1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በይፋ ብሪክስን ስትቀላቀል ባለሙያዎች ስለ ፋይዳው ጥርጣሬ ገብቷቸዋል

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2016

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ (Sherpa) ሆነው ተሾመዋል። ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ኢራንን የተቀበለው ብሪክስ የአባላቱ ቁጥር 10 ደርሷል። የብሪክስ መስፋፋት ተጽዕኖውን እንደሚያሳድገው ቢታመንም ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ለሀገራቸው በሚኖረው ፋይዳ ላይ ጥያቄ አላቸው።

https://p.dw.com/p/4alsQ
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ (Sherpa) ሆነው ተሾመዋል።ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

ኢትዮጵያ በይፋ ብሪክስን ስትቀላቀል ባለሙያዎች ስለ ፋይዳው ጥርጣሬ ገብቷቸዋል

ኢትዮጵያ ነሐሴ 2015 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ውስጥ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ የስብስቡ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ተከትሎ ዛሬ አባል ሀገርነቷ በይፋ ይጀምራል። ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ተደርጎ ተወስዷል። 

ኢትዮጵያ ብሪክስን ለምን ተቀላቀለች? 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሲየሽን ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው "የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕቀብ ጫና ስለበዛባት" መሆኑን በጉዳዩ ላይ ባደረገው ጥናት ከተሳተፉ 330 ባለሙያዎች አብዛኞቹ ሲደመድሙ፣ ሌሎች ደግሞ "የውጭ ግንኙነቷ በጣም እየወረደ ስለመጣ" ነው ብለዋል። የውጭ ጣልቃ ገብነት መብዛትም በጥናቱ እንደ አንድ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ምጣኔ ሐብታዊ ወይስ ፖለቲካዊ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ መሆኗ ታይቶና ታምኖበት ይህንን ስብስብ ለመቀላቀል ይሁንታ ማግኘቷን በወቅቱ ገልፀዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና እንደሚሉት ግን ጉዳዩ ሌላ ነው። "ፈልጋ የገባች አይመስለኝም። ጎትተው ያስገቧት ነው የሚመስለኝ። በተለይ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል የሚያስችል አቅም አላት ?

የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ምዕራባዊያን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ስትወድቅ በሀገር ሕልውና እና ነፃነት ላይ ጣልቃ መግባታቸው በጉልህ በመንግስት በኩል ስለታመነበት ቻይና እና ሩሲያ ወደሚመሩት ስብስብ ፊትን የማዞር ችኩል እርምጃ መገባቱን አመልክተው የውሳኔው መነሻ ግን ውስጣዊ ሁኔታ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል። "አንድ ውሳኔ ለመወሰን ከውስጥ ወደ ውጭ የሚመነጭ አቋም ነው መኖር የነበረበት" ሲሉ ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ መሆኗ ታይቶና ታምኖበት ይህንን ስብስብ ለመቀላቀል ይሁንታ ማግኘቷን በወቅቱ ገልፀዋል።ምስል Reuters/T. Negeri

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር በመሆኗ ከዋና ዋና የገንዘብ ተቋማት የብድር ክልከላ እና መቋረጥ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት መቀነስ ሊገጥም እንደሚችል የኢኮኖሚክ አሶሴሽን ጥናት አመልክቷል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን የጠየቀችዉ ጎራ ለማማረጥ አይደለም-ዉጉሚ

ስብስቡን የተቀላቀለችው "የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ችግር" ውስጥ በመሆኗ መሆኑንም የባለሙያዎች ቡድን የጥናት ውጤት አሳይቷል። አቶ ክቡር ገና መንግሥት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ስላለች ይሁንታ አገኘች በሚል ያቀርበው ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጠይቃ ይሁንታ ሳታገኝ እስካሁን አመታት የተቆጠረበትን እና የብሪክስ አባል ለመሆን የቻለችበትን ፍጥነት በአግባቡ መመዘን ከጀርባ ያለውን ምክንያት በውል የሚያስረዳ አድርገውም አቅርበውታል።

አዲስ አበባ ከተማ
ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው "የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ችግር" ውስጥ በመሆኗ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር የጥናት ውጤት አሳይቷል።ምስል Solomon Muchie/DW

"በመንግሥት በኩል የሚቀርበው 120 ሚሊዮን ሕዝብ አለን ነው። ሌላ ነገር የለም። ጠጋ ብለህ ስትመለከተው 120 ሚሊዮን ሕዝብ በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነው እንጂ በማደግ፣ ሀብት በማፍራት፣ ኢኮኖሚውን በማሳደግ ላይ ያለ ሀገር አይደለም" ብለዋል። 

 የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት አንድምታ

አቶ ሽዋፈራሁ ሽታሁን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን ከመወሰኑ በፊት "የዲፕሎማሲ አቅጣጫውን በአግባቡ መመዘን" እንዳለበት ይገልጻሉ። አክለውም "የአጭር ጊዜ ጥቅም መስዋዕት ሆኖ የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ጥቅም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ባይ ናቸው። ከምእራቡ አለም "በገንዘብም፣ በፖለቲካ ተፈላጊነትም አቅም ሊያሳጣት የሚችል" እርምጃ መውሰድ ሊኖርባት የተገባ እንዳልሆነም አክለዋል። "ይሄ ውሳኔ በበቂ ምክንያት የተደገፈ ውሳኔ ነው ለማለት ያስቸግረኛል" ብለዋል። 

ብራዚል ፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ያቋቋሙት ብሪክስ የተባለው ስብስብ ነሐሴ 2015 ዓ. ም ላይ ባደረገው ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገሮችን በአባልነት ተቀብሏል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሲየሽን የተከናወነው ጥናት ኢትዮጵያ ከስብስቡ አባል ሀገራት ተነፃፃሪ የገንዘብ እና የአስተዳደር ሥርዓት ካልዘረጋች ፣ ነፃና ገለልተኛ ብሔራዊ ባንክ እንዲኖራት ካላደረገች ብሪክስን መቀላቀሏ የረባ ጥቅም እንደማያስገኛት አመልክቷል።

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር