1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሸገር ከተማ ቤቶች መፍረስ እና የኢሰመኮ መግለጫ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 23 2015

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በተዋቀረው ሸገር ከተማ ውስጥ "እየተካሄደ ያለው ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳት እርምጃ" የመኖሪያ ቤት አልባነትን ከማባባሱ ባለፈ በርካታ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ቀውስ መዳረጉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4PafO
Äthiopien l Gebäude Ethiopian Human Rights Commission( EHRC)
ምስል Solomon Muchie/DW

በሸገር ከተማ ቤቶች አላግባብ መፍረስ ላይ የኢሰመኮ መግለጫ

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በተዋቀረው ሸገር ከተማ ውስጥ "እየተካሄደ ያለው ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳት እርምጃ" የመኖሪያ ቤት አልባነትን ከማባባሱ ባለፈ በርካታ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ቀውስ መዳረጉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደር እየወሰደ ያለው ቤት የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳት እርምጃ "ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት ፣ ያለ በቂ የቅድመ ማስጠንቀቂያ የተከናወነ እና አድሎዓዊ እርምጃ ነው" ያለው ኢሰመኮ ድርጊቱን ተከትሎ እሥር ፣ የአካል እና የሥና ልቦና ጉዳት እንዲሁም እንግልት መድረሱንም ገልጿል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችን ማነጋገሩን ያስታወቀው መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ኢሰመኮ ባለሥልጣናቱ "ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸውን” ግንባታዎች በማፍረስ ላይ እንደሚገኙ እንደገለፁለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች ምን ያህል እንደሆኑ ያልጠቀሰው ኢሰመኮ እንዚህ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ እና ካሳ በአፋጣኝ እንዲመቻችላቸውም ጠይቋል።የቤቶች ፈረሳና እርምጃዉ ያስከተለዉ ጣጣ

"ሕገ ወጥ ግንባታን የማፍረስ እርምጃ ሕጋዊ ሂደትን መከተልና እርምጃው ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊ ቀውስ ከግንዛቤ በማስገባት አማራጭ መፍትሔዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል" ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች በየአካባቢው ከሚገኙ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውኃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ መሆናቸውን፣ ለተለያዩ የአካባቢው የልማት ሥራዎች እንደ ማንኛውም ማኅበረሰብ ክፍያዎችን ሲከፍሉ መቆየታቸውን በመጥቀስ መኖሪያ ቤቶቻቸው ከሕግ አግባብ ውጭ እንደፈረሱባቸው እንደገለፁለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ " የፍርድ ቤት ማገጃ የወጣባቸው ቤቶች" ጭምር መፍረሳቸውን ተናግረዋል።
ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የሸገር ከተማ የሥራ ኃላፊዎች የከተማ አስተዳደሩ እንደ አዲስ መመሥረቱን ተከትሎ “ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸውን” ግንባታዎች በማፍረስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸውልኛል ብሏል። ሆኖም እርምጃው ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት ፣ ያለ በቂ የቅድመ ማስጠንቀቂያ የተከናወነ እና አድሎዓዊ እርምጃ ከመሆኑም በላይ ለአንድ ሰው መሞት ምክንያት መሆኑንም አስታውቋል።ልማትና የቤቶች መፍረስ
ኢሰመኮ "እርምጃው በርካታ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ቀውስ ዳርጓል፤ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ለማቋረጥ ተገደዋል፤ በርካታ ቤተሰቦች የእለት ተእለት ተግባራቸውን ማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል" ብሏል። እስካሁን ከ 2 ሺህ በላይ ሰዎች ለኮሚሽኑ አቤቱታ ማቅረባቸውንም ዶክተር ብራይትማን ለ ዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነው ኢሰመኮ በዚህ ቤት የማፍረስ ድርጊት ተጎጂ የሆኑ ሰዎች "በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት እድል እንዲዘጋጅ እና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ካሳ በአፋጣኝ ሊመቻችላቸው ይገባል ብሏል፡፡

Äthiopien Addis Abeba | Behördliche Zerstörtung von alten Häusern
ምስል Seyoum Getu/DW

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ