1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢሰመኮ በአደዋ በዓል ሰው የገደሉ እንዲጠየቁ አሳሰበ

ዓርብ፣ የካቲት 24 2015

ትናንት አዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ ላይ በተከበረው 127ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ የጸጥታ ኃይሎች በፈጸሙት ከልክ ያለፈ የኃይል አጠቃቀም አንድ ሰው መገደሉንና ሌሎች የበዓሉ ታዳሚዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ ።

https://p.dw.com/p/4OE5C
Äthiopien Addis Abeba Adwa Sieg
ምስል Solomon Muche/DW

የአደዋ ድል በዓልን የማጠልሸት እንቅስቃሴ ጎልቷል

ትናንት አዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ ላይ በተከበረው 127ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ የጸጥታ ኃይሎች በፈጸሙት ከልክ ያለፈ የኃይል አጠቃቀም አንድ ሰው መገደሉንና ሌሎች የበዓሉ ታዳሚዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ ። ከልክ ያለፈ ድርጊት ፈጽመዋል ያላቸው የጸጥታ ኃይሎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የጠየቀው ኢሰመኮ በክብረ በዓላት አከባበር ላይ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ የሕግ አስከባሪዎች አስፈላጊ ሥልጠና እንዲያገኙ ሊደረግ ይገባልም ብሏል ።

በበዓሉ አከባበር ወቅት አንድ አባሉ እንደተገደለበት የገለፀው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) «በመንግስት ደረጃ መዋቅራዊና ሥርአታዊ በሆነ መልኩ ታሪክ ለመበረዝ የተሄደበትን ርቀት ተመልከተናል» ሲል ወቅሷል ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፦ መሰል «አገራዊ ክብረ በዓላትን ለማስተጓጎል የሚጥሩ አካላት እንደነበሩ የጸጥታ አካላት አስቀድሞ መረጃ ነበራቸው» በማለት  የጸጥታ አካላት ታዳሚዎች ለጉዳት እንዳይዳረጉ ጥረት ሲያደርጉ መዋላቸውን ገልጿል ። «ጥቂት ምዕመናን ላይ ጉዳት ደርሷል» በማለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ። 

ትናንት በተከበረው 127 ኛው የአድዋ ድል ክብረ በዓልላይ በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች ወደ ምኒልክ አደባባይ እንዳይሄዱ ክልከላ ሲደረግባቸው ነበር። ጥብቅ የነበረውን ፍተሻ አልፈው የገቡትም በርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ የአበባ ጉንጉን ከተቀመጠ በኋላ የተፈጠረው ውጥረት አይሎ ፖሊሶች በታዳሚዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል፣ የጭስ ቦንብም በመተኮስ ሰውን በትነዋል ።

ኅብረተሰቡየአደዋ ድልን ለማክበር በምንሊክ አደባባይ ተሰባስቦ
ኅብረተሰቡየአደዋ ድልን ለማክበር በምንሊክ አደባባይ ተሰባስቦምስል Solomon Muche/DW

አዲሱ ኃይሌ የተባለ ሰው ደግሞ በዓሉን ለማክበር አብሮት የወጣው የአክስቱ ልጅ በጥይት ተመትቶ መገደሉን ገልጿል። የሟቹን አስክሬን ወደ ትውልድ ስፍራው እየወሰዱ መሆኑንም ለ ዶቼ ቬለ አረጋግጧል ።

እድሜያቸው 52 ዓመት መሆኑን የነገሩን አንድ እናት ደግሞ በተፈጠረው ችግር እጅ እና እግራቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ "የጸጥታ ኃይሎች በዓሉን ለማክበር በወጣው ሕዝብ ላይ ከልክ ያለፈ አላስፈላጊ ድብደባ፣ አስለቃሽ ጭስ፣ ጥይትና ሌሎች ከመጠን ያለፉ እምጃዎችን መውሰዳቸውን" ገልፀው በተወሰደው እርምጃ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችና ሕፃናት ጭምር መጎዳታቸውን ተናግረዋል። በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ 13 የፀጥታ ኃይሎች ባለፉት ስድስት ወራት የወንጀልን ጨምሮ  ሌሎች ተጠያቂነቶች እንዲደርስባቸው መደረጉን ገልፀው አሁንም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን ) «በመንግሥት ደረጃ መዋቅራዊና ሥርአታዊ በሆነ መልኩ ታሪክ ለመበረዝ ጥረት መደረጉን» ገልጾ «መንግሥት የፈፀመውን ሕገ - ወጥ ድርጊት በማመን ሕዝብን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ» እና እንዳይደገም ጠይቋል።

ርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴና ባለሥልጣናት በምንሊክ አደባባይ
ርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴና ባለሥልጣናት በምንሊክ አደባባይምስል Solomon Muche/DW

መሰል "አገራዊ ክብረ በዓላትን ለማስተጓጎል የሚጥሩ አካላት እንደነበሩ የጸጥታ አካላት አስቀድሞ መረጃ ነበራቸው" ያለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ የጸጥታ አካላት ታዳሚዎች ለጉዳት እንዳይዳረጉ ጥረት ሲያደርጉ መዋላቸውን ሆኖም «ጥቂት ምዕመናን ላይ ጉዳት ደርሷል» በማለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በሌላ በኩል ትናንት ረፋድ ላይ ፒያሳ በሚገኝ የሥራ ቦታው ላይ የነበረ አንድ ጋዜጠኛ በፖሊስ ከቢሮው ተይዞ መወሰዱንና እስካሁን የት እንዳላ እንደማይታወቅ አንድ ግለሰቡ ሲወሰድ የተመለከተች ሴት ገልፃለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአድዋ ድል ክብረ በዓልላይ ልዩነትች እየተስተዋሉ መሆኑ በጉልህ መታየት ጀምሯል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ