1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ከኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ ገዢዎች ጋር በሚቀጥለው ሣምንት ውይይት ሊደረግ ነው

Eshete Bekele
ዓርብ፣ ኅዳር 14 2016

በኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ አከፋፈል ላይ በሚቀጥለው ሣምንት ከገዢዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ለዶይቼ ቬለ ገለጹ። ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ የጀመረችው ድርድር በጎርጎሮሳዊው 2024 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ሚኒስትር ዴኤታው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/4ZQX9

በኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዩሮ ቦንድ አከፋፈል ላይ በሚቀጥለው ሣምንት ከገዢዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ለዶይቼ ቬለ ገለጹ። ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ የጀመረችው ድርድር በጎርጎሮሳዊው 2024 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ሚኒስትር ዴኤታው ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረበው በሐምሌ 2013 ነው። እጅጉን የተጓተተው ድርድር “አሁን ጥሩ እየሔደ ነው” ያሉት ዶክተር ኢዮብ በጎርጎሮሳዊው 2024 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ይጠናቀል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ይኸ ሒደት እስኪጠናቀቅ ድረስ ኢትዮጵያ በብድር ክፍያ “ጊዜያዊ እፎይታ” እንድታገኝ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ጭምር በሚሳተፉበት በዕዳ ላይ የሚመክር መድረክ (Global Sovereign Debt Roundtable) መወሰኑን ዶክተር ኢዮብ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ “ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ” ከአበዳሪ የፋይናንስ ተቋማቷ ድርድር እንዲደረግ የወሰነችው ቻይናን ጨምሮ “ሌሎቹም አበዳሪ ሀገራት የሁለት ዓመት ጊዜያዊ እፎይታ ይሰጣሉ” ያሉት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ውሳኔው የዩሮ ቦንድ አበዳሪዎችን ጭምር እንደሚመለከት አስረድተዋል። 

“ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎቻችን ጋር ውይይት ጀምረናል። ገና አልጨረስንም። በሚቀጥለው ሣምንት እናገኛቸዋለን። የእነሱም እንደ ሌላው የዕዳ አይነት መፍትሔ ይኖረዋል” ሲሉ ዶክተር ኢዮብ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዳር 2007 የሸጠችውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዩሮ ቦንድ በሚቀጥለው ዓመት ይጎመራል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ ሳሉ የተሸጠው የኢትዮጵያ ቦንድ 6.625 በመቶ ወለድ የሚከፈልበት ነው። የቦንዱ ገዢዎች የኢትዮጵያን የመክፈያ ጊዜ ከ2024 ወደ 2029 ወይም 2030 የማራዘም ፍላጎት እንዳላቸው ሬውተርስ ዘግቧል።