሳ ሸሽተው የነበሩት አቶ መሐመድ ሁሴን የተባሉ ገበሬ የማሽላ ማሳቸውን ተዋጊዎች "እንዳይሆን" እንዳደረጉት ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር።  "መሀሉ ላይ ጥይት እየተኮሱ ማሽላው ራሱ ጠፍቷል። እየደረሰ የነበረውን ማሽላ አወደሙት። ምርት ለመስጠት የደረሱ ብዙ ነገሮች አሉ። እነሱ ሁሉ ወደሙ።  ማሳው መሳሪያ መታኮሻ ሆነ። ተደብቆ መሳሪያ ይተኮስበታል፤ ጠቅላላ ማሽላው በመሳሪያ ከመሬት ላይ ጠፋ" እያሉ ተዋጊዎቹ በአካባቢው ከደረሱ በኋላ ደረሰ ያሉትን ጥፋት ዘርዝረዋል።

ከአቶ መሐመድ ቀዬ የምትገኘው የመርሳ ከተማ ጠባሳ ዛሬም አለ። ይኸን የጦርነት ጠባሳ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከከተማዋ ሸሽቶ የነበረው ያሲን መሐመድ በየቀኑ ያየዋል። "መስታወታቸው የተሰበሩ ሕንጻዎች፤ የፈረሱ ቤቶች አሉ" የሚለው ያሲን የተደፈሩ እንስቶች መኖራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። "አንዲት ልጅ አልደፈርም ብላ ሶስት ጊዜ ከታፋዋ ላይ መተዋት ቆስላ አሁን ድረስ እቤቷ ቁጭ ያለች ልጅ አለች።" ሲል ያሲን መሐመድ ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ በአፋር ክልል የተፈናቀሉ ሕጻናት
ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ከ200 ሺሕ በላይ ሕጻናት በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ለትልቅ ችግር መጋለጣቸውን የገለጹት የአፋር ክልል ምክትል የጤና ቢሮ ኃላፊ "ወደ 66 ሺሕ የሚሆኑ እርጉዝ እና አጥቢ እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች የደረሰባቸው ናቸው" ሲሉ አስረድተዋል። ምስል Seyoum Getu/DW

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሶስተኛ ሰለባ የሆነው የአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት በጤናው ዘርፍ ብቻ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመበት የክልሉ ምክትል የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "በአጠቃላይ በአፋር ውስጥ 44 ጤና ጣቢያ ከጥቅም ውጪ አድርገዋል። ዕቃዎቻቸው ተወስደውባቸው ምንም አይነት አገልግሎት እየሰጡ አልነበረም። ወደ 170 ጤና ኬላዎች ወደ 3 ሆስፒታሎች ናቸው ዕቃዎቻቸው ተወስደውባቸው አንዳንድ ጉዳት የደረሰባቸው" ሲሉ አቶ ያሲን ሐቢብ ተናግረዋል። ኃላፊው እንደሚሉት በውጊያው ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ያጡ፤ የቆሰሉ እና የተፈናቀሉ የክልሉ የጤና ባለሙያዎች አሉ።

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ከ200 ሺሕ በላይ ሕጻናት በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ለትልቅ ችግር መጋለጣቸውን የገለጹት የአፋር ክልል ምክትል የጤና ቢሮ ኃላፊ "ወደ 66 ሺሕ የሚሆኑ እርጉዝ እና አጥቢ እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች የደረሰባቸው ናቸው" ሲሉ አስረድተዋል። አራት ጊዜ ወደ አፋር ክልል በተዛመተው ጦርነት ሳቢያ "በአጠቃላይ ወደ 1.4 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሎ ነበር።"

አቶ ያሲን እንደሚሉት የአፋር ክልል የጤና ባለሙያዎች "ሕጻናት ሲሞቱ፤ እርጉዞች በየዛፉ ሥር ለመውለድ ሲገደዱ" አይተዋል። የጠነከረ የጤና አገልግሎት ቀድሞም ባልነበረው አፋር ጦርነቱ እንደ ጎርፍ ካሉ ሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተደማምሮ ያስከተለው ቀውስ እንዲህ በቀላሉ መፍትሔ የሚበጅለት አይደለም። ይኸ ሥጋት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የደረሰውን ለተመለከቱ ሁሉ የሚያብሰለስል ነው። የሁለት አመታቱ ተፋላሚዎች በደቡብ አፍሪካ የሰላም ሥምምነት ቢፈራረሙም ይዘቱ እና አተገባበሩ ገና በውል አለየም።  ሥምምነቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ለተፈጸመባቸው፤ አካላቸው ለጎደለ፤ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚፈይደው ካለ ወደፊት ይታያል።

እሸቴ በቀለ