1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጪ መላክ ስትጀምር የባሌ ገበሬዎች በተመን ጉዳይ ቅሬታ ገብቷቸዋል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ የካቲት 8 2015

የባሌ ገበሬዎች በሕዳር እና ታኅሣስ ወራት እስከ 4,200 ብር ያወጣ የነበረው አንድ ኩንታል ስንዴ በ3,200 ብር ለመሸጥ በመገደዳቸው ቅሬታ ገብቷቸዋል። አንድ የጋሰራ ወረዳ ገበሬ "የመኪና፣ የሠራተኛ ወጪ ሲታሰብ ምንም ትርፍ የለውም። ዞሮ ዞሮ መንግሥት ያተርፍ እንደሆነ ነው እንጂ አርሶ አደር ተጎጂ ነው" ሲሉ ቅሬታቸውን አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/4NXH6
Äthiopien | Oromia | Getreidelieferung
ምስል Office of the PM of Ethiopia

ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጪ መላክ ስትጀምር የባሌ ገበሬዎች በተመን ጉዳይ ቅሬታ ገብቷቸዋል

የአጋርፋው ገበሬ አቶ አስፋው ጋረደው ያመረቱት ስንዴ በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ለውጪ ገበያ ሲዘገጃጅ እርሳቸው ግን ከቅሬታቸው አልተላቀቁም። በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ የሚኖሩት አቶ አስፋው ከማሳቸው የሚመረተው ስንዴ ለውጪ ገበያ እንደሚቀርብ ሲነገራቸው የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙ ተስፋ ነበራቸው።

"መጀመሪያ ዋጋ በውድ ነው የተነገረን" የሚሉት አቶ አስፋው "ከዚያ በኋላ ደግሞ ከዚህ በላይ እንዳይገዙ ተብሎ ተለጠፈ። [አንድ ኩንታል ስንዴ] ከ3,200 ብር በላይ እንዳትገዙ ተባለ" ሲሉ በተስፋቸው ላይ ውኃ የቸለሰውን ጉዳይ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ምርጥ ዘር በ5,000 ሺሕ ብር፤ ማዳበሪያ በ5,000 ብር መግዛታቸውን የሚያስረዱት ገበሬ 500 ብር ይሸጥ የነበረ የዋግ መድሐኒት 1,800 ብር መግባቱን እየገለጹ "እንደዚህ እየተጠቀምን ነው የከረምንው" ሲሉ ይናገራሉ። አቶ አስፋው "አንዳንድ የተቸገረ ሰው መቼም መሸጡ አይቀርም እንጂ በብዛት አልተሸጠም። ሰው እንደዚያው ይዞ ነው የተቀመጠው" ሲሉ የመንግሥት የዋጋ ተመን ያሳደረውን ተጽዕኖ ይገልጻሉ። 

በተያዘው ዓመት ከአንድ ሔክታር መሬት እስከ 40 ኩንታል ስንዴ ያመረቱት አቶ አስፋው ጋረደው ለእርሻ ሥራቸው የራሳቸው ትራክተር አላቸው። ትራክተር የሌለው ገበሬ ግን አቶ አስፋው እንደሚሉት አንድ ሔክታር መሬት ለማሳረስ በ4,500 ብር መከራየት ይጠበቅበታል። "ኮምባይነር ዘንድሮ በጣም ውድ ነው። አንድ ኩንታል [ስንዴ ለመሰብሰብ] በ150 ብር ተጀመረ። ከጋሰራ በታች ካለፈ አንድ ኩንታል 250 ብር ገባ" ሲሉ ተናግረዋል።

ወደ ውጪ የሚላክ ስንዴ ለመጫን የተዘጋጁ ከባድ ተሽከርካሪዎች
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሣምንት መገባደጃ በባሌ ዞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት መርሐ-ግብር ስንዴ ወደ ውጪ መላክ መጀመሩን ይፋ ሲያደርግ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በክልሉ በ2015 በክረምት፣ በበጋ እና በበልግ በ2.7 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ከ100 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ይመረታል የሚል ዕቅድ እንዳለ ገልጸው ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ውጪ የሚላክ መሆኑን ተናግረዋል።ምስል Office of the PM of Ethiopia

ይኸ የአቶ አስፋው ቅሬታ የብቻቸው አይደለም። በዚያው በባሌ ዞን ጋሰራ ወረዳ ገበሬ የሆኑት አቶ ቱፋ ቀጄላ በኅዳር እና ታኅሣስ ወራት እስከ 4,200 ብር የነበረው አንድ ኩንታል ስንዴ ለመንግሥት ሲሸጥ ከ5,000 እስከ 6,000 ብር ያወጣል የሚል ልብ የሚያሞቅ ዜና ከሰሙት መካከል ናቸው። አቶ ቱፋ የምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ጸረ-ተባይ መድሐኒቶች ወጪ ከትራክተር እና ኮምባይነር ኪራይ ጋር ተደማምሮ የእርሻ ሥራው በአንድ ሔክታር እስከ 37 ሺሕ ብር ገደማ እንደሚጠይቅ ይናገራሉ። አቶ ቱፋ እንደሚሉት ግን ይኸ ወጪ የሰው ጉልበትን አይጨምርም። የስንዴ ምርታቸውን ከገበያው ዋጋ በታች ለመሸጥ መገደዳቸውን ለዶይቼ ቬለ ያረጋገጡት አቶ ቱፋ የመንግሥት ተመን የገበሬውን ወጪዎች ያገናዘበ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

"ምርት የሚሰበሰበው በህብረት ሥራ ማህበራት ነው። ከማህበራቱ ውጪ ያለው የገበያ አማራጭ ተዘግቷል። ማህበራቱ ደግሞ ከ3 ሺሕ 200 ብር በላይ መግዛት አትችሉም ተብለው ታግደዋል። መንግሥት ከነሱ ሲቀበል ደግሞ በኩንታል የ161 ብር ትርፍ ያስብላቸዋል" ያሉት አቶ ቱፋ ቀጄላ "የመኪና፣ የሠራተኛ ወጪ ሲታሰብ ምንም ትርፍ የለውም። ዞሮ ዞሮ መንግሥት ያተርፍ እንደሆነ ነው እንጂ አርሶ አደር ተጎጂ ነው" ሲሉ ቅሬታቸውን አስረድተዋል።

በዚያው በባሌ ዞን ጋሰራ ወረዳ በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ አቦ አዱኛ የስንዴ ምርታቸውን በሸጡበት ተመን እና በገበያው ዋጋ መካከል በተፈጠረው ልዩነት ቅሬታ ካደረባቸው መካከል ናቸው። "መንግሥት መጀመሪያ ግንዛቤ በሰጠን መሰረት ትልቅ ተስፋ ነበር የሰነቅንው። ´በተመጣጠነ ዋጋ ነው ምርታችሁን የምንሰበስበው´ ብሎን በትልቅ ተነሳሽነት ነበር ወደ ምርት የገባነው። አሁን ግን ገበያው እንደዚያ አልሆነም። ምንም ከፍተኛ ድካም ብናወጣበትም መንግሥት ካለው ውጪ ምን ማድረግ እንችላለን? አሁን ከዚህ በፊት ለነጋዴዎች ስንሸጥ ከነበረው ገበያው እጅግ ወርዷል" ያሉት አቶ አቦ "በአሁኑ ወቅት ለቀጣይ የምርት ጊዜ የሚውል መሬት አርሰን በዝግጅት ላይ ብንሆንም እየተስተዋለው ባለው የዋጋ ተመን መውረድ ተነሳሽነታችን ወድቋል" በማለት ተጽዕኖውን አስረድተዋል።

ከባሌ ዞን ወደ ውጪ ሊላክ የተዘጋጀ ስንዴ
አቶ ግርማ  ብሩ "የአምናው ክረምት እና የዘንድሮውን የበጋ ምርት ጨምሮ አጠቃላይ የስንዴ የምርት ሚዛን በእያንዳንዱ ነፍስ ወከፍ የስንዴ የአመት ፍጆታ ተለክቶ ከእኛ ፍጆታ የሚተርፍ በጥሩ ግምት ላይ ተመስርቶ ወደ 32 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚኖር አረጋግጠን [ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ] አቅርበንላቸው ነው የስንዴ ምርቱ የኤክስፖርት ውሳኔ የተደረሰው" ሲሉ የመንግሥትን አመክንዮ አስረድተዋል።ምስል Office of the PM of Ethiopia

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሣምንት መገባደጃ በባሌ ዞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት መርሐ-ግብር ስንዴ ወደ ውጪ መላክ መጀመሩን ይፋ ሲያደርግ የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በክልሉ በ2015 በክረምት፣ በበጋ እና በበልግ በ2.7 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ከ100 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ይመረታል የሚል ዕቅድ እንዳለ ገልጸው ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ውጪ የሚላክ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት መርሐ-ግብር ንግግር ያደረጉት አቶ ጌቱ "ወደ ውጪ ለመላክ ከታቀደው 10 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር፤ በጥር ወር 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንድንገዛ ታቅዶ እስካሁን 1.21 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የተገዛ ሲሆን፤ ከተገዛው ስንዴ ውስጥ 654, 777 ኩንታል በላኪዎች መጋዘን የሚገኝ በዛሬው ዕለት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በተገኙበት ኤክስፖርት ሊደረግ ተዘጋጅቷል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ የስንዴ ፍላጎቷን ሞላች?...መንግሥት እንዲያ እያለ ነው

ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጪ መላክ መጀመሯን ይፋ ያደረገችው በጦርነት ከምትታመሰው ዩክሬን 25,000 ቶን እህል ከተረከበች ሁለት ወር ሳይሞላ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የዕርዳታ ድርጅቶች ዩክሬንን ጨምሮ ከዓለም ገበያ ሸምተው ለተረጂዎች የሚሰጡት ስንዴ ሙሉ በሙሉ ከአገር ውስጥ እንዲገዛ ዝግጅ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና የማክሮ ኤኮኖሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ብሩ እንዳሉት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ 2.9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ እንደ የዓለም የምግብ ድርጅት ለመሳሰሉ  ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለመሸጥ የሚያስችል ውል ሊፈረም ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ሱዳን እና ኬንያን ጨምሮ ለስድስት አገሮች 3 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ስንዴ ለመሸጥ በንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር በኩል ውል መገባቱን የተናገሩት አቶ ግርማ  "የአምናው ክረምት እና የዘንድሮውን የበጋ ምርት ጨምሮ አጠቃላይ የስንዴ የምርት ሚዛን በእያንዳንዱ ነፍስ ወከፍ የስንዴ የአመት ፍጆታ ተለክቶ ከእኛ ፍጆታ የሚተርፍ በጥሩ ግምት ላይ ተመስርቶ ወደ 32 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚኖር አረጋግጠን [ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ] አቅርበንላቸው ነው የስንዴ ምርቱ የኤክስፖርት ውሳኔ የተደረሰው" ሲሉ የመንግሥትን አመክንዮ አስረድተዋል።

ከዩክሬን ወደ ኢትዮጵያ ስንዴ ያጓዘች ብሬቭ ኮማንደር የተባለች መርከብ በባህር ላይ ስትንሳፈፍ ትታያለች
ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጪ መላክ መጀመሯን ይፋ ያደረገችው በጦርነት ከምትታመሰው ዩክሬን 25,000 ቶን እህል ከተረከበች ሁለት ወር ሳይሞላ ነው። ምስል Str/NurPhoto/picture alliance

ኢትዮጵያ እስካሁን በ2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ 5.52 ሚሊዮን ቶን ስንዴ እንደምታመርት የአሜሪካ ግብርና ቢሮ ባለፈው ጥቅምት 2015 ይፋ ያደረገው ሰነድ ያሳያል። ይሁንና የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ፣ ዳቦ፣ ብስኩት እና ፓስታ የመሳሰሉትን የመመገብ ባህል እያደገ ሲሔድ የአገሪቱ የማምረት አቅም እና የገበያው ፍላጎት አልተጣጣሙም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በ2015 በጀት ዓመት በ1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ይመረታል ብሎ ይጠብቃል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሳካት ብቻ ያገሪቱ ገበሬዎች 7 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ማምረት ይጠበቅባቸዋል።

ትርፍ ወይስ የውጭ ምንዛሪ ፍለጋ?

"433 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ስንዴ" በጎርጎሮሳዊው 2020/2021 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የአሜሪካ ግብርና መሥሪያ ቤት ሪፖርት እያጣቀሱ የግብርና ኤኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ጸጋዬ ይልማ ያስረዳሉ። "ከዚህ ውስጥ 175 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው በእርዳታ ከአሜሪካ የመጣ ሲሆን፤ ሌላው 257 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ስንዴ ከዓለም ገበያ የተገዛ ነው" የሚሉት ዶክተር ጸጋዬ ኢትዮጵያ 30 በመቶ የስንዴ ፍጆታዋን ዩክሬን፣ ሩሲያ እና ቱርክን ከመሳሰሉ አገሮች በእርዳታ እና በግዢ እያስገባች እንደምትሸፍን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ስንዴ በመስኖ የማምረትን ተሞክሮ ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት ከሚያደንቁ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ጸጋዬ ብርቱው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከአገር ውስጥ ገበያ ይልቅ ስንዴ ወደ ውጪ እንዲልክ ሳያስገድደው እንዳልቀረ ይገምታሉ። ዶክተር ጸጋዬ "የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጫና ሲረግብ መንግሥት አቅጣጫው ይቀየራል" የሚል ተስፋ አላቸው።

በዩክሬን የእርሻ ማሳ ስንዴ ሲሰበሰብ
ኢትዮጵያ እንደ ባሌ ካሉ የእርሻ ማሳዎች የተመረተ ስንዴ ይዛ ወደ ጎረቤት ሃገራት ገበያ ብቅ ስትል እንደ አሜሪካ እና ሩሲያ ካሉ ሥመ ጥር ስንዴ አምራቾች መወዳደር ይጠበቅባታል። ምስል Alexey Furman/Getty Images

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚክስ ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር መንግሥቱ ከተማ እንደ ዶክተር ጸጋዬ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ስንዴ ወደ ውጪ እንዲላክ ሲወስን ዋንኛ ዓላማው የውጭ ምንዛሪ እንደሆነ ይስማማሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ እንደ ባሌ ካሉ የእርሻ ማሳዎች የተመረተ ስንዴ ይዛ ወደ ጎረቤት ሃገራት ገበያ ብቅ ስትል እንደ አሜሪካ እና ሩሲያ ካሉ ሥመ ጥር ስንዴ አምራቾች መወዳደር ይጠበቅባታል።

"ስንዴን ኤክስፖርት ከሚያደርጉ እንደ ሩሲያ፣ ዩክሬን እና አሜሪካ ያሉ ታላላቅ ሃገራት ጋር ተወዳዳሪ ሆና እነሱ አንድ ኩንታል በሚሸጡበት ከ34 እስከ 37 ዶላር አካባቢ ዋጋ እኛም መሸጥ የምንችል አይመስለኝም" የሚሉት ፕሮፌሰር መንግሥቱ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ፣ ማሽኖች እና ነዳጅን ጨምሮ ግብርናው የሚያስፈልገውን ግብዓት በዶላር ስትሸምት "እነዚህ የማምረቺያ ወጪን ከፍ ስለሚያደርጉት አትራፊ ሆነን ወደ ውጪ እንልካለን የሚል እምነት የለኝም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

"አሁን ወደ ውጪ ሲላክ በዚህ ዋጋ ነው የመሸጥ ያለባችሁ ተብሎ ተመን ወጥቶለት፤ ከገበሬው ተሰብስቦ ነው። ገበሬው ይደብቃል። እነሱ ደግሞ ተከታትለው መሸጥ አለባችሁ እያሉ ሰብስበው ነው ወደ ውጪ ለመላክ ያዘጋጁት። ይኸ የሚያሳየው ወደ ውጪ መላክ እና የውጭ ምንዛሪ ማግኘትን ዓላማ ያደረገ ሆኖ እንጂ አትራፊ ሆኖ አይደለም" የሚሉት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚክስ ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደ ባሌ እና አርሲ ባሉ አካባቢዎች ሕገ ወጥ የስንዴ ግብይት መታየቱን ይጠቅሳሉ። "የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አገሪቷ ስንዴ ወደ ውጪ ልትልክ ትችላለች" የሚሉት ፕሮፌሰር መንግሥቱ "ነገር ግን አትራፊ ሆና ወደፊትም በዘላቂነት የስንዴ ላኪ አገር ለመሆን ዕድሉ ያላት አይመስለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።

ሥዩም ጌቱ 

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ