1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ሕብረት በሰላም ስምምነቱ ላይ የሰጠው አስተያየት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 24 2015

የአውሮጳፓ ኅብረት ቃል አቀባይ ወይዘሪት ናቢላ ማስራሊ ለዲ ደብሊው በሰጡት ስተያየትም ኅብረቱ ስምምነቱን እንዴት እንደተቀበለው አብራርተዋል፤

https://p.dw.com/p/4J2R1
Belgien Brüssel | Flaggen vor der EU Kommission auf Halbmast nach Tod der Queen
ምስል Yves Herman/REUTERS

በሰላም ስምምነቱ የአውሮፓ ሕብረት አስተያየት

የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ባለፉት ሁለት አመታት ሲያካሂዱት የቆዩትን ደመ አፋሳሺ ጦርነት ከትናንት ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ ለማቆምና በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ በጋራ ለመሥራት ትናንት ደቡብ አፍርካ ፕሪቶሪያ ላይ ተስማማተዋል። የአፍሪካ ኅብረት የአፍርካ ቀንድ ልዩ መልክተኛና የኢትዮጵያው ግጭት ዋና አሸማጋይ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳት ኦሌሴንጎ ኦባሳንጆ ከፊርማ ስነስርአቱ በኋላ ባሰሙት ንግግር « ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖቾ ተኩስ  ለማቆማና ሰላማዊና ስርአታዊ የትጥቅ ማስፈታት ሂደትንም ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል በማለት ከስምምነት የደረሱትን ወገኖችና ለሰላም ነግግሩ መሳክት የበኩላቸውን ያደረጉትን አካላት ሁሉ አመስግነዋል። 
የሰላም ስምምነቱ ጦርነቱን አሁኑኑ በማቆም በቀጣይና ደረጃ በደረጃ የህወሀት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ የሚያደርግና ብቸኛው የአገሪቱ ሰላም አስከባሪ ኃይልም የመክላከያ ሠራዊቱ መሆኑን የሚያረጋግጥ፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሕገመንግሥቱና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት ስምምነት የተደረሰበት ሰነድ መሆኑ ተገልጿል። ሆኖም የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱ በራሱ ግብ ሊሆን እንደማይችልና ወሳኙ ነገር የተደረሰወን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ላይ መሆኑን ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ አጽናኦት ሰጥተው አሳስበዋል።   
ከሁለት ዓመት በፊት በዛሬው ዕለት የተጀመረው የፌዴራል መንግሥቱና ህዝብዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ጦርነት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ  በአውዳሚነቱና አስከፊነቱ የሚጠቀስ ነው። ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በያዟቸው የተለያዩ አቋሞችና ተጻራሪ ሀሳቦች በርካቶች የሰላም ንግግሩ መሳክቱን ይጠራጠሩ የነበር ቢሆንም፤  በዚህ ወቅት ከዚህ አጠቃላይ የሰላም ስምምነት መደረሱ ግን ብዙዎችን አስደንቋል። በርካታ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተደረሰው ስምምነት ደስታቸውን በመግለጽ፤ ሁሉም ወገኖች ስምምነቱን እንዲያከብሩና ተግባራዊም እንዲያደርጉ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ናቸው።  
የአውራፓ ኅብረት ቃል አቀባይ ወይዘሪት ናቢላ ማስራሊ ለዲ ደብሊው በሰጡት ስተያየትም ኅብረቱ ስምምነቱን እንዴት እንደተቀበለው አብራርተዋል፤  «የአውሮፓ ኅብረት የተኩስ ማቆም ስምምነቱን በደስታ ነው የተቀበለው። የኢትዮጵያን መንግሥትንና  የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅትን ለሰላም ሲሉ ለወሰዷቸው  እርምጃዎች እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እንፈልጋለን » ብለዋል። ኅብረቱ ድርድሩን የመራውን የአፍሪካ ኅብረትንና፤ ታዛቢዎችንና አስተናጋጇን ደቡብ አፍሪካንም የሚያስመስግን ሥራ መሥራታቸውንም አንስተዋል። በሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ቅድሚያ ሊስጠው ይገባል ያሉትን ሲያብራሩም፤ «ቅድሚያ የሚስጠው፤ የሰብአዊ እርዳታ በሁሉም ጦርነቱ በጎዳቸውና ባጎሳቆላቸው አካባቢዎች ማድረስና በተለይም በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር ነው» ብለዋል። 
የአውሮፓ ኅብረት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ አግዶት የነበረውን የበጀት ድጋፍ ከዚህ ስምምነት በኋላ የሚለቅ ስለመሆኑ የተጠይቁት ቃል አቀባይ ናቢላ፣ የበጀት እርዳታው የታገደው ጦርነቱ እንዲቆምና የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ያለገደብ እንዲደርስ፤ የኤርትራ ሠራዊትም ከኢትዮጵያ እንዲወጣ  በመጠየቅ እንደነበር አውስተው፤ የታገደው የበጀት እርዳታ መቼና እንዴት ሊለቀቅ እንደሚችል ግን ከመናገር ተቆጥበዋል ። 
ገበያው ንጉሤ 
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ