1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኪራሙ ወረዳ ሰዎች ተገደሉ፣ ከብቶች ተዘረፉ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2015

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ታጣቂዎች ከትናንት በስቲያ ባደረሱት ጥቃት 6 ሰዎች ገደሉ፤ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል። የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንዳሉት ታጣቂዎቹ በሁለት ቀበሌዎች ላይ ዘምተዉ ሰዉ ከመግደልና ንብረት ከማጥፋታቸዉ በተጨማሪ የቁም እንስሳትንም ዘርፈዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4VSYn
ኪረሙ ከተማ
ኪረሙ ከተማ ምስል Privat

«ታጣቂዎቹ በሁለት ቀበሌዎች ላይ ዘምተዉ ሰዎች ገድለዋል፤ ንብረት አዉድመዋል፤እንስሳትን ዘርፈዋል»

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ታጣቂዎች ከትናንት በስቲያ ባደረሱት ጥቃት 6 ሰዎች ገደሉ፤ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል ። የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንዳሉት ታጣቂዎቹ በሁለት ቀበሌዎች ላይ ዘምተዉ ሰዉ ከመግደልና ንብረት ከማጥፋታቸዉ በተጨማሪ የቁም እንስሳትንም ዘርፈዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር በበኩሉ በሁለቱ ቀበሌዎች ውስጥ በደረሰው ጥቃት የሰው ሕይወት ማለፉን አረጋግጧል፡ በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ  እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ የተባለ ወረዳ ውስጥ በተለያዩ ጊዜ ለሚደርሱ ጥቃቶች ነዋሪው በፋኖ እና በሼነ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደርጋል። 

ፎቶ ማህደር፤ ምዕራብ ወለጋ
ፎቶ ማህደር፤ ምዕራብ ወለጋ ምስል Negassa Dessalegen/DW

ከትናንት በስቲያ በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ጨፈ ጉድና ኖሌ  እና ባደሳ በተባሉ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ታጣቂዎች ጥቃት ማድረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ጫፈ ጉድና በተባለ ስፍራ አንድ ወንድማቸው በደረሰው ጥቃት የመቁሰል አደጋ እንደ ደረሰበት የነገሩን አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የኪረሙ ወረዳ ነዋሪ በጥቃቱ 5 ሰዎች በአንድ ቦታ መደገላቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ አንዱ በደሳ በተባለ ቦታ ነው ዳዊት  የተባለ አንድ ወጣት ነው የገደሉት፡፡ ለላ አንድ ነዋሪ ደግሞ ቆስሎ ሆስፒታል ነው ያለው፡፡ በተመሳሳይ ኖሌ በተባለች ወደ ሀሮ ቀበሌ በቅርብ ርቀት ላይ የሚትገኝ ቦታ ላይ 5 ወጣቶችን ነው የገደሉት፡፡ ታጣቂዎቹ በብዛት ከአማራ ክልል ነው እየሸሹ ወደ እዚህ እየተሻገሩ ያሉት‹‹ ብሏል፡፡

ሌላው የኪረሙ ወረዳ ነዋሪ በተመሳሳይ እንደነገሩንም በጥቃቱ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱን ያደረሱት በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በኪረሙ ሀሮ የተባለ ቦታ ከፍተኛ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እንደሚታይም አክለዋል፡፡

ፎቶ ማህደር፤ ወለጋ ዩንቨርስቲ ለተፈናቃዮች እርዳታ
ፎቶ ማህደር፤ ወለጋ ዩንቨርስቲ ለተፈናቃዮች እርዳታ ምስል Dr. Hasen

የኪረሙ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት በወረዳው ሁለት ቀበሌ ውስጥ ሰሞኑን ከአማራ ክልል የተሻገሩ የታጠቁ ሀይሎች ጉዳት ማድረሳቸውን አመልክተዋል፡፡ የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጅረኛ ሂርጳ በሁለት ቀበሌ ውስጥ ታጣቂዎቹ 6 ሰዎች መግደላቸውን አረጋግጠዋል፡፡

‹‹ ጨፈ ጉድና ኖሌ በተባለ ልዩ ቦታ የፋኖ ሀይሎች አምስት ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል፡፡ ከተገደሉት መካከል 2ቱ ሴቶች ሲሆኑ  3ቱ ወንዶች ናቸው፡፡ በአንድ ስፍራ አሰቃቂ በሆነ መልኩ ገድለዋል፡፡ በተመሳሳይ ዕለት እሁድ 5 ሰዓት ገደማ ባደሳ ቀበሌ ውስጥ ዳዊት ዋቅጅራ የተባለ ነዋሪ ችግኝ እየተንከባከበ ባለበት ሰዓት ገድለውታል፡፡‹‹

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ 10 ከሚደርሱት ቀበሌዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ነዋሪው ተፈናቅሎ እንደሚገኝ የወረዳው ኮሙኒኬሽን ገልጸዋል፡፡ በወረዳው 52ሺ በ8 መቶ 22 ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙም ከጽ/ቤቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በኪረሙ ጸጥታ ሁኔታ ላይ ከምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረኩት ጥረት ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ