1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፦ ሚያዚያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም.

Hirut Melesseዓርብ፣ ሚያዝያ 18 2016

የሚያዚያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. አርዕሰተ ዜና የአፍሪቃ ሕብረት «የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው» በሚል የተሰራጨው መረጃ «የተሳሳተ» ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ። የሶማሊያ መንግሥት ራሽን በመስረቅ የተጠረጠሩ በዩናይትድ ስቴትስ የሰለጠኑ የልዩ ኮማንዶ አባላት ማገዱንና ማሰሩን አስታወቀ። በጋዛ ሰርጥ አስቸኳይ ፣ቅድመ ሁኔታ የሌለውና ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ቻይና ጥሪ አቀረበች። የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በጋዛ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ በጸጥታው ምክር ቤት የሚደረገውን ጥረት ማደናቀፍ እንዲቆምም ጠይቃለች።

https://p.dw.com/p/4fEoL

አዲስ አበባ   የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ 

የአፍሪቃ ሕብረት «የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው» በሚል የተሰራጨው መረጃ «የተሳሳተ» ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ የአፍሪቃ ሕብረት ግቢው ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳቡ ላይ በሀሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ለማዘዋወር ከተደረገበት ሙከራ በኋላ የወጡ መሰል «ከሕብረቱ ጋር ባደረግነው ቀጥተኛ ውይይት ይህ አይነት እሳቤ በተቋሙ ውስጥ እንደሌለ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል» ሲሉ ተናግረዋል።

ኅብረቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ሊቀ ዐዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ከሳምንት በፊት«ከሕብረቱ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ» የተባሉ ሀሰተኛ ሰነዶች በመጠቀም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከኅብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ ለማዘዋወር ሲሞክሩ ከተያዙ በኋላ ነበር The Reporter የእንግሊዝኛው ጋዜጣ የኅብረቱን የገንዘብ ባለሞያች ጠቅሶ ሕብረቱ የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ከኢትዮጵያ ሊያዘዋውር መሆኑን እንደገለፁለት የዘገበው።

መቅዲሾ       የሶማሊያ መንግሥት ራሽን ሰርቀዋል ያላቸውን ኮማንዶዎች አሰረ

 

የሶማሊያ መንግሥት ራሽን በመስረቅ የተጠረጠሩ በዩናይትድ ስቴትስ የሰለጠኑ የልዩ ኮማንዶ አባላት ማገዱንና ማሰሩን አስታወቀ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚቀርበውን ራሽን ሰረቁ ስለተባሉት ስለእነዚሁ ኮማንዶዎች ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጋሮች እንዲያውቁት መደረጉንና የምርመራውን ውጤትም እንደሚያጋራ የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ድናብ የተባለው የኮማንዶዎቹ ክፍል ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለውን አሸባብን ለመውጋት በሚደረጉት ጥረቶች ዩናይትድ ስቴትስ ከምትደግፋቸው መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ ለድናብ 5 ወታደራዊ ጦር ሰፈሮችን ለመገንባት ከ 100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ለማድረግ ባለፈው የካቲት ወር ተስማምታለች። ዋሽንግተን 3 ሺህ አባላት ያሉት ልዩ ኮማንዶው በአሸባብ ላይ ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ለማሰልጠንና ለማስታጠቅ የተስማማው በጎርጎሮሳዊውe 2017 ዓም ነበር አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን ለሮይተርስ በላኩት መግለጫ ዋሽንግተን ከሙስና ጋር የተያያዙ ክሶችን ከምር የምትወስደው ጉዳይ ነው ብለዋል።

 

ናይሮቢ          ጅቢቲ ባህር ላይ ሰኞ ከሰጠመችው ጀልባ ተሳፋሪዎች 24ቱ መሞታቸው ተረጋገጠ

 

ጅቡቲ ባህር ላይ በሰጠመችው ጀልባ ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 77 ሰዎችን አሳፍራ የነበረችው ጀልባ በደረሰባት አደጋ የሞቱት ቁጥር ወደ 24 ከፍ ማለቱን የተመ የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት አስታወቋል።  በሁለት ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሰኞ በደረሰው በዚሁ የጀልባ መስጠም አደጋ መሞታቸው ከተረጋገጠው 24 ሰዎች ሌላ 20 ደግሞ እስከ ትናንት ድረስ የደረሱበት እንዳልታወቀ ድርጅቱ ገልጿል። ከአደጋው የተረፉ 33 ሰዎች ደግሞ ኦቦክ በሚገኘው የድርጅቱ ማዕከል እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑንንም አስታውቋል። የጠፉት ፍለጋም ቀጥሏል። ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያውያንን ጭና የነበረች አነስተኛ ጀልባ ጅቡቲ ሰጥማ የ38 ኢትዮጵያውያን ሕይወት አልፏል። IOM እንዳለው ይህችው ወደ ሳዑዲ አረብያ መጓዝ ጀምራ የነበረችው ጀልባ ጉዞ ግብዋ ሳይሳካላት ሲቀር ከየመን ወደ ጅቢቲ ስትመለስ ነበር ጅቡቲ ባህር ላይ የሰጠመችው። ድርጅቱ እንደሚለው በዚሁ በምሥራቁ የፍልሰት መስመር ከዛሬ 10 ዓመት ወዲህ 1350 ሰዎች ሞተዋል። በ ጎሮጎሮሳዊው 2023 ዓም ብቻ 698 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ 105 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።  

 

ለንደን   የብሪታንያ ፖሊስ ሕገ ወጥ ፍልሰትን በማገዝ የጠረጠራቸውን ከሰሰ

 

የብሪታንያ ፖሊስ ሕገ ወጥ ፍልሰትን በማገዝ የጠረጠራቸውን ሁለት ሰዎች ከሰሰ።የብሪታንያ ብሔራዊ የወንጀል ጉዳዮች ድርጅት እንዳስታወቀ ከሁለቱ ተጠርጣሪዎች አንዱ የ22 ዓመት ደቡብ ሱዳናዊ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ብሪታንያ ለመግባት የሞከሩ ፍልሰተኞችን በመርዳትና ካለ ሕጋዊ የመግቢያ ፈቃድ ብሪታንያ ለመግባት በመሞከር ተከሷል። ሌላኛው ከሱዳን የመጣ የ22 ዓመት ወጣትም ያለ ሕጋዊ የመግቢያ ፈቃድ ብሪታንያ ለመግባት በመሞከር ነው የተከሰሰው።  በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ደቡብ ምሥራቅ እንግሊዝ ኬንት ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት ዛሬ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሌላ ከሱዳን የመጣ ተጨማሪ ምርመራዎች ይካሄዱበታል የተባለ የ18 ዓመት ወጣት ደግሞ በዋስ መለቀቁ ተገልጿል። ፖሊስ ክሱን የመሰረተው በዚህ ሳምንት ማክሰኞ በትንሽ ጀልባ የእንግሊዝ ቻናልን አቋርጠው ወደ ብሪታንያ ለመሄድ ከሞከሩት መካከል የአምስት ስደተኞች ሕይወት ካለፈ በኋላ ነው። የፍልሰተኞቹ ሕይወት ያለፈው የብሪታንያ ፓርላማ ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ወደ ሩዋናዳ ለማባረር የሚያስችለውን ሕግ ባጸደቀ በሰዓታት ውስጥ ነበር። ከዚህ ዓመት ጥር ወዲህ በፈረንሳይ በኩል በትናንሽ ጀልባዎች ብሪታንያ የገቡት ፍልሰተኞች ቁጥር ወደ 6 ሺህ አምስት መቶ እንደሚደርስ ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል።

 

ቤይጂንግ   ቻይና በጋዛ ሰርጥ አስቸኳይ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረበች

 

ቻይና በጋዛ ሰርጥ አስቸኳይ ፣ቅድመ ሁኔታ የሌለውና ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረበች።  የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ትንናት በሰጡት መግለጫ የፍልስጤማውያንን ስቃይ ለማቆም በተቻለ ፍጥነት በጋዛ የተኩስ አቁም ሊደረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።ዌንቢን በጋዛ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ በጸጥታውe ምክር ቤት የሚደረገውን ጥረት ማደናቀፍ ይቅር የማይባል ነው ሲሉም ኮንነዋል።

« ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሀገራት የጸጥታው ምክር ቤትን እርምጃዎች ማደናቀፍን በማቆም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ የተባበሩት መንግሥትት ውሳኔ 2728 ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር በጋዛ አስቸኳይ ፣ቅድመ ሁኔታ የሌለው እና ዘላቂ የተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲሆን ፣ ሳይታጎል ሰብዓዊ እርዳታ በዘላቂነት መድረሱ እንዲረጋገጥ ጥሪ እናቀርባለን። »

200 ቀናት ባለፉት የእስራኤል ሀማስ ጦርነት የተመድ እንደሚለው 10 ሺህ ሴት ከመካከላቸው ስድስት ሺሁ እናቶች ናቸው።በጦርነቱ ምክንያትም 19 ሺህ ህጻናት ወላጅ አልባ ሆነዋል። በአጠቃላይ ጦርነቱ የገደላቸው ፍልስጤማውያን ቁጥር በሀማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር እንደተናገረው ከ34 ሺህ በላይ ነው። የቆሰሉት ደግሞ ከ 77 ሺህ ይበልጣሉ።

 

እየሩሳሌም፤የግብጽ ልዑካን ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር ተነጋገሩ

 

 

የግብጽ ልዑካን የጋዛውን ጦርነት ለማስቆምና እስራኤላውያን ታጋቾችን ለማስመለስ ንግግር የሚጀመርበትን መንገድ ለመፈለግ  ዛሬ ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸው ተሰማ። አንድ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደነገሩት ምንም እንኳን እስራኤል 33 ታጋቾቿ እንዲለቀቁ የተገደበ የተኩስ አቁም የማድረግ ፍላጎት ቢኖራትም አሁን ግን የምታቀርበው አዲስ ሀሳብ የላትም። ባለስልጣኑ እንዳሉት አሁን በእስራኤልና በሀማስ መካከል ታጋቾችን የሚመለከት ንግግርም ሆነ ይህን በሚመለከት እሥራኤል ያቀረበችው አዲስ ሃሳብ የለም። አሁን ያለው ነገር ግብጽ የምታደርገው ንግግሩን መልሶ የማስጀመር ጥረት ብቻ ነው ብለዋል። ግብጽ የ33ቱን ታጋቾች መለቀቅ የሚያካትት ሀሳብ አቅርባለች። የእስራኤል የደኅንነት ባለሥልጣናት ሀማስ ያያዛቸው 33 ሴቶች ፣አረጋውያንና ታማሚ ታጋቾች ጋዛ ውስጥ በሕይወት አሉ ብለው ያምናሉ።እስካሁን ድረስ ዋና አደራዳሪ የነበረችው ቃታር የሀማስ መሪዎችን ከግዛቷ እንድታስወጣና የገንዘብ ምንጫቸውን እንድትዘጋ እስራኤል ያቀረበችውን ጥያቄ ባለመቀበልዋ የግንባር ቀደም አደራዳሪነትዋ ሚና ቀንሷል።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።