1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ማዳበሪያ በወቅቱ ያልደረሳቸው ገበሬዎች እርሻ እንዳይስተጓጎል ሰግተዋል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ግንቦት 30 2015

ክረምት ሲቃረብ የአፈር ማዳበሪያ ያልደረሳቸው ገበሬዎች ሥጋት ውስጥ ወድቀዋል። አቅሙ ያላቸው በውድ ከነጋዴዎች ለመግዛት መገደዳቸውን ይናገራሉ። ከአቅርቦቱ ባሻገር በየጊዜው የሚንረው የማዳበሪያ ዋጋ ሌላ ፈተና ነው። መንግሥት ከገዛው 12.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ 5.67 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል

https://p.dw.com/p/4SJee
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ማዳበሪያ በወቅቱን ያልደረሳቸው ገበሬዎች እርሻ እንዳይስተጓጎል ሰግተዋል

የጎጃሙ ገበሬ አቶ አስማማው ሉሌ ድንች የሚዘሩበት ጊዜ በማለፉ ይቆጫቸዋል።በቀያቸው ደቡብ አቸፈር ድንች የሚዘራው በመጋቢት እና ሚያዝያ ወራት እንደሆነ የሚናገሩት ገበሬ በወቅቱ ዘር እና ማሳ አዘጋጅተው የቀረው የአፈር ማዳበሪያ ብቻ ነበር። "ማዳበሪያ ዋጋው እንደቀነሰ፤ ግብዓቱም እንደለገሰ አድርገው አሳነፉት እና ገበሬው ምንም ነገር ሳያገኝ ዘር አምጥተው ሸጡልን" የሚሉት አቶ አስማማው ማዳበሪያ በመጥፋቱ ድንች ሳይዘሩ ወቅቱ እንዳለፈ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። 

የአቸፈሩ ገበሬ አራት ሔክታር ገደማ በሚሰፋ መሬታቸው ከድንች እና በቆሎ በተጨማሪ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ ገብስ ያመርታሉ። የአቶ አስማማው ማሳ በቆሎ ሲዘራ አምስት ኪሎ ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ ይፈልጋል። የበቆሎው ማሳ በሐምሌ ወር ገደማ ተጨማሪ አምስት ኪሎ ዩሪያ ማዳበሪያ ይሻል። "ነገር ግን ሁለቱም የለም። እንዴት እንዝራው? ተማምነንም መዝራት አይቻልም። የተሰጠን ነገር የለም" ሲሉ አቶ አስማማው በገበሬ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል የሚሰራጨው ማዳበሪያ እንዳልደረሰ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ አስማማው ማዳበሪያ በወቅቱ ማግኘት ካለመቻላቸው ባሻገር በየጊዜው የሚጨምረው ዋጋ ሌላ ፈተና ሆኖባቸዋል። "አንድ ሺሕ ብር ያለው ሰው፤ ሁለት ሺሕ ብር ያለው ሰው ሙሉ ማሳ ይዘራ ነበር። እየተወደደ ሲመጣ 20 ሺሕ ብር ገባ። ከ20 ሺሕ ብር ደግሞ 48 ሺሕ ብር ደረሰ" ሲሉ የዋጋ ጭማሪውን አስረድተዋል።

ደቡብ ክልል ገበሬዎች በእርሻ ሥራ ላይ
ገበሬዎች የአፈር ማዳበሪያ ወቅቱን ጠብቆ ስላልደረሳቸው የመዝሪያ ወቅት እንዳያልፍ ሰግተዋል። የግብርና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ግን ችግሩ የሥርጭት እንደሆነ ገልጸዋል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ባለፈው ሣምንት የይልማ እና ዴንሳ ወረዳ ገበሬዎች በባሕር ዳር ከተማ ጅራፋቸውን እያጮሁ "ማዳበሪያ ይሰጠን" የሚል አቤቱታቸውን አሰምተዋል። አቶ አስማማው "ወደ ክልል አመልክተናል፤ ወደ ዞን አመልክተናል። ነገ እያሉ ተስፋ ነው የሚሰጡን። ማመልከት ከጀመርን ሁለት ሣምንት አልፏል። ግን አንድም ውጤት የላቸውም" ሲሉ መፍትሔ እንዳጡ አስረድተዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ችግር ግን በአማራ ክልል ብቻ የተወሰነ አይደለም። በደቡብ ክልል ሐላባ ዞን  ዌራ ወረዳ ገደባ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ አብዱላሒ ተማም ለመኸር የሚያስፈልጋቸውን በቂ ማዳበሪያ አላገኙም። የአፈር ማዳበሪያ "በከፊል አግኝቻለሁ። በቂ የሚባል አይደለም። ከምፈልገው ሩብም አይደለም ያገኘሁት። በግል ከነጋዴ ገዝቼ፤ ከወረዳም ወስጃለሁ። ግን ገበሬው ችግር ላይ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የማዳበሪያ ጉዳይ አቶ አብዱላሒ የሚኖሩበትን የደቡብ ክልል መደበኛ በጀት እስከ መፈታተን የደረሰ ነው። የክልሉ መንግሥት ከ2006 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብዓቶች ለገበሬዎች ሲያቀርብ ለ4.5 ቢሊዮን ብር ዕዳ ተዳርጓል። የክልሉ መንግሥት የማዳበሪያ ሽያጭ እጅ በእጅ እንዲከናወን ውሳኔ ቢያስተላልፍም የተጠራቀመው ዕዳ ግን እንደ ሐላባ ዞን ባሉ አካባቢዎች የሠራተኞች ደመወዝ ክፍያን እስከማስተጓጎል ደርሷል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ የአቶ አሕመድ ሽዴ ከአንድ ወር ገደማ በፊት "አንዳንድ ክልሎች የተደለደለላቸውን በጀት ቀድሞ በነበረው የማዳበሪያ ዕዳ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ስለማይተላለፍላቸው የሠራተኛ ደመወዝ እንኳን መክፈል" እንዳልቻሉ ተናግረው ነበር። ችግሩ በጠናበት በደቡብ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከመጨመሩም ባሻገር አቅርቦቱ ያላረካቸው ገበሬዎች የነጋዴዎችን መደብሮች ለማማተር ተገደዋል።

አቶ አብዱላሒ "በየዓመቱ ዋጋው ይገለባበጣል። አሁንም ሁለት አይነት ነው። ከነጋዴ የምገዛው ወደ አምስት ሺሕ ብር አካባቢ ነው። ከግብርና ራሳቸው የሚያከፋፍሉት ሶስት ሺሕ ሰባት መቶ ብር አካባቢ ነው። አምና በበልግ ሁለት ቀረጢት መቶ ኪሎ ግራም ማዳበሪያ አንድ ሺሕ ስምንት መቶ ብር ነበር የገዛሁት" ሲሉ አስረድተዋል።

Äthiopien Adama | Welt ohne Hunger | Traditionelle Weizenernte
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል የማዳበሪያ ጥያቄ እንደሚቀርብ ተናግረዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት የአገሪቱ አማካኝ አመታዊ ፍጆታ ግን 15 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ነው። ምስል Stefan Trappe/Imago Images

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ባለፈው ሣምንት እንደተናገሩት የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት "ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ" ነው። ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፊት የመሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት ሲያቀርቡ በየዓመቱ ጥቅም ላይ የሚውለው ማዳበሪያ በአማካኝ 15 ሚሊዮን ኩንታል እንደሆነ ገልጸዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የገዛውን 12.8 ሚሊዮን ኩንታል እና ካለፈው አመት የተረፈውን 2.2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በ2015/2016 የምርት ዘመን ለማሰራጨት አቅዷል።

ዶክተር ግርማ ማዳበሪያውን ለመግዛት አንድ ቢሊዮን ዶላር ከመንግሥት መጠየቁን ተናግረዋል። የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) "ከተገዛው 12.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ 6.2 ሚሊዮን ኩንታል ጅቡቲ ወደብ ደርሷል። ከዚህ 6.2 ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ 5.67 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል" ሲሉ ተናግረዋል።

ዶክተር ሶፊያ ተገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ የገባውን እና ካለፈው ዓመት የተረፈውን ጨምሮ 7.8 ሚሊዮን ኩንታል መቅረቡን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል። በሚኒስትር ደኤታዋ ማብራሪያ መሠረት ከፍተኛ የማዳበሪያ ፍጆታ ያላቸው የኦሮሚያ ክልል 1.1 ሚሊዮን ኩንታል፤ የአማራ ክልል 389 ሺሕ ኩንታል ካለፈው ዓመት የተረፈ ነበራቸው። አዲስ ከተገዛው ማዳበሪያ የኦሮሚያ ክልል 3 ሚሊዮን ኩንታል፤ የአማራ ክልል 1.7 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷቸዋል።

"7.1 ሚሊዮን ኩንታል ወደ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበር ተጓጉዟል። መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር አርሶ አደሩ የሚገዛበት ቦታ ማለት ነው" ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ ለገበሬ የተሠራጨው ግን "3.7 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ" እንደሆነ ተናግረው ነበር። የቀረው 4.1 ሚሊዮን ኩንታል በማዕከላዊ መጋዘን እና በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት መጋዘን ውስጥ ይገኛል።

አድአ ወረዳ ገበሬ
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን "ችግር አለ" ሲባል በተደረገ ድንገተኛ ክትትል 700 ሺሕ ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ ተከማችቶ መገኘቱን ዶክተር ሶፊያ ለቋሚ ኮሜቴው አስረድተዋል።ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu

በሚኒስትር ድኤታዋ ማብራሪያ መሠረት በኦሮሚያ ክልል 2.4 ሚሊዮን ኩንታል፤ በአማራ ክልል 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሮች አልተሰራጨም። በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን "ችግር አለ" ሲባል በተደረገ ድንገተኛ ክትትል 700 ሺሕ ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ ተከማችቶ መገኘቱን ዶክተር ሶፊያ ለቋሚ ኮሜቴው አስረድተዋል።

"ሀገር በሌላት የውጭ ምንዛሪ ማዳበሪያ ተገዝቶ ሲመጣ የእኛ የመጨረሻ ዓላማችን በመጋዘን ውስጥ ማስቀመጥ አይደለም። አንድ ኩንታልም ይሁን ሁለት ኩንታል በየደረጃው ያለው አመራር ተረባርቦ ማድረስ አለበት" ሲሉ ዶክተር ሶፊያ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ገበሬዎች በየአካባቢያቸው የአፈር ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ በውድ ዋጋ እየተሸጠ እንደሚገኝ ይገልጻሉ። ይኸ የማዳበሪያ ሕገ-ወጥ ግብይት ጉዳይ ግንቦት 17 ቀን 2015 የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይም ተነስቷል።

"ማዳበሪያን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት አጓጉዞ ሲያመጣ ለማዕከላዊ መጋዘን ነው የሚያስረክበው። ለህብረት ሥራ ማኅበር ማለት ነው። አንድም ኩንታል ማዳበሪያ ለግለሰብ አይሰጥም። መቶ ፐርሰንት ሕገ ወጥ ንግድ የለም ብዬ ማረጋገጥ አልችልም። ኃላፊነት የማይሰማቸው የማዕከላዊ መጋዘን እና የመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኃላፊዎች ከሕገ ወጦች ጋር በመመሳጠር የተወሰነ ማዳበሪያ ሊወጣ ይችል ይሆናል" ያሉት ዶክተር ሶፊያ  ባለፈው ዓመት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች "በርካታ የሥራ ኃላፊዎች እስር ቤት እንዲገቡ" መደረጉን አስረድተዋል።

Deutschland Äthiopien Steinterassen gegen Bodenerosion in Nord-Äthiopien
የኢትዮጵያ መንግሥት ለገበሬው የሚቀርበውን ማዳበሪያ "በ2022 ወደ 32.9 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ በዕቅድ" አለው።ምስል GIZ/Thomas Imo

ኢትዮጵያ የራሷ የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎች ለመገንባት የነበራት ዕቅድ በመክሸፉ በመጪዎቹ ዓመታትም ከዓለም ገበያ መሸመቷ አይቀርም። መንግሥት ለገበሬው የሚቀርበውን ማዳበሪያ "በ2022 ወደ 32.9 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ በዕቅድ" አለው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረው ውይይት ላይ ማዳበሪያ ለመግዛት "በየዓመቱ ጨረታ የምናወጣው ለምንድነው? ለምንድነው በማዕቀፍ ግዢ የማናደርገው? የሚቀጥለውን ዓመት ማዳበሪያ ለምን በታህሳስ እንጭናለን? ለምን በሐምሌ አንጭንም? ለምን ነሐሴ አንጭንም?" ሲሉ የጠየቁት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ መንግሥታቸው ማዳበሪያ በጨረታ መግዛት ሊያቆም እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ በመጪዎቹ ሣምንታት ለማቅረብ ቃል ቢገቡም ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ገበሬዎች በወቅቱ ለመድረሱ አሁንም ሥጋት አላቸው። ማዳበሪያ በወቅቱ ካልደረሰ ገበሬዎቹ እምብዛም ተፈላጊ ወዳልሆኑ ምርቶች ፊታቸውን ሊያዞሩ ይችላሉ። የአቸፈሩ አቶ አስማማው ግን ከምርት እጥረት ሊከሰት የሚችል "የረሐብ እልቂት" ያሰጋቸዋል። ሥጋታቸው ከፍ ያለ ነው። "የበቆሎ ጊዜ ሊያልፍ እኮ ነው። የጤፍ ጊዜ ደግሞ እስከ ሰኔ 15 ነው የሚዘራው። መቼ መጥቶ ነው የሚዘራው?" ሲሉ የሚጠይቁት ገበሬ "ከዚህ በኋላ ተስፋም እንደሌለን ነው ያየንው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ