1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ኢትዮጵያ የሁለቱ ክልሎች ምሥረታ

ዓርብ፣ ነሐሴ 12 2015

ከደቡብ ክልል የተነጠሉት ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት የሚያስችላቸውን መሥራች ጉባዔውን ማካሄድ ጀመሩ። ጉባዔው ዞኖቹና ልዩ ወረዳዎቹ 12ኛ ክልል በመሆን ፌዴሬሽኑን በይፋ መቀላቀላቸውን የሚያውጁበት የመጨረሻ ምዕራፍ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4VKk1
ፎቶ ፡ ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን የተወሰደ
ከደቡብ ክልል የተነጠሉት ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት የሚያስችላቸውን መሥራች ጉባዔውን ማካሄድ ጀመሩ። ፎቶ ፡ ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን የተወሰደምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሁለቱ ክልሎች ምሥረታ

 

ከደቡብ ክልል የተነጠሉት ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት የሚያስችላቸውን መሥራች ጉባዔውን እያካሄዱ ነው። ጉባዔው ዞኖቹና ልዩ ወረዳዎቹ 12ኛ ክልል በመሆን ፌዴሬሽኑን በይፋ መቀላቀላቸውን የሚያውጁበት የመጨረሻ ምዕራፍ ነው ተብሏል።

የክልሎቹ አደረጃጀት

አዲስ የሚዋቀሩት ሁለቱ ክልሎች መሥራች ጉባዔያቸውን በመካሄድ ላይ የሚገኙት «የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል» በአርባምንጭ፤ «የማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል» ደግሞ በወልቂጤ ከተሞች ነው። የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የጌዴኦ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የኮንሶ ዞኖችና የደራሼ፣ የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የኧሌና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎችን ያካተተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዚህ ጉባኤ የፌዴሬሽኑ 12ኛ ክልል መሆኑን በይፋ ምሥታውን ያውጃል ተብሎ ይጠበቃል። በአንፃሩ የጉራጌ ፣ የሥልጤ ፣ የከምባታ ጠንባሮ ፣ የሃድያ ፣ የሀላባ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳን ያካተተውና ከነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች የማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚል ራሱን መልሶ በማደራጀት የሚቀጥል ይሆናል ነው የተባለው።

ፎቶ ፡ ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን የተወሰደ
በአርባ ምንጭ እና በወልቂጤ ከተሞች የሚካሄዱት ሁለቱም ጉባዔዎች በዛሬው ውሏቸው በቀረቡ የረቂቅ ሕገ መንግሥቸው ላይ በመምከር በአብላጫ ድምፅ አጽድቀዋል። ፎቶ ፡ ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን የተወሰደምስል Southern Region Government communication

መሥራች ጉባዔዎቹ

አዲስ የሚዋቀሩት ክልሎች ዛሬ ጠዋት በጀመሩት መሥራች ጉባዔያቸው እስከአሁን በረቂቅ ሕገ መንግሥቸው ላይ በመምከር በአብላጫ ድምፅ አጽድቀዋል። በተለይ በሁለቱም ጉባዔዎች ቀርበው የጸደቁት ሕገ መንግሥቶች ከባለፈው የደቡብ ክልል ሕገ መንግሥት ደካማና ጠንካራ ጎኖች በመነሳት በክልሎች የሚገኙ ሕዝቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ መዘጋጀታቸውን ነው በክልል አደረጃጀት ማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የረቂቅ ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎች ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ዎላይቴ  ቤቴ ለጋዜጠኞች የተናገሩት። ጉባኤዎቹ በቀጣይ የክልሉ አስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅ፣ የክልሉ ምክር ቤት እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆች ላይ  ተወያይተው ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የየጉባዔዎቹ መረሃ ግብር ያመለክታል።

ቅሬታዎች  

የክልሎቹን ምሥረታ ጉባዔ በተመለከተ ዶቼ ቬለ DW አስተያያታቸውን የጠየቃቸው የፖለቲካ ተንታኝና የቀድሞው የተወካዮች ምክር አባል አቶ ደያሞ ዳሌ «ምሥረታው ጥድፊያ የበዛበት፤ ከተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተነሱ ቅሬታዎችን ለማየት ጊዜ ያልሠጠ ነው» ይላሉ፡፡ ለአብነት በጉራጌበተናጠል የመደራጀት ፍላጎት፣ በከምባታ ጠምባሮ የአስፈጻሚ ተቋማት ድልድል ኢ ፍትሃዊ ነው የሚል አቤቱታ፣ እንዲሁም የልዩ ወረዳዎች ወደ ዞን መዋቅር ከፍ የማለት ከቅሬታዎቹ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዳያሞ «እነኝህ ጥያቄዎች ከወዲሁ ምላሽ ካላገኙ ወደፊት በአዳዲሶች ክልል ዕዳ ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለኝ» ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ